በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

ሕዝቅኤል 43:1-27

የመጽሐፉ ይዘት

  • የይሖዋ ክብር ቤተ መቅደሱን ሞላው (1-12)

  • መሠዊያው (13-27)

43  ከዚያም ከምሥራቅ ትይዩ ወደሆነው በር ወሰደኝ።+  በዚያም የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ ሲመጣ አየሁ፤+ ድምፁም እንደሚጎርፍ ውኃ ድምፅ ነበር፤+ ከክብሩም የተነሳ ምድር አበራች።+  ያየሁት ነገር ከተማዋን ለማጥፋት* በመጣሁ* ጊዜ ያየሁትን ራእይ ይመስል ነበር፤ ደግሞም በኬባር ወንዝ+ አቅራቢያ አይቼው ከነበረው ነገር ጋር ይመሳሰል ነበር፤ እኔም መሬት ላይ በግንባሬ ተደፋሁ።  ከዚያም የይሖዋ ክብር ከምሥራቅ ትይዩ በሆነው በር በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ* ገባ።+  መንፈስም አንስቶ ወደ ውስጠኛው ግቢ አመጣኝ፤ እኔም ቤተ መቅደሱ በይሖዋ ክብር ተሞልቶ አየሁ።+  ከዚያም አንድ ሰው ከቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲያናግረኝ ሰማሁ፤ ሰውየውም መጥቶ አጠገቤ ቆመ።+  አምላክም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፣ ይህ የዙፋኔ መቀመጫ፣+ የእግሬ ማሳረፊያና+ በእስራኤል ልጆች መካከል ለዘላለም የምኖርበት ስፍራ ነው።+ የእስራኤል ቤት ሰዎች፣ እነሱም ሆኑ ንጉሦቻቸው በሚፈጽሙት መንፈሳዊ ምንዝርና በሞቱት ንጉሦቻቸው* ሬሳ ከእንግዲህ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም።+  በእኔና በእነሱ መካከል ግንቡ ብቻ ሲቀር፣ ደፋቸውን ከቤቴ ደፍ አጠገብ፣ መቃናቸውንም ከቤቴ መቃን አጠገብ በማድረግ+ በሠሯቸው አስጸያፊ ነገሮች ቅዱስ ስሜን አርክሰዋል፤ ስለዚህ በቁጣዬ አጠፋኋቸው።+  ከእንግዲህ የሚፈጽሙትን መንፈሳዊ ምንዝር ያስወግዱ፤ የንጉሦቻቸውንም ሬሳ ከእኔ ያርቁ፤ እኔም በመካከላቸው ለዘላለም እኖራለሁ።+ 10  “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ ከሠሩት በደል የተነሳ ኀፍረት እንዲሰማቸው+ ለእስራኤል ቤት ሰዎች ስለ ቤተ መቅደሱ ግለጽላቸው፤+ ንድፉንም ያጥኑ።* 11  በሠሩት ነገር ሁሉ ኀፍረት ከተሰማቸው የቤተ መቅደሱን ንድፍ፣ አቀማመጡን፣ መውጫዎቹንና መግቢያዎቹን አሳውቃቸው።+ አጠቃላይ ንድፉንና ደንቦቹን፣ ንድፉንና ሕጎቹን አሳያቸው፤ ደግሞም እነሱ እያዩ ጻፋቸው፤ ይህን የምታደርገው አጠቃላይ ንድፉንና ደንቦቹን አስተውለው በተግባር እንዲያውሉ ነው።+ 12  የቤተ መቅደሱ ሕግ ይህ ነው። በተራራው አናት ዙሪያ ያለው ቦታ ሁሉ እጅግ ቅዱስ ነው።+ እነሆ፣ የቤተ መቅደሱ ሕግ ይህ ነው። 13  “የመሠዊያው ልክ በክንድ* ሲለካ መጠኑ ይህ ነው፤+ እያንዳንዱ ክንድ አንድ ጋት ተጨምሮበት ነበር። የመሠዊያው መሠረት አንድ ክንድ ነው፤ ወርዱም አንድ ክንድ ነው። በጠርዙ ዙሪያ፣ ወርዱ አንድ ስንዝር* የሆነ ክፈፍ አለው። ይህ የመሠዊያው መሠረት ነው። 14  መሬት ላይ ካረፈው መሠረት አንስቶ በዙሪያው እስካለው የታችኛው እርከን ድረስ ሁለት ክንድ ሲሆን ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ ነው። በዙሪያው ካለው ከትንሹ እርከን እስከ ትልቁ እርከን ድረስ አራት ክንድ፣ ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ ነው። 15  የመሠዊያው ምድጃ ከፍታ አራት ክንድ ሲሆን ከምድጃው በላይ ወጣ ወጣ ያሉ አራት ቀንዶች አሉ።+ 16  የመሠዊያው ምድጃ አራት ማዕዘን ሲሆን ርዝመቱ 12 ክንድ፣ ወርዱም 12 ክንድ ነው።+ 17  በዙሪያው ያለው እርከን አራቱም ጎኖች ርዝመታቸው 14 ክንድ፣ ወርዳቸውም 14 ክንድ ነው፤ በዙሪያውም ያለው ክፈፍ ግማሽ ክንድ ሲሆን መሠረቱም በሁሉም ጎኖች አንድ ክንድ ነው። “ደረጃዎቹም ከምሥራቅ ትይዩ ነበሩ።” 18  ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፣ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በመሠዊያው ላይ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ እንዲቀርብና በላዩ ላይ ደም እንዲረጭበት፣ መሠዊያው ሲሠራ ሊከተሏቸው የሚገቡት መመሪያዎች እነዚህ ናቸው።’+ 19  “‘እኔን ለማገልገል በፊቴ ለሚቀርቡት የሳዶቅ ዘር ለሆኑት ሌዋውያን ካህናት፣+ ከመንጋው መካከል ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ ወይፈን ትሰጣቸዋለህ’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። 20  ‘ከደሙ ጥቂት ወስደህ በመሠዊያው አራት ቀንዶች፣ በዙሪያው ባለው እርከን አራት ጎኖችና በዙሪያው ባለው ጠርዝ ላይ አድርግ፤ ይህን የምታደርገው መሠዊያውን ከኃጢአት ለማንጻትና ለመሠዊያው ማስተሰረያ ለማቅረብ ነው።+ 21  ከዚያም ከመቅደሱ ውጭ፣ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለዚህ ተብሎ በተመደበው ቦታ ታቃጥለው ዘንድ የኃጢአት መባ የሆነውን ወይፈን ውሰድ።+ 22  በሁለተኛው ቀን የኃጢአት መባ የሚሆን እንከን የሌለበት ተባዕት ፍየል ታቀርባለህ፤ እነሱም በወይፈኑ መሠዊያውን ከኃጢአት እንዳነጹት ሁሉ በዚህም መሠዊያውን ከኃጢአት ያነጹታል።’ 23  “‘መሠዊያውን ከኃጢአት ካነጻህ በኋላ ከከብቶቹ መካከል እንከን የሌለበት አንድ ወይፈንና ከመንጋው መካከል እንከን የሌለበት አንድ አውራ በግ ታቀርባለህ። 24  ለይሖዋ ታቀርባቸዋለህ፤ ካህናቱም ጨው ከነሰነሱባቸው+ በኋላ ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ አድርገው ያቀርቧቸዋል። 25  በየዕለቱ፣ ለሰባት ቀናት አንድ አውራ ፍየል የኃጢአት መባ አድርገህ ታቀርባለህ፤+ እንዲሁም ከከብቶቹ መካከል አንድ ወይፈንና ከመንጋው መካከል አንድ አውራ በግ ታቀርባለህ፤ የምታቀርባቸው እንስሳት እንከን የሌለባቸው* ይሁኑ። 26  ለሰባት ቀናት ለመሠዊያው ማስተሰረያ ያቀርባሉ፤ መሠዊያውንም ያነጹታል እንዲሁም ለአገልግሎት ያዘጋጁታል። 27  እነዚህ ቀናት ከተፈጸሙ በኋላ ከስምንተኛው ቀን+ አንስቶ ካህናቱ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባችሁንና* የኅብረት መሥዋዕቶቻችሁን በመሠዊያው ላይ ያቀርባሉ፤ እኔም በእናንተ ደስ እሰኛለሁ’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

እንዲህ ያደረገው ስለ ከተማዋ ጥፋት ትንቢት በመናገር ነው።
“በመጣ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ቤቱ።”
ንጉሦቻቸው አድርገው የሚመለከቷቸውን ጣዖቶች የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
ቃል በቃል “ንድፉን ይለኩ።”
ይህ ረጅም ክንድ የሚባለውን መለኪያ ያመለክታል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ስንዝር 22.2 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ፍጹም።”
ሕዝቡ የሚያቀርበውን ማለት ነው።