በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ኢያሱ 11:1-23

የመጽሐፉ ይዘት

  • በስተ ሰሜን ያሉት ከተሞች ተያዙ (1-15)

  • ኢያሱ ድል ያደረጋቸው አካባቢዎች (16-23)

11  የሃጾር ንጉሥ ያቢን ይህን ሲሰማ ወደ ማዶን ንጉሥ+ ወደ ዮባብ፣ ወደ ሺምሮን ንጉሥ፣ ወደ አክሻፍ ንጉሥ+  እንዲሁም በስተ ሰሜን በሚገኘው ተራራማ አካባቢ፣ በደቡብ ኪኔሬት ባሉት ሜዳዎችና* በሸፌላ ወደሚገኙት እንዲሁም በስተ ምዕራብ በዶር+ ሸንተረሮች ወዳሉት ነገሥታት፣  በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ወዳሉት ከነአናውያን፣+ ወደ አሞራውያን፣+ ወደ ሂታውያን፣ ወደ ፈሪዛውያን፣ በተራራማው አካባቢ ወደሚኖሩት ወደ ኢያቡሳውያን እንዲሁም በምጽጳ ምድር በሄርሞን+ ግርጌ ወደሚገኙት ወደ ሂዋውያን+ መልእክት ላከ።  እነሱም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ ከሆነው ሠራዊታቸው ሁሉ ጋር ወጡ፤ እጅግ ብዙ ፈረሶችና የጦር ሠረገሎችም ነበሯቸው።  እነዚህም ነገሥታት በሙሉ አንድ ላይ ለመገናኘት ተስማሙ፤ ከዚያም እስራኤልን ለመውጋት መጥተው በመሮም ውኃ አጠገብ አንድ ላይ ሰፈሩ።  በዚህ ጊዜ ይሖዋ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ነገ በዚህ ሰዓት ገደማ ሁሉንም ለእስራኤላውያን አሳልፌ ስለምሰጣቸው አትፍሯቸው፤+ እናንተም ትፈጇቸዋላችሁ። የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ቁረጡ፣+ ሠረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ።”  ከዚያም ኢያሱና አብረውት የነበሩት ተዋጊዎች በሙሉ በመሮም ውኃ አጠገብ ድንገተኛ ጥቃት ሰነዘሩባቸው።  ይሖዋም ለእስራኤላውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤+ እነሱም ድል አደረጓቸው፤ እስከ ታላቋ ሲዶና፣+ እስከ ሚስረፎትማይምና+ በስተ ምሥራቅ እስካለው እስከ ምጽጳ ሸለቆ ድረስም አሳደዷቸው፤ አንድም ሰው በሕይወት ሳያስቀሩ መቷቸው።+  ከዚያም ኢያሱ ልክ ይሖዋ እንደነገረው አደረገባቸው፤ የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ቆረጠ፤ ሠረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ።+ 10  ከዚህም በተጨማሪ ኢያሱ ተመልሶ ሃጾርን ተቆጣጠረ፤ ንጉሥዋንም በሰይፍ መትቶ ገደለው፤+ ምክንያቱም ሃጾር ቀደም ሲል የእነዚህ መንግሥታት ሁሉ የበላይ ነበረች። 11  እነሱም በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ በሰይፍ በመምታት ፈጽመው አጠፉ።+ እስትንፋስ ያለው አንድም ነገር አላስቀሩም።+ ከዚያም ሃጾርን በእሳት አቃጠላት። 12  ኢያሱ የእነዚህን ነገሥታት ከተሞች በሙሉ በቁጥጥር ሥር አዋለ፤ ነገሥታታቸውንም ሁሉ በሰይፍ ድል አደረገ።+ የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ባዘዘውም መሠረት ፈጽሞ አጠፋቸው።+ 13  ሆኖም እስራኤላውያን ኢያሱ ካቃጠላት ከሃጾር በስተቀር በኮረብቶቻቸው ላይ ካሉት ከተሞች አንዱንም አላቃጠሉም ነበር። 14  እስራኤላውያን ከእነዚህ ከተሞች ያገኙትን ምርኮና የቤት እንስሳ ሁሉ ለራሳቸው ወሰዱ።+ ሰዎቹን ግን አንድ በአንድ በሰይፍ መተው ሁሉንም አጠፏቸው።+ እስትንፋስ ያለው አንድም ሰው አላስቀሩም።+ 15  ይሖዋ አገልጋዩን ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ ሙሴም ኢያሱን አዞት ነበር፤+ ኢያሱም እንደተባለው አደረገ። ኢያሱ፣ ይሖዋ ሙሴን ካዘዘው ሁሉ ሳይፈጽም የቀረው አንድም ነገር አልነበረም።+ 16  ኢያሱ ይህን ምድር በሙሉ ይኸውም ተራራማውን አካባቢ፣ ኔጌብን+ በሙሉ፣ የጎሸንን ምድር ሁሉ፣ ሸፌላን፣+ አረባን፣+ የእስራኤልን ተራራማና ቆላማ አካባቢዎች በሙሉ ድል አደረገ፤ 17  ወደ ሴይር ሽቅብ ከሚወጣው ከሃላቅ ተራራ አንስቶ በሄርሞን ተራራ+ ግርጌ በሊባኖስ ሸለቆ እስከሚገኘው እስከ በዓልጋድ+ ድረስ ያለውን አካባቢ በሙሉ ድል አደረገ፤ ነገሥታታቸውን ሁሉ በቁጥጥር ሥር አዋለ፤ ድል አደረጋቸው፤ ገደላቸውም። 18  ኢያሱ ከእነዚህ ሁሉ ነገሥታት ጋር ለተወሰነ ጊዜ ተዋጋ። 19  በገባኦን ከሚኖሩት ሂዋውያን በስተቀር ከእስራኤላውያን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የፈጠረ አንድም ከተማ አልነበረም።+ ሌሎቹን ሁሉ በጦርነት ድል አደረጓቸው።+ 20  በእስራኤል ላይ ጦርነት እንዲከፍቱና ምንም ሳይራራላቸው ፈጽሞ ያጠፋቸው+ ዘንድ ልባቸው እንዲደነድን የፈቀደው ይሖዋ ነው።+ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሙሉ በሙሉ መጥፋት ነበረባቸው።+ 21  በዚያን ጊዜ ኢያሱ ከተራራማው አካባቢ ከኬብሮን፣ ከደቢር፣ ከአናብ እንዲሁም ከይሁዳ ተራራማ አካባቢዎች ሁሉና ከእስራኤል ተራራማ አካባቢዎች ሁሉ ኤናቃውያንን+ ጠራርጎ አጠፋ። ኢያሱ እነሱንም ሆነ ከተሞቻቸውን ሙሉ በሙሉ አጠፋቸው።+ 22  በእስራኤላውያን ምድር የተረፈ አንድም ኤናቃዊ አልነበረም፤ ኤናቃውያን የነበሩት በጋዛ፣+ በጌት+ እና በአሽዶድ+ ብቻ ነበር።+ 23  ስለዚህ ኢያሱ ይሖዋ ለሙሴ በገባው ቃል መሠረት ምድሩን ሁሉ ተቆጣጠረ፤+ ከዚያም ኢያሱ ለእስራኤላውያን በየነገዳቸው ድርሻቸውን ርስት አድርጎ ሰጣቸው።+ ምድሪቱም ከጦርነት አረፈች።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በአረባና።”
ወይም “ነፍስ።”