በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ኢያሱ 23:1-16

የመጽሐፉ ይዘት

  • ኢያሱ ለእስራኤል መሪዎች የተናገራቸው የስንብት ቃላት (1-16)

    • ይሖዋ ከተናገረው ቃል ሳይፈጸም የቀረ የለም (14)

23  ይሖዋ እስራኤላውያንን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፋቸው+ ከብዙ ጊዜ በኋላ፣ ኢያሱም አርጅቶና ዕድሜው ገፍቶ ሳለ+  ኢያሱ እስራኤላውያንን በሙሉ፣ ሽማግሌዎቻቸውን፣ መሪዎቻቸውን፣ ዳኞቻቸውንና አለቆቻቸውን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦+ “እንግዲህ እኔ አርጅቻለሁ፤ ዕድሜዬም ገፍቷል።  አምላካችሁ ይሖዋ ለእናንተ ሲል በእነዚህ ብሔራት ላይ ያደረገውን ሁሉ ራሳችሁ አይታችኋል፤ ምክንያቱም ለእናንተ እየተዋጋላችሁ የነበረው አምላካችሁ ይሖዋ ነው።+  እኔም ከዮርዳኖስ አንስቶ በስተ ምዕራብ* እስከሚገኘው እስከ ታላቁ ባሕር* ድረስ ያጠፋኋቸውን ብሔራት ሁሉ ምድር+ ጨምሮ የቀሩትን ብሔራት ምድር+ ለየነገዶቻችሁ ርስት እንዲሆን በዕጣ አከፋፍዬ+ ሰጥቻችኋለሁ።  እነሱን ከፊታችሁ ያባረራቸው አምላካችሁ ይሖዋ ነው፤+ እሱም ለእናንተ ሲል አባረራቸው፤* እናንተም አምላካችሁ ይሖዋ በገባላችሁ ቃል መሠረት ምድራቸውን ወረሳችሁ።+  “እንግዲህ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ+ ውስጥ ከተጻፈው ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ፈጽሞ ዞር ሳትሉ+ ሕጉን ሁሉ ለመጠበቅና ለመፈጸም ደፋሮች ሁኑ፤  እንዲሁም በመካከላችሁ ከቀሩት ከእነዚህ ብሔራት ጋር አትቀላቀሉ።+ ሌላው ቀርቶ የአማልክታቸውን ስም አታንሱ፤+ በእነሱም አትማሉ፤ ፈጽሞ አታገልግሏቸው እንዲሁም አትስገዱላቸው።+  ከዚህ ይልቅ እስከዚህ ቀን ድረስ እንዳደረጋችሁት ሁሉ ከአምላካችሁ ከይሖዋ ጋር ተጣብቃችሁ ኑሩ።+  ይሖዋ ታላላቅና ኃያላን ብሔራትን ከፊታችሁ ያባርራቸዋል፤+ እስከዚህ ቀን ድረስ አንድም ሰው ሊቋቋማችሁ አልቻለም።+ 10  አምላካችሁ ይሖዋ በገባላችሁ ቃል መሠረት+ ለእናንተ ስለሚዋጋላችሁ+ ከእናንተ አንዱ፣ ሺህ ሰው ያሳድዳል።+ 11  ስለዚህ አምላካችሁን ይሖዋን በመውደድ+ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።*+ 12  “ይሁንና ወደ ኋላ ዞር ብትሉና ከእነዚህ ብሔራት መካከል ተርፈው ከእናንተ ጋር ከቀሩት+ ሰዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ብትመሠርቱ፣ በጋብቻ ብትዛመዱ+ እንዲሁም እናንተ ከእነሱ ጋር ብትወዳጁ፣ እነሱም ከእናንተ ጋር ወዳጅነት ቢመሠርቱ 13  አምላካችሁ ይሖዋ ከዚህ በኋላ ለእናንተ ሲል እነዚህን ብሔራት እንደማያባርራቸው* በእርግጥ እወቁ።+ እነሱም አምላካችሁ ይሖዋ ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር ላይ እስክትጠፉ ድረስ ወጥመድ፣ አሽክላ፣ ለጀርባችሁ ጅራፍ እንዲሁም በዓይናችሁ ውስጥ እንዳለ እሾህ ይሆኑባችኋል።+ 14  “እንግዲህ እኔ መሞቻዬ ተቃርቧል፤* አምላካችሁ ይሖዋ ከገባላችሁ መልካም ቃል ሁሉ አንዲቷም እንኳ ሳትፈጸም እንዳልቀረች በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ* ታውቃላችሁ። ሁሉም ተፈጽሞላችኋል። ከመካከላቸው ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም።+ 15  ሆኖም አምላካችሁ ይሖዋ የገባላችሁ መልካም ቃል በሙሉ እንደተፈጸመላችሁ ሁሉ ይሖዋ አመጣባችኋለሁ ብሎ+ የተናገረውን ጥፋት ሁሉ* ያመጣባችኋል፤ አምላካችሁ ይሖዋ ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድርም ያጠፋችኋል።+ 16  አምላካችሁ ይሖዋ እንድትጠብቁት ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ካፈረሳችሁ እንዲሁም ሄዳችሁ ሌሎች አማልክትን ካገለገላችሁና ለእነሱ ከሰገዳችሁ የይሖዋ ቁጣ በእናንተ ላይ ይነድዳል፤+ ከሰጣችሁም መልካም ምድር ላይ በፍጥነት ትጠፋላችሁ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በፀሐይ መግቢያ።”
ሜድትራንያንን ያመለክታል።
ወይም “አስለቀቃቸው።”
ወይም “ነፍሳችሁን በጥንቃቄ ጠብቁ።”
ወይም “እንደማያስለቅቃቸው።”
ቃል በቃል “ዛሬ የምድርን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው።”
ወይም “ክፉ ቃል ሁሉ።”