በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ኢያሱ 18:1-28

የመጽሐፉ ይዘት

  • የቀረው ምድር በሴሎ ተከፋፈለ (1-10)

  • የቢንያም ርስት (11-28)

18  ከዚያም መላው የእስራኤላውያን ማኅበረሰብ በሴሎ+ ተሰበሰበ፤ በዚህ ጊዜ ምድሪቱ በፊታቸው ተገዝታላቸው+ ስለነበር የመገናኛ ድንኳኑን በዚያ ተከሉ።+  ይሁንና ከእስራኤላውያን መካከል ገና ርስት ያልተሰጣቸው ሰባት ነገዶች ነበሩ።  በመሆኑም ኢያሱ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ “የአባቶቻችሁ አምላክ ይሖዋ የሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ለመውረስ ችላ የምትሉት እስከ መቼ ነው?+  ከእያንዳንዱ ነገድ ሦስት ሦስት ወንዶችን ስጡኝ፤ እኔም እልካቸዋለሁ፤ እነሱም ሄደው ምድሪቱን ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ በሚወርሱት ድርሻ መሠረት ይሸነሽኗታል። ከዚያም ተመልሰው ወደ እኔ ይመጣሉ።  ምድሪቱንም ሰባት ቦታ ይከፋፈሏታል።+ ይሁዳ በስተ ደቡብ ያለውን ክልሉን ይዞ ይኖራል፤+ የዮሴፍ ቤት ደግሞ በስተ ሰሜን ያለውን ክልሉን ይዞ ይኖራል።+  እናንተ ግን ምድሪቱን ሰባት ቦታ ትሸነሽኗታላችሁ፤ ከዚያም የሸነሸናችሁትን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እዚህ በአምላካችን በይሖዋ ፊት ዕጣ አወጣላችኋለሁ።+  ሌዋውያኑ ግን ለይሖዋ የሚያቀርቡት የክህነት አገልግሎት ውርሻቸው ስለሆነ+ በመካከላችሁ ድርሻ አይኖራቸውም፤+ ጋድ፣ ሮቤልና የምናሴ ነገድ እኩሌታም+ ቢሆኑ የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ በሰጣቸው መሠረት ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ርስታቸውን አስቀድመው ወስደዋል።”  ሰዎቹም ለመሄድ ተነሱ፤ ኢያሱም ምድሪቱን ለመሸንሸን የሚሄዱትን ሰዎች “ሂዱና ምድሪቱን ተዘዋውራችሁ በማየት ሸንሽኗት፤ ከዚያም ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እዚሁ በሴሎ በይሖዋ ፊት ዕጣ አወጣላችኋለሁ”+ ሲል አዘዛቸው።  ሰዎቹም ሄደው በምድሪቱ ተዘዋወሩ፤ ከዚያም በከተማ በከተማ ሰባት ቦታ ሸንሽነው በመጽሐፍ አሰፈሩት። በኋላም በሴሎ ባለው ሰፈር ወደሚገኘው ወደ ኢያሱ ተመልሰው መጡ። 10  ኢያሱም በሴሎ በይሖዋ ፊት ዕጣ አወጣላቸው።+ በዚያም ኢያሱ ምድሪቱን ለእስራኤላውያን በየድርሻቸው አከፋፈላቸው።+ 11  የመጀመሪያውም ዕጣ ለቢንያም ነገድ በየቤተሰቡ ወጣ፤ በዕጣ የደረሳቸውም ክልል በይሁዳ ሰዎችና+ በዮሴፍ ሰዎች+ መካከል የሚገኘው ነበር። 12  በሰሜን በኩል ያለው ወሰናቸው ከዮርዳኖስ ተነስቶ በስተ ሰሜን ወዳለው የኢያሪኮ+ ሸንተረር ይወጣና በስተ ምዕራብ ወደ ተራራው ያቀናል፤ ከዚያም ወደ ቤትአዌን+ ምድረ በዳ ይዘልቃል። 13  ከዚያ ደግሞ ወሰኑ ቤቴል+ ወደምትባለው ወደ ሎዛ ማለትም ወደ ሎዛ ደቡባዊ ሸንተረር ያቀናል፤ በመቀጠልም ከታችኛው ቤትሆሮን+ በስተ ደቡብ በሚገኘው ተራራ ላይ አድርጎ ወደ አጣሮትዓዳር+ ይወርዳል። 14  በስተ ምዕራብ ያለው ወሰንም በስተ ደቡብ በኩል ከቤትሆሮን ትይዩ ከሆነው ተራራ በመነሳት ወደ ደቡብ ይታጠፋል፤ ከዚያም የይሁዳ ከተማ የሆነችው ቂርያትበአል ይኸውም ቂርያትየአሪም + ጋ ሲደርስ ያበቃል። ይህ ምዕራባዊው ወሰን ነው። 15  በስተ ደቡብ ያለው ወሰን ደግሞ ከቂርያትየአሪም ጫፍ ተነስቶ ወደ ምዕራብ ይዘልቃል፤ ከዚያም ወደ ነፍቶአ+ የውኃ ምንጭ ይወጣል። 16  ከዚያም ከሂኖም ልጅ ሸለቆ+ ፊት ለፊት ወደሚገኘውና በረፋይም ሸለቆ*+ ሰሜናዊ ጫፍ ወዳለው ተራራ ግርጌ ይወርዳል፤ በመቀጠልም ወደ ሂኖም ሸለቆ ይኸውም በስተ ደቡብ ወደሚገኘው ወደ ኢያቡሳውያን+ ሸንተረር ይወርድና እስከ ኤንሮጌል+ ይዘልቃል። 17  ከዚያም ወደ ሰሜን በማቅናት ወደ ኤንሼሜሽ ያልፍና ከአዱሚም አቀበት+ ፊት ለፊት እስከምትገኘው እስከ ገሊሎት ይደርሳል፤ በመቀጠልም የሮቤል ልጅ የቦሃን+ ድንጋይ+ እስካለበት ድረስ ይወርዳል። 18  ወሰኑ አረባ ፊት ለፊት ወዳለው ሰሜናዊ ሸንተረር ይሄድና ቁልቁል ወደ አረባ ይወርዳል። 19  ከዚያም ወደ ቤትሆግላ+ ሰሜናዊ ሸንተረር ይዘልቅና በዮርዳኖስ ደቡባዊ ጫፍ፣ የጨው ባሕር*+ ሰሜናዊ ዳርቻ ላይ ሲደርስ ያበቃል። ደቡባዊው ወሰን ይህ ነበር። 20  በስተ ምሥራቅ በኩል ወሰኑ ዮርዳኖስ ነበር። የቢንያም ዘሮች በየቤተሰባቸው ያገኙት ርስት ወሰን ዙሪያውን ይህ ነበር። 21  የቢንያም ነገድ በየቤተሰቡ ያገኛቸው ከተሞች እነዚህ ናቸው፦ ኢያሪኮ፣ ቤትሆግላ፣ ኤሜቀጺጽ፣ 22  ቤትአረባ፣+ ጸማራይም፣ ቤቴል፣+ 23  አዊም፣ ጳራ፣ ኦፍራ፣ 24  ከፋርአሞናይ፣ ኦፍኒ እና ጌባ፤+ በአጠቃላይ 12 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ። 25  ገባኦን፣+ ራማ፣ በኤሮት፣ 26  ምጽጳ፣ ከፊራ፣ ሞጻ፣ 27  ራቄም፣ ይርጰኤል፣ ታራላ፣ 28  ጸላህ፣+ ኤሌፍ፣ ኢያቡስ ማለትም ኢየሩሳሌም፣+ ጊብዓ+ እና ቂርያት፤ በአጠቃላይ 14 ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ነበሩ። የቢንያም ዘሮች በየቤተሰባቸው ያገኙት ርስት ይህ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ሙት ባሕርን ያመለክታል።