በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

ኢያሱ 2:1-24

የመጽሐፉ ይዘት

  • ኢያሱ ሁለት ሰላዮችን ወደ ኢያሪኮ ላከ (1-3)

  • ረዓብ ሰላዮቹን ደበቀች (4-7)

  • ለረዓብ የተገባላት ቃል (8-21ሀ)

    • ለምልክት የሚያገለግለው ቀይ ገመድ (18)

  • ሰላዮቹ ወደ ኢያሱ ተመለሱ (21ለ-24)

2  ከዚያም የነዌ ልጅ ኢያሱ ከሺቲም+ ሁለት ሰላዮችን በድብቅ ላከ። እነሱንም “እስቲ ሄዳችሁ ምድሪቱን በተለይም ኢያሪኮን አይታችሁ ኑ” አላቸው። ሰዎቹም ሄደው ረዓብ+ ወደተባለች አንዲት ዝሙት አዳሪ ቤት ገቡ፤ በዚያም አረፉ።  የኢያሪኮም ንጉሥ “እስራኤላውያን የሆኑ ሰዎች ምድሪቱን ለመሰለል ዛሬ ማታ ወደዚህ መጥተዋል” ተብሎ ተነገረው።  በዚህ ጊዜ የኢያሪኮ ንጉሥ ወደ ረዓብ እንዲህ የሚል መልእክት ላከባት፦ “ቤትሽ መጥተው ያረፉትን ሰዎች አውጪ፤ ምክንያቱም ወደዚህ የመጡት ምድሪቱን በሙሉ ለመሰለል ነው።”  ሴትየዋ ግን ሁለቱን ሰዎች ደበቀቻቸው። ከዚያም እንዲህ አለች፦ “በእርግጥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተው ነበር፤ ሆኖም ከየት እንደመጡ አላወቅኩም።  ምሽት ላይ የከተማዋ በር ሊዘጋ ሲል ወጥተው ሄደዋል። ወዴት እንደሄዱ አላውቅም፤ ሆኖም ፈጥናችሁ ከተከታተላችኋቸው ልትደርሱባቸው ትችላላችሁ።”  (ይሁንና ሰዎቹን ጣሪያ ላይ ይዛቸው ወጥታ በተረበረበ የተልባ እግር ውስጥ ደብቃቸው ነበር።)  ሰዎቹም ሰላዮቹን በመከታተል ወደ ዮርዳኖስ አቅጣጫ በመልካው*+ በኩል ሄዱ፤ አሳዳጆቹ ወጥተው እንደሄዱም የከተማዋ በር ተዘጋ።  እሷም ሰላዮቹ ከመተኛታቸው በፊት እነሱ ወዳሉበት ወደ ጣሪያው ወጣች።  እንዲህም አለቻቸው፦ “ይሖዋ ምድሪቱን እንደሚሰጣችሁ አውቃለሁ፤+ እኛም እናንተን በመፍራት ተሸብረናል።+ የምድሪቱ ነዋሪዎች በሙሉ በእናንተ የተነሳ ልባቸው ከድቷቸዋል፤+ 10  ምክንያቱም ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ ይሖዋ ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀው+ እንዲሁም ከዮርዳኖስ ማዶ* በደመሰሳችኋቸው በሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት፣ በሲሖንና+ በኦግ+ ላይ ምን እንዳደረጋችሁ ሰምተናል። 11  ይህን ስንሰማ ልባችን ቀለጠ፤ በእናንተም የተነሳ ወኔ ያልከዳው ማንም አልነበረም፤ ምክንያቱም አምላካችሁ ይሖዋ በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ ነው።+ 12  እንግዲህ እኔ ታማኝ ፍቅር እንዳሳየኋችሁ ሁሉ እናንተም ለአባቴ ቤት ታማኝ ፍቅር እንደምታሳዩ እባካችሁ በይሖዋ ማሉልኝ፤ እንዲሁም አስተማማኝ ምልክት ስጡኝ። 13  አባቴን፣ እናቴን፣ ወንድሞቼን፣ እህቶቼንና የእነሱ የሆነውን ሁሉ አትርፉልኝ፤ ከሞትም ታደጉን።”*+ 14  በዚህ ጊዜ ሰዎቹ እንዲህ አሏት፦ “በእናንተ ምትክ ሕይወታችንን እንሰጣለን!* ስለ ተልእኳችን ካልተናገራችሁ ይሖዋ ምድሪቱን በሚሰጠን ጊዜ ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት እናሳያችኋለን።” 15  እሷም ሰዎቹን በመስኮት በኩል በገመድ አወረደቻቸው፤ ምክንያቱም ቤቷ ከከተማው ቅጥር ጋር ተያይዞ የተሠራ ነበር። እንዲያውም የምትኖረው ቅጥሩ ላይ ነበር።+ 16  ከዚያም እንዲህ አለቻቸው፦ “የሚያሳድዷችሁ ሰዎች እንዳያገኟችሁ ወደ ተራራማው አካባቢ ሄዳችሁ ለሦስት ቀን ተደበቁ። ከዚያም የሚያሳድዷችሁ ሰዎች ከተመለሱ በኋላ ወደምትፈልጉት ቦታ መሄድ ትችላላችሁ።” 17  ሰዎቹም እንዲህ አሏት፦ “እንደሚከተለው ካላደረግሽ ባስማልሽን በዚህ መሐላ ተጠያቂ አንሆንም፦+ 18  ወደ ምድሪቱ በምንገባበት ጊዜ ይህን ቀይ ገመድ እኛን ባወረድሽበት መስኮት በኩል አንጠልጥይው። እንዲሁም አባትሽ፣ እናትሽ፣ ወንድሞችሽና የአባትሽ ቤት በሙሉ ቤትሽ ውስጥ እንዲሰበሰቡ ማድረግ አለብሽ።+ 19  ከቤትሽ ወጥቶ ደጅ የሚገኝ ማንኛውም ሰው ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ እኛም ከበደል ነፃ እንሆናለን። ሆኖም ከአንቺ ጋር ቤት ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ጉዳት ቢደርስበት* ደሙ በእኛ ላይ ይሆናል። 20  ስለ ተልእኳችን ከተናገርሽ+ ግን ባስማልሽን በዚህ መሐላ ተጠያቂ አንሆንም።” 21  እሷም “እንዳላችሁት ይሁን” አለቻቸው። ከዚያም አሰናበተቻቸው፤ እነሱም ሄዱ። እሷም ቀዩን ገመድ መስኮቱ ላይ አሰረችው። 22  እነሱም ወደ ተራራማው አካባቢ ሄደው አሳዳጆቹ እስኪመለሱ ድረስ በዚያ ለሦስት ቀን ተቀመጡ። አሳዳጆቹም በየመንገዱ ሁሉ ፈለጓቸው፤ ሆኖም አላገኟቸውም። 23  ከዚያም ሁለቱ ሰዎች ከተራራማው አካባቢ ወርደው ወንዙን በመሻገር ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ መጡ። ያጋጠማቸውንም ሁሉ ነገሩት። 24  ኢያሱንም እንዲህ አሉት፦ “ይሖዋ ምድሪቱን በሙሉ በእጃችን ሰጥቶናል።+ እንዲያውም የምድሪቱ ነዋሪዎች ሁሉ በእኛ የተነሳ ልባቸው ከድቷቸዋል።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።
በስተ ምሥራቅ ያለውን ያመለክታል።
ወይም “ነፍሳችንን ከሞት ታደጉ።”
ወይም “በእናንተ ምትክ ነፍሳችን ትሞታለች!”
ወይም “እጅ ቢያርፍበት።”