በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

ኢያሱ 10:1-43

የመጽሐፉ ይዘት

  • እስራኤላውያን ለገባኦናውያን ተዋጉላቸው (1-7)

  • ይሖዋ ለእስራኤል ተዋጋ (8-15)

    • እየሸሹ በነበሩት ጠላቶች ላይ የበረዶ ድንጋይ ወረደባቸው (11)

    • ፀሐይ ባለችበት ቆመች (12-14)

  • ጥቃት የሰነዘሩት አምስት ነገሥታት ተገደሉ (16-28)

  • በስተ ደቡብ ያሉት ከተሞች ተያዙ (29-43)

10  የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ፣ ኢያሱ ጋይን እንደተቆጣጠራትና እንደደመሰሳት፣ በኢያሪኮና በንጉሥዋ+ ላይ እንዳደረገው ሁሉ በጋይና በንጉሥዋም+ ላይ እንዳደረገ እንዲሁም የገባኦን ነዋሪዎች ከእስራኤላውያን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት+ ፈጥረው በመካከላቸው እየኖሩ እንዳሉ ሲሰማ  በጣም ደነገጠ፤+ ምክንያቱም ገባኦን በንጉሥ እንደሚተዳደሩት ከተሞች ሁሉ ታላቅ ከተማ ነበረች። ይህች ከተማ ከጋይ+ ትበልጥ የነበረ ሲሆን ነዋሪዎቿም በሙሉ ጦረኞች ነበሩ።  በመሆኑም የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ለኬብሮን+ ንጉሥ ለሆሐም፣ ለያርሙት ንጉሥ ለፒራም፣ ለለኪሶ ንጉሥ ለያፊአ እና ለኤግሎን ንጉሥ+ ለደቢር እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦  “መጥታችሁ እርዱኝና በገባኦን ላይ ጥቃት እንሰንዝር፤ ምክንያቱም ገባኦን ከኢያሱና ከእስራኤላውያን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ፈጥራለች።”+  በዚህ ጊዜ አምስቱ የአሞራውያን+ ነገሥታት ይኸውም የኢየሩሳሌም ንጉሥ፣ የኬብሮን ንጉሥ፣ የያርሙት ንጉሥ፣ የለኪሶ ንጉሥና የኤግሎን ንጉሥ ከነሠራዊታቸው አንድ ላይ ተሰብስበው በመዝመት ገባኦንን ለመውጋት ከበቧት።  የገባኦን ሰዎችም በጊልጋል+ በሚገኘው ሰፈር ወደነበረው ወደ ኢያሱ እንዲህ የሚል መልእክት ላኩበት፦ “እኛን ባሪያዎችህን አትተወን።+ ፈጥነህ ድረስልን! አድነን፤ እርዳን! በተራራማው አካባቢ የሚኖሩት የአሞራውያን ነገሥታት በሙሉ እኛን ለመውጋት ተሰብስበዋል።”  በመሆኑም ኢያሱ ተዋጊዎቹንና ኃያላን የሆኑትን ጦረኞች+ በሙሉ ይዞ ከጊልጋል ወጣ።  ከዚያም ይሖዋ ኢያሱን “በእጅህ አሳልፌ ስለሰጠኋቸው+ አትፍራቸው።+ አንዳቸውም እንኳ ሊቋቋሙህ አይችሉም”+ አለው።  ኢያሱም ከጊልጋል በመነሳት ሌሊቱን ሙሉ ሲገሰግስ አድሮ ድንገት መጣባቸው። 10  ይሖዋም በእስራኤላውያን ፊት ግራ እንዲጋቡ አደረጋቸው፤+ እነሱም ገባኦን ላይ ክፉኛ ጨፈጨፏቸው፤ ወደ ቤትሆሮን አቀበት በሚወስደው መንገድ ላይ በማሳደድ እስከ አዜቃ እና እስከ መቄዳ ድረስ መቷቸው። 11  እነሱም ከእስራኤላውያን በመሸሽ የቤትሆሮንን ቁልቁለት እየወረዱ ሳሉ እስከ አዜቃ ድረስ ይሖዋ ከሰማይ ትላልቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው፤ እነሱም ሞቱ። እንዲያውም በእስራኤላውያን ሰይፍ ከሞቱት ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት ይበልጣሉ። 12  ይሖዋ አሞራውያንን ከእስራኤላውያን ፊት ባባረረበት ዕለት ኢያሱ በእስራኤላውያን ፊት ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “ፀሐይ ሆይ፣ በገባኦን ላይ ቁሚ፤+ አንቺም ጨረቃ ሆይ፣ በአይሎን ሸለቆ* ላይ ቀጥ በይ!” 13  በመሆኑም ብሔሩ ጠላቶቹን እስኪበቀል ድረስ ፀሐይ ባለችበት ቆመች፤ ጨረቃም አልተንቀሳቀሰችም። ይህስ በያሻር መጽሐፍ+ ላይ ተጽፎ የሚገኝ አይደለም? ፀሐይ በሰማይ መካከል ባለችበት ቆመች፤ ለአንድ ቀን ያህል ለመጥለቅ አልቸኮለችም። 14  ይሖዋ የሰውን ቃል የሰማበት+ እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ ፈጽሞ አልነበረም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ለእስራኤል እየተዋጋ ነበር።+ 15  ከዚያ በኋላ ኢያሱና መላው እስራኤል በጊልጋል ወደሚገኘው ሰፈር+ ተመለሱ። 16  በዚህ ጊዜ አምስቱ ነገሥታት ሸሽተው በመቄዳ+ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ተደብቀው ነበር። 17  ከዚያም ኢያሱ “አምስቱ ነገሥታት በመቄዳ+ በሚገኘው ዋሻ ውስጥ ተደብቀው ተገኝተዋል” የሚል መልእክት ደረሰው። 18  እሱም እንዲህ አለ፦ “ትላልቅ ድንጋዮች አንከባላችሁ የዋሻውን አፍ ግጠሙትና እነሱን የሚጠብቁ ሰዎች መድቡ። 19  የተቀራችሁት ግን ዝም ብላችሁ አትቁሙ። ጠላቶቻችሁን እያሳደዳችሁ ከኋላ ምቷቸው።+ አምላካችሁ ይሖዋ በእጃችሁ አሳልፎ ስለሰጣቸው ወደ ከተሞቻቸው እንዲገቡ አትፍቀዱላቸው።” 20  ኢያሱና እስራኤላውያን፣ አምልጠው ወደተመሸጉት ከተሞች ከገቡት ጥቂት ሰዎች በቀር ጠላቶቻቸውን እስኪጠፉ ድረስ ክፉኛ ከጨፈጨፏቸው በኋላ 21  ሕዝቡ ሁሉ በመቄዳ በሚገኘው ሰፈር ወደነበረው ወደ ኢያሱ በሰላም ተመለሰ። በእስራኤላውያን ላይ አንዲት ቃል ሊናገር የደፈረ* ሰው አልነበረም። 22  ከዚያም ኢያሱ “የዋሻውን አፍ ከፍታችሁ አምስቱን ነገሥታት ከዋሻው አውጥታችሁ ወደ እኔ አምጧቸው” አለ። 23  ስለሆነም እነዚህን አምስት ነገሥታት ማለትም የኢየሩሳሌምን ንጉሥ፣ የኬብሮንን ንጉሥ፣ የያርሙትን ንጉሥ፣ የለኪሶን ንጉሥና የኤግሎንን ንጉሥ ከዋሻው አውጥተው ወደ እሱ አመጧቸው።+ 24  ኢያሱም እነዚህን ነገሥታት ወደ እሱ ባመጧቸው ጊዜ የእስራኤልን ሰዎች በሙሉ ጠርቶ አብረውት የሄዱትን የሠራዊቱን አዛዦች “ወደዚህ ቅረቡ። እግራችሁን በእነዚህ ነገሥታት ማጅራት ላይ አድርጉ” አላቸው። እነሱም ቀርበው እግራቸውን በማጅራታቸው ላይ አደረጉ።+ 25  ከዚያም ኢያሱ እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ ወይም አትሸበሩ።+ ይሖዋ በምትዋጓቸው ጠላቶቻችሁ ሁሉ ላይ እንዲህ ስለሚያደርግ ደፋርና ብርቱ ሁኑ።”+ 26  ከዚያም ኢያሱ መትቶ ገደላቸው፤ በአምስት እንጨቶችም* ላይ ሰቀላቸው፤ በእንጨቶቹም ላይ እንደተሰቀሉ እስከ ምሽት ድረስ ቆዩ። 27  ፀሐይም ልትጠልቅ ስትቃረብ ኢያሱ፣ አስከሬኖቻቸው ከእንጨቶቹ ላይ እንዲወርዱና+ ተደብቀውበት በነበረው ዋሻ ውስጥ እንዲጣሉ ትእዛዝ ሰጠ። ከዚያም በዋሻው አፍ ላይ ትላልቅ ድንጋዮችን አደረጉ፤ እነዚህም እስከ ዛሬ ድረስ እዚያው ይገኛሉ። 28  ኢያሱም በዚያን ዕለት መቄዳን+ በመቆጣጠር ሕዝቡን በሰይፍ ፈጀ። ንጉሥዋንና በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ አንድም ሳያስቀር ፈጽሞ አጠፋ።+ በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ እንዳደረገውም ሁሉ በመቄዳ ንጉሥ+ ላይ አደረገ። 29  ከዚያም ኢያሱና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከመቄዳ ወደ ሊብና በመሄድ ሊብናን+ ወጓት። 30  ይሖዋም ከተማዋንና ንጉሥዋን+ በእስራኤላውያን እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነሱም ከተማዋንና በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ አንድም ሳያስቀሩ በሰይፍ መቱ። በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ እንዳደረጉትም ሁሉ በንጉሥዋ ላይ አደረጉ።+ 31  በመቀጠልም ኢያሱና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከሊብና ወደ ለኪሶ+ ሄዱ፤ እሷንም ከበው ወጓት። 32  ይሖዋም ለኪሶን ለእስራኤላውያን አሳልፎ ሰጣት፤ እነሱም በሁለተኛው ቀን ያዟት። በሊብና ላይ እንዳደረጉትም ሁሉ ከተማዋንና በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ በሰይፍ መቱ።+ 33  በዚህ ጊዜ የጌዜር+ ንጉሥ ሆራም ለኪሶን ለመርዳት ወጣ፤ ሆኖም ኢያሱ እሱንና ሕዝቡን አንድም ሳያስቀር መታቸው። 34  በመቀጠልም ኢያሱና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከለኪሶ ወደ ኤግሎን+ በመሄድ ከበው ወጓት። 35  እነሱም በዚያን ቀን ከተማዋን በመቆጣጠር በሰይፍ መቷት። በለኪሶ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ በዚያኑ ዕለት ሙሉ በሙሉ አጠፉ።+ 36  ከዚያም ኢያሱና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ከኤግሎን ወደ ኬብሮን+ በመውጣት ኬብሮንን ወጓት። 37  እሷንም ተቆጣጥረው ከተማዋን፣ ንጉሥዋንና በዙሪያዋ ያሉትን አነስተኛ ከተሞች እንዲሁም በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ አንድም ሳያስቀሩ በሰይፍ መቱ። በኤግሎንም ላይ እንዳደረገው ሁሉ ከተማዋንና በውስጧ ያለውን ሰው* ሁሉ ሙሉ በሙሉ አጠፋ። 38  በመጨረሻም ኢያሱና ከእሱ ጋር የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ደቢር+ በመዞር ወጓት። 39  ከተማዋን፣ ንጉሥዋንና በዙሪያዋ ያሉትን አነስተኛ ከተሞች ተቆጣጠረ፤ እነሱንም በሰይፍ መቷቸው፤ በውስጧ ያለውንም ሰው* ሁሉ አንድም ሳያስቀሩ+ ፈጽመው አጠፉ።+ በኬብሮን እንዲሁም በሊብና እና በንጉሥዋ ላይ እንዳደረገው ሁሉ በደቢርና በንጉሥዋ ላይ አደረገ። 40  ኢያሱም ምድሩን ሁሉ ይኸውም ተራራማውን አካባቢ፣ ኔጌብን፣ ሸፌላን፣+ ሸንተረሮቹንና ነገሥታታቸውን በሙሉ ድል አደረገ፤ አንድም ሰው አላስቀረም፤ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ባዘዘውም መሠረት+ እስትንፋስ ያለውን ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ።+ 41  ኢያሱ ከቃዴስበርኔ+ አንስቶ እስከ ጋዛ+ ድረስ እንዲሁም የጎሸንን+ ምድር በሙሉ እስከ ገባኦን+ ድረስ ድል አደረገ። 42  ኢያሱ እነዚህን ሁሉ ነገሥታትና ምድራቸውን በሙሉ በአንድ ጊዜ ተቆጣጠረ፤ ምክንያቱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ለእስራኤላውያን እየተዋጋላቸው ነበር።+ 43  ከዚያም ኢያሱና እስራኤላውያን በሙሉ በጊልጋል+ ወደሚገኘው ሰፈር ተመለሱ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ቃል በቃል “ምላሱን ያሾለ።”
ወይም “ዛፎችም።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”