በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ሐጌ 1:1-15

የመጽሐፉ ይዘት

  • ቤተ መቅደሱን መልሰው ባለመገንባታቸው ተወቀሱ (1-11)

    • ‘በእንጨት በተለበጡ ቤቶቻችሁ የምትኖሩበት ጊዜ ነው?’ (4)

    • “መንገዳችሁን ልብ በሉ” (5)

    • ‘ብዙ ዘራችሁ፤ የምትሰበስቡት ግን ጥቂት ነው’ (6)

  • ሕዝቡ የይሖዋን ድምፅ ሰማ (12-15)

1  ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በስድስተኛው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የይሖዋ ቃል በነቢዩ ሐጌ*+ በኩል የይሁዳ ገዢ ወደሆነው ወደ ሰላትያል ልጅ ወደ ዘሩባቤልና+ ሊቀ ካህናት ወደሆነው ወደ የሆጼዴቅ ልጅ ወደ ኢያሱ እንዲህ ሲል መጣ፦  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነዚህ ሰዎች “የይሖዋ ቤት* የሚገነባበት* ጊዜ ገና አልደረሰም” ይላሉ።’”+  የይሖዋም ቃል በነቢዩ ሐጌ+ በኩል እንዲህ ሲል በድጋሚ መጣ፦  “ይህ ቤት ፈርሶ እያለ፣ እናንተ በሚያምር እንጨት በተለበጡ ቤቶቻችሁ ውስጥ የምትኖሩበት ጊዜ ነው?+  አሁንም የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘መንገዳችሁን ልብ በሉ።*  ብዙ ዘር ዘራችሁ፤ የምትሰበስቡት ግን ጥቂት ነው።+ ትበላላችሁ፤ ሆኖም አትጠግቡም። ትጠጣላችሁ፤ ሆኖም አትረኩም። ትለብሳላችሁ፤ የሚሞቀው ሰው ግን የለም። ተቀጥሮ የሚሠራው ደሞዙን ብዙ ቀዳዳዎች ባሉት ከረጢት ውስጥ ያስቀምጣል።’”  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘መንገዳችሁን ልብ በሉ።’*  “‘ወደ ተራራው ወጥታችሁ ጥርብ እንጨት አምጡ።+ እኔ ደስ እንድሰኝበትና እንድከበርበት+ ቤቱን ሥሩ’+ ይላል ይሖዋ።”  “‘ብዙ ነገር ጠበቃችሁ፤ ሆኖም ያገኛችሁት ጥቂት ነው፤ ወደ ቤት ባመጣችሁትም ጊዜ እፍ ብዬ በተንኩት።+ ይህ የሆነው ለምንድን ነው?’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። ‘የእኔ ቤት ፈርሶ እያለ እያንዳንዳችሁ የገዛ ቤታችሁን ለማሳመር ስለምትሯሯጡ ነው።+ 10  ስለዚህ ከእናንተ በላይ ያሉት ሰማያት ጠል ማዝነባቸውን አቆሙ፤ ምድርም ፍሬዋን አልሰጥ አለች። 11  እኔም በምድር ላይ፣ በተራሮች ላይ፣ በእህሉ ላይ፣ በአዲሱ የወይን ጠጅ ላይ፣ በዘይቱ ላይ፣ ምድሪቱ በምታበቅለው ነገር ላይ፣ በሰዎች ላይ፣ በመንጎች ላይ እንዲሁም እጆቻችሁ በደከሙበት ነገር ሁሉ ላይ ድርቅን ጠራሁ።’” 12  የሰላትያል+ ልጅ ዘሩባቤል፣+ የየሆጼዴቅ+ ልጅ ሊቀ ካህናቱ ኢያሱና የቀረው ሕዝብ በሙሉ የአምላካቸውን የይሖዋን ድምፅ እንዲሁም ነቢዩ ሐጌ የተናገረውን ቃል ሰሙ፤ አምላካቸው ይሖዋ ልኮታልና፤ ሕዝቡም ከይሖዋ የተነሳ ፈሩ። 13  ከዚያም የይሖዋ መልእክተኛ የሆነው ሐጌ ከይሖዋ በተሰጠው ተልእኮ መሠረት ለሕዝቡ “‘እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ’+ ይላል ይሖዋ” የሚል መልእክት ተናገረ። 14  ስለዚህ ይሖዋ የይሁዳን ገዢ+ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፣ የሊቀ ካህናቱን የየሆጼዴቅን ልጅ የኢያሱን+ መንፈስ እንዲሁም የቀረውን ሕዝብ መንፈስ በሙሉ አነሳሳ፤+ እነሱም መጥተው የአምላካቸውን የሠራዊት ጌታ የይሖዋን ቤት መሥራት ጀመሩ።+ 15  ይህ የሆነው ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በስድስተኛው ወር፣ ከወሩም በ24ኛው ቀን ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“በበዓል ቀን የተወለደ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ወይም “ዳግመኛ የሚገነባበት።”
ወይም “በጥሞና አስቡበት።”
ወይም “በጥሞና አስቡበት።”