በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

መሳፍንት 21:1-25

የመጽሐፉ ይዘት

  • የቢንያም ነገድ ከመጥፋት ተረፈ (1-25)

21  የእስራኤል ሰዎች በምጽጳ+ ተሰብስበው “ከእኛ መካከል ማንም ሰው ሴት ልጁን ከቢንያም ወገን ለሆነ ሰው መዳር የለበትም” በማለት ተማምለው ነበር።+  በመሆኑም እስራኤላውያን ወደ ቤቴል+ መጥተው በዚያ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አምርረው እያለቀሱ በእውነተኛው አምላክ ፊት እስከ ምሽት ድረስ ተቀመጡ።  እነሱም “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር እንዲከሰት ለምን ፈቀድክ? ዛሬ ከእስራኤል መካከል አንድ ነገድ እንዴት ይጥፋ?” ይሉ ነበር።  በማግስቱም ሕዝቡ በማለዳ ተነስቶ የሚቃጠሉ መባዎችንና የኅብረት መባዎችን+ ለማቅረብ በዚያ መሠዊያ ሠራ።  የእስራኤል ሰዎችም በምጽጳ በይሖዋ ፊት ያልተገኘ ሰው ሁሉ ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት በማለት በጥብቅ ተማምለው ስለነበር “ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል በይሖዋ ፊት ለመሰብሰብ ያልወጣው ማን ነው?” በማለት ጠየቁ።  የእስራኤል ሰዎችም በወንድማቸው በቢንያም ላይ በደረሰው ነገር አዘኑ። እንዲህም አሉ፦ “እነሆ ዛሬ ከእስራኤል መካከል አንድ ነገድ ተቆርጧል።  እንግዲህ እኛ ሴት ልጆቻችንን ለእነሱ ላለመዳር በይሖዋ ምለናል፤+ ታዲያ የተረፉት ወንዶች ሚስት ማግኘት እንዲችሉ ምን ብናደርግ ይሻላል?”+  እነሱም “ከእስራኤል ነገዶች መካከል በምጽጳ በይሖዋ ፊት ለመቅረብ ያልወጣው የትኛው ነው?”+ በማለት ጠየቁ። ከኢያቢስጊልያድ ጉባኤው ወደነበረበት ሰፈር የመጣ ማንም ሰው አልነበረም።  ሕዝቡ በተቆጠረበት ጊዜ ከኢያቢስጊልያድ ነዋሪዎች መካከል አንድም ሰው እንዳልነበር ተገነዘቡ። 10  በመሆኑም ማኅበረሰቡ እጅግ ኃያል ከሆኑት ተዋጊዎች መካከል 12,000 ሰዎችን ወደዚያ ላከ። እንዲህም ሲሉ አዘዟቸው፦ “ሂዱ፤ የኢያቢስጊልያድን ነዋሪዎች በሰይፍ ምቱ፤ ሴቶችንና ልጆችንም እንኳ አታስቀሩ።+ 11  እንግዲህ እንዲህ አድርጉ፦ እያንዳንዱን ወንድ እንዲሁም ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የሚያውቁ ሴቶችን ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ።” 12  እነሱም ከኢያቢስጊልያድ ነዋሪዎች መካከል ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የማያውቁ 400 ደናግል ሴቶችን አገኙ። እነሱንም በከነአን ምድር በሴሎ+ ወደሚገኘው ሰፈር አመጧቸው። 13  ከዚያም መላው ማኅበረሰብ በሪሞን በሚገኘው ዓለት+ ወዳሉት ቢንያማውያን መልእክት በመላክ የሰላም ጥሪ አቀረበላቸው። 14  በመሆኑም በዚህ ጊዜ ቢንያማውያን ወደ ምድራቸው ተመለሱ። ከኢያቢስጊልያድ ሴቶች መካከል በሕይወት እንዲተርፉ የተዉአቸውንም ሴቶች ሰጧቸው፤+ ሆኖም በቂ ሴቶች አላገኙላቸውም። 15  ሕዝቡም ይሖዋ በእስራኤል ነገዶች መካከል ክፍፍል እንዲኖር በማድረጉ የተነሳ በቢንያማውያን ላይ በደረሰው ነገር አዘነ።+ 16  የማኅበረሰቡም ሽማግሌዎች “ቢንያማውያን ሴቶች በሙሉ ስላለቁ ለተረፉት ወንዶች ሚስት ለማግኘት ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሉ። 17  እነሱም እንዲህ በማለት መለሱ፦ “ከእስራኤል መካከል አንድ ነገድ ሙሉ በሙሉ እንዳይጠፋ በሕይወት ለተረፉት ቢንያማውያን ርስት ሊኖራቸው ይገባል። 18  ሆኖም እኛ ሴቶች ልጆቻችንን ለእነሱ መዳር አይፈቀድልንም፤ ምክንያቱም የእስራኤል ሰዎች ‘ለቢንያም ልጁን የሚድር የተረገመ ነው’ ብለው ምለዋል።”+ 19  ከዚያም “ከቤቴል በስተ ሰሜንና ከቤቴል ወደ ሴኬም ከሚወስደው አውራ ጎዳና በስተ ምሥራቅ እንዲሁም ከለቦና በስተ ደቡብ በምትገኘው በሴሎ+ በየዓመቱ ለይሖዋ የሚከበር በዓል አለ” አሉ። 20  በመሆኑም የቢንያምን ሰዎች እንዲህ በማለት አዘዟቸው፦ “ሂዱና በወይን እርሻው ውስጥ አድፍጣችሁ ጠብቁ። 21  የሴሎ ወጣት ሴቶች ክብ ሠርተው ለመጨፈር ሲወጡ ስታዩ እያንዳንዳችሁ ከወይን እርሻው ውስጥ ወጥታችሁ ከሴሎ ወጣት ሴቶች መካከል ለራሳችሁ ሚስት ጠልፋችሁ ውሰዱ፤ ከዚያም ወደ ቢንያም ምድር ተመለሱ። 22  አባቶቻቸው ወይም ወንድሞቻቸው መጥተው በእኛ ላይ ስሞታ ቢያሰሙ እንዲህ እንላቸዋለን፦ ‘ባደረግነው ጦርነት ለእያንዳንዳቸው የሚሆኑ ሚስቶችን ማግኘት ስላልቻልን ለእነሱ ስትሉ ውለታ ዋሉልን፤+ እናንተም ብትሆኑ ሴቶቹን ፈቅዳችሁ ስላልሰጣችኋቸው በጥፋተኝነት አትጠየቁም።’”+ 23  በመሆኑም የቢንያም ሰዎች እንደተባሉት አደረጉ፤ እያንዳንዳቸውም ከሚጨፍሩት ሴቶች መካከል ሚስቶችን ጠልፈው ወሰዱ። ከዚያም ወደየርስታቸው ተመልሰው በመሄድ ከተሞቻቸውን በድጋሚ ገንብተው+ በዚያ መኖር ጀመሩ። 24  በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን እያንዳንዳቸው ወደየነገዳቸውና ወደየቤተሰባቸው በመሄድ ከዚያ አካባቢ ተበተኑ፤ እያንዳንዳቸውም ከዚያ ተነስተው ወደየርስታቸው ሄዱ። 25  በዚያ ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም።+ እያንዳንዱም ሰው ለራሱ ትክክል መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች