በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

ቆላስይስ 1:1-29

የመጽሐፉ ይዘት

  • ሰላምታ (1, 2)

  • የቆላስይስ ክርስቲያኖች ላሳዩት እምነት የቀረበ ምስጋና (3-8)

  • መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የቀረበ ጸሎት (9-12)

  • ክርስቶስ የሚጫወተው ወሳኝ ሚና (13-23)

  • ጳውሎስ ጉባኤውን በትጋት አገልግሏል (24-29)

1  በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፣+  በቆላስይስ ለሚገኙ ከክርስቶስ ጋር አንድነት ላላቸው ታማኝ የሆኑ ቅዱሳን ወንድሞች፦ አባታችን ከሆነው አምላክ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።  ስለ እናንተ ስንጸልይ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነውን አምላክ ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤  ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳን ሁሉ ስለምታሳዩት ፍቅር ሰምተናል፤  ይህም የሆነው በሰማይ ከሚጠብቃችሁ ተስፋ የተነሳ ነው።+ ይህን ተስፋ በተመለከተ ቀደም ሲል የሰማችሁት፣ በተነገራችሁ የእውነት መልእክት ይኸውም በምሥራቹ አማካኝነት ሲሆን  ይህም ምሥራች ወደ እናንተ ደርሷል። ምሥራቹ በመላው ዓለም እየተስፋፋና ፍሬ እያፈራ+ እንደሆነ ሁሉ የአምላክን ጸጋ እውነት ከሰማችሁበትና በትክክል ካወቃችሁበት ቀን አንስቶ በእናንተም መካከል እያደገና ፍሬ እያፈራ ነው።  የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ በእኛ ምትክ ከሚሠራውና አብሮን ባሪያ ከሆነው ከተወዳጁ ኤጳፍራ+ የተማራችሁት ይህን ነው።  ደግሞም ስለ መንፈሳዊ ፍቅራችሁ ነግሮናል።  ከዚህም የተነሳ ይህን ከሰማንበት ቀን አንስቶ ከጥበብና ከመንፈሳዊ ግንዛቤ+ ሁሉ ጋር በፈቃዱ ትክክለኛ እውቀት+ ትሞሉ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለያችንንና መለመናችንን አላቋረጥንም፤+ 10  ይህም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁና ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም+ እያደጋችሁ ስትሄዱ ለይሖዋ* በሚገባ ሁኔታ እንድትመላለሱና እሱን ሙሉ በሙሉ እንድታስደስቱ ነው፤ 11  በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት እንድትቋቋሙ የአምላክ ታላቅ ኃይል የሚያስፈልጋችሁን ብርታት ሁሉ ይስጣችሁ፤+ 12  ደግሞም በብርሃን ውስጥ ያሉት ቅዱሳን ከሚያገኙት ውርሻ+ ለመካፈል ያበቃችሁን አባት አመስግኑ። 13  እሱ ከጨለማው ሥልጣን ታድጎን+ ወደሚወደው ልጁ መንግሥት አሻግሮናል፤ 14  ልጁም ቤዛውን በመክፈል ነፃ እንድንወጣ ይኸውም የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝ አድርጎናል።+ 15  እሱ የማይታየው አምላክ አምሳልና+ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው፤+ 16  ምክንያቱም በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ፣ የሚታዩትና የማይታዩት ነገሮች፣ ዙፋኖችም ሆኑ ጌትነት፣ መንግሥታትም ሆኑ ሥልጣናት የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት ነው።+ ሌሎች ነገሮች በሙሉ የተፈጠሩት በእሱ በኩልና+ ለእሱ ነው። 17  በተጨማሪም እሱ ከሌሎች ነገሮች ሁሉ በፊት ነው፤+ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ወደ ሕልውና የመጡትም በእሱ አማካኝነት ነው፤ 18  እሱ የአካሉ ማለትም የጉባኤው ራስ ነው።+ በሁሉም ነገር ቀዳሚ መሆን እንዲችልም እሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኩር ነው፤+ 19  ይህም የሆነው እሱ በሁሉም ነገር ሙሉ እንዲሆን አምላክ ስለፈለገ ነው፤+ 20  እንዲሁም በመከራው እንጨት* ላይ ባፈሰሰው ደም+ አማካኝነት ሰላም በመፍጠር ሌሎቹን ነገሮች ሁሉ ይኸውም በምድርም ሆነ በሰማያት ያሉትን ነገሮች ሁሉ በእሱ በኩል ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ስለወደደ ነው።+ 21  በእርግጥ እናንተ በአንድ ወቅት አእምሯችሁ በክፉ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ስለነበር ከአምላክ የራቃችሁና ጠላቶች ነበራችሁ፤ 22  አሁን ግን እሱ ቅዱሳንና እንከን የሌለባችሁ እንዲሁም ከማንኛውም ክስ ነፃ የሆናችሁ አድርጎ በፊቱ ሊያቀርባችሁ ስለፈለገ+ ራሱን ለሞት አሳልፎ በሰጠው ሰው ሥጋዊ አካል አማካኝነት ከራሱ ጋር አስታርቋችኋል፤ 23  በእርግጥ ይህ የሚሆነው በእምነት መሠረት ላይ ታንጻችሁና+ ተደላድላችሁ በመቆም፣+ የሰማችሁት ምሥራች ካስገኘላችሁ ተስፋ ሳትወሰዱ በእምነት ጸንታችሁ ስትኖሩ ነው፤+ ይህም ምሥራች ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ* ተሰብኳል።+ እኔም ጳውሎስ የዚህ ምሥራች አገልጋይ ሆኛለሁ።+ 24  ለእናንተ ስል በተቀበልኩት መከራ+ አሁን እየተደሰትኩ ነው፤ በክርስቶስ የተነሳ በአካሌ ላይ የሚደርሰው መከራ በዚህ ብቻ አያበቃም። ይህ መከራ እየደረሰብኝ ያለው ለአካሉ+ ይኸውም ለጉባኤው+ ስል ነው። 25  የአምላክን ቃል በተሟላ ሁኔታ እሰብክ ዘንድ ለእናንተ ጥቅም ሲባል ከአምላክ ከተሰጠኝ የመጋቢነት ሥራ+ ጋር በሚስማማ መንገድ የዚህ ጉባኤ አገልጋይ ሆኛለሁ፤ 26  ይህም ቃል ካለፉት ሥርዓቶችና* ካለፉት ትውልዶች አንስቶ ተሰውሮ+ የቆየው ቅዱስ ሚስጥር+ ነው። አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጧል።+ 27  በተጨማሪም አምላክ በአሕዛብ መካከል የዚህን ቅዱስ ሚስጥር ታላቅ ብልጽግና ለቅዱሳኑ ያሳውቅ ዘንድ ወዷል፤+ ይህ ቅዱስ ሚስጥር የክብሩ ተስፋ+ የሆነውና ከእናንተ ጋር አንድነት ያለው ክርስቶስ ነው። 28  እያንዳንዱን ሰው የጎለመሰ* የክርስቶስ ደቀ መዝሙር አድርገን ለአምላክ ማቅረብ እንድንችል ሰውን ሁሉ እያሳሰብንና በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምናውጀው ስለ እሱ ነው።+ 29  ይህን ዳር ለማድረስ፣ በውስጤ እየሠራ ባለው በእሱ ብርቱ ኃይል አማካኝነት አቅሜ በሚፈቅደው ሁሉ በትጋት እየሠራሁ ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ መካከል።”
ወይም “ካለፉት ዘመናትና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ፍጹም።”