በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

ኢያሱ 6:1-27

የመጽሐፉ ይዘት

  • የኢያሪኮ ግንብ ፈረሰ (1-21)

  • ረዓብና ቤተሰቧ ከጥፋት ተረፉ (22-27)

6  ኢያሪኮ በእስራኤላውያን የተነሳ ጥርቅም ተደርጋ ተዘግታ ነበር፤ ወደ ውጭ የሚወጣም ሆነ ወደ ውስጥ የሚገባ አልነበረም።+  ይሖዋም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ ኢያሪኮን፣ ንጉሥዋንና ኃያል ተዋጊዎቿን በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ።+  ተዋጊ የሆናችሁት ወንዶችም ሁሉ ከተማዋን ዙሪያዋን በመሄድ አንድ ጊዜ ዙሯት። ለስድስት ቀን እንዲህ አድርጉ።  ሰባት ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት* ይዘው በታቦቱ ፊት ይሂዱ። በሰባተኛው ቀን ግን ከተማዋን ሰባት ጊዜ ዙሯት፤ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ።+  ቀንደ መለከቱ ሲነፋና የቀንደ መለከቱን ድምፅ* ስትሰሙ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ የጦርነት ጩኸት ያሰማ። ከዚያም የከተማዋ ቅጥር ይፈራርሳል፤+ ሕዝቡም ሁሉ፣ እያንዳንዱም ሰው ቀጥ ብሎ ወደ ፊት ይሂድ።”  ስለዚህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ካህናቱን አንድ ላይ ጠርቶ “የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሱ፤ ሰባት ካህናትም ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በይሖዋ ታቦት ፊት ይሂዱ” አላቸው።+  ሕዝቡንም “እናንተ ተነሱና ከተማዋን ዙሩ፤ የታጠቁት ተዋጊዎችም+ ከይሖዋ ታቦት ቀድመው ይሄዳሉ” አላቸው።  ኢያሱ ለሕዝቡ በተናገረው መሠረት ሰባት ቀንደ መለከት የያዙት ሰባት ካህናት በይሖዋ ፊት ቀድመው በመሄድ ቀንደ መለከታቸውን ነፉ፤ የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦትም ይከተላቸው ነበር።  የታጠቁትም ተዋጊዎች ቀንደ መለከቱን ከሚነፉት ካህናት ቀድመው ሄዱ፤ የኋላው ደጀን ደግሞ ታቦቱን ይከተል ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ቀንደ መለከቱ ያለማቋረጥ ይነፋ ነበር። 10  ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ ሲል አዘዘ፦ “መጮኽም ሆነ ድምፃችሁን ማሰማት የለባችሁም። እኔ ‘ጩኹ!’ ብዬ እስከማዛችሁ ቀን ድረስ ከአፋችሁ አንድም ቃል መውጣት የለበትም። ከዚያ በኋላ ትጮኻላችሁ።” 11  እሱም የይሖዋ ታቦት በከተማዋ ዙሪያ በመሄድ ከተማዋን አንድ ጊዜ እንዲዞር አደረገ፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው በዚያ አደሩ። 12  በሚቀጥለው ቀን ኢያሱ በማለዳ ተነሳ፤ ካህናቱም የይሖዋን ታቦት አነሱ፤+ 13  ሰባት ቀንደ መለከት የያዙ ሰባት ካህናት ያለማቋረጥ መለከታቸውን እየነፉ ከይሖዋ ታቦት ፊት ፊት ይሄዱ ነበር። የታጠቁት ተዋጊዎችም ከእነሱ ፊት ይሄዱ ነበር፤ የኋላው ደጀን ደግሞ የይሖዋን ታቦት ይከተል ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ቀንደ መለከቱ ያለማቋረጥ ይነፋ ነበር። 14  በሁለተኛውም ቀን ከተማዋን አንድ ጊዜ ዞሯት፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ ተመለሱ። ለስድስት ቀን ልክ እንደዚሁ አደረጉ።+ 15  በሰባተኛው ቀን ገና ጎህ ሲቀድ ተነስተው ከተማዋን በዚሁ መንገድ ሰባት ጊዜ ዞሯት። ከተማዋን ሰባት ጊዜ የዞሯት በዚያ ቀን ብቻ ነበር።+ 16  በሰባተኛው ዙር ላይ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ ከተማዋን አሳልፎ ስለሰጣችሁ ጩኹ!+ 17  ከተማዋም ሆነች በውስጧ ያለው ነገር ሁሉ ሙሉ በሙሉ መጥፋት አለበት፤+ ከተማዋ ሙሉ በሙሉ የይሖዋ ነች። በሕይወት የሚተርፉት ዝሙት አዳሪዋ ረዓብና+ ከእሷ ጋር በቤቱ ውስጥ ያሉት ብቻ ናቸው፤ ምክንያቱም እሷ የላክናቸውን መልእክተኞች ደብቃለች።+ 18  እናንተ ግን ለጥፋት የተለየው ነገር እንዳያጓጓችሁና እንዳትወስዱት፣ በእስራኤልም ሰፈር ላይ መዓት* በማምጣት ሰፈሩን ለጥፋት የተለየ እንዳታደርጉት+ ለጥፋት ከተለየው ነገር ራቁ።+ 19  ሆኖም ብሩ፣ ወርቁ እንዲሁም ከመዳብና ከብረት የተሠሩት ዕቃዎች ሁሉ ለይሖዋ የተቀደሱ ናቸው።+ ወደ ይሖዋ ግምጃ ቤት መግባት አለባቸው።”+ 20  ከዚያም ቀንደ መለከቱ ሲነፋ ሕዝቡ ጮኸ።+ ሕዝቡ የቀንደ መለከቱን ድምፅ ሰምቶ ታላቅ የጦርነት ጩኸት ሲያሰማ ቅጥሩ ፈረሰ።+ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ፣ እያንዳንዱም ሰው በቀጥታ ወደ ከተማዋ በመግባት ከተማዋን ያዛት። 21  እነሱም በከተማዋ ውስጥ የነበረውን በሙሉ ይኸውም ወንዱንና ሴቱን፣ ወጣቱንና ሽማግሌውን እንዲሁም በሬውን፣ በጉንና አህያውን በሰይፍ ሙሉ በሙሉ አጠፉ።+ 22  ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉትን ሁለቱን ሰዎች “ወደ ዝሙት አዳሪዋ ቤት ገብታችሁ በማላችሁላት መሠረት ሴትየዋንና የእሷ የሆነውን ሁሉ ከዚያ አውጡ” አላቸው።+ 23  በመሆኑም ወጣቶቹ ሰላዮች ገብተው ረዓብን፣ አባቷን፣ እናቷን፣ ወንድሞቿንና የእሷ የሆነውን ሁሉ አዎ፣ ቤተሰቧን በሙሉ+ አውጥተው ከእስራኤል ሰፈር ውጭ ወዳለ ስፍራ በሰላም አመጧቸው። 24  ከዚያም ከተማዋንና በውስጧ የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። ብሩን፣ ወርቁን እንዲሁም ከመዳብና ከብረት የተሠሩትን ዕቃዎች ግን ወደ ይሖዋ ግምጃ ቤት አስገቡ።+ 25  ኢያሱ በሕይወት እንዲተርፉ ያደረገው ዝሙት አዳሪዋን ረዓብን፣ የአባቷን ቤተሰብና የእሷ የሆነውን ብቻ ነበር፤+ እሷም እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤል መካከል ትኖራለች፤+ ምክንያቱም ኢያሱ ኢያሪኮን እንዲሰልሉ የላካቸውን መልእክተኞች ደብቃ ነበር።+ 26  በዚያን ጊዜ ኢያሱ ይህን ቃለ መሐላ አወጀ፦* “ይህችን የኢያሪኮን ከተማ ለመገንባት የሚነሳ ሰው በይሖዋ ፊት የተረገመ ይሁን። የከተማዋን መሠረት ሲጥል የበኩር ልጁ ይጥፋ፤ በሮቿንም ሲያቆም የመጨረሻ ልጁ ይጥፋ።”+ 27  ይሖዋም ከኢያሱ ጋር ነበር፤+ በመላውም ምድር ላይ ዝነኛ ሆነ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ከአውራ በግ ቀንድ የተሠራ መለከት።”
ወይም “ቀንደ መለከቱ በረጅሙ ሲነፋ።”
ወይም “ችግር፤ መጠላት።”
“ሕዝቡ ይህን ቃለ መሐላ እንዲምል አደረገ” ማለትም ሊሆን ይችላል።