በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

የሉቃስ ወንጌል 14:1-35

የመጽሐፉ ይዘት

  • ሰውነት የሚያሳብጥ በሽታ የያዘው ሰው በሰንበት ተፈወሰ (1-6)

  • ‘ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ይደረጋል’ (7-11)

  • ብድር ሊመልሱላችሁ የማይችሉትን ጋብዙ (12-14)

  • ሰበብ ያቀረቡት ተጋባዦች ምሳሌ (15-24)

  • ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከፍለው ዋጋ (25-33)

  • ጣዕሙን ያጣ ጨው (34, 35)

14  በሌላ ወቅት ኢየሱስ በአንድ የሰንበት ቀን ከፈሪሳውያን መሪዎች ወደ አንዱ ቤት ምግብ ሊበላ በገባ ጊዜ በቤቱ ውስጥ ያሉት ሰዎች በትኩረት ይከታተሉት ነበር።  በዚያም ሰውነት የሚያሳብጥ በሽታ* የያዘው አንድ ሰው ከፊት ለፊቱ ነበር።  ኢየሱስም ሕግ አዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን “በሰንበት መፈወስ በሕግ ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?” ሲል ጠየቃቸው።+  እነሱ ግን ዝም አሉ። በዚህ ጊዜ በሰውየው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሰውና አሰናበተው።  ከዚያም “ከእናንተ መካከል ልጁ ወይም በሬው በሰንበት ቀን የውኃ ጉድጓድ ውስጥ ቢወድቅ ወዲያውኑ ጎትቶ የማያወጣው ማን ነው?” አላቸው።+  እነሱም ለዚህ መልስ ሊሰጡ አልቻሉም።  ኢየሱስ የተጋበዙት ሰዎች ለራሳቸው የክብር ቦታ ሲመርጡ+ ተመልክቶ እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦  “አንድ ሰው ወደ ሠርግ ሲጠራህ በክብር ቦታ አትቀመጥ።+ ምናልባት ከአንተ የበለጠ የተከበረ ሰው ተጠርቶ ሊሆን ይችላል።  በመሆኑም ሁለታችሁንም የጋበዘው ሰው መጥቶ ‘ቦታውን ለዚህ ሰው ልቀቅለት’ ይልሃል። በዚህ ጊዜ እያፈርክ ወደ ዝቅተኛው ቦታ ትሄዳለህ። 10  አንተ ግን ስትጋበዝ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ የጋበዘህም ሰው ሲመጣ ‘ወዳጄ ሆይ፣ ወደ ላይ ከፍ በል’ ይልሃል። በዚህ ጊዜ አብረውህ በተጋበዙት ሰዎች ሁሉ ፊት ክብር ታገኛለህ።+ 11  ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋልና፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።”+ 12  ቀጥሎ ደግሞ የጋበዘውን ሰው እንዲህ አለው፦ “የምሳ ወይም የራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ጓደኞችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ሀብታም ጎረቤቶችህን አትጥራ። አለዚያ እነሱም ሊጋብዙህና ብድር ሊመልሱልህ ይችላሉ። 13  ሆኖም ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን፣ ሽባዎችን፣ አንካሶችንና ዓይነ ስውራንን ጥራ፤+ 14  ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ ደስተኛ ትሆናለህ። ምክንያቱም በጻድቃን ትንሣኤ+ ብድራት ይመለስልሃል።” 15  ከተጋበዙት መካከል አንዱ ይህን ሲሰማ “በአምላክ መንግሥት፣ ከማዕድ የሚበላ ደስተኛ ነው” አለው። 16  ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “አንድ ሰው ትልቅ የራት ግብዣ አዘጋጅቶ+ ብዙ ሰዎች ጠራ። 17  የራት ግብዣው ሰዓት በደረሰ ጊዜ የተጋበዙትን ሰዎች ‘አሁን ሁሉም ነገር ስለተዘጋጀ ኑ’ ብሎ እንዲጠራቸው ባሪያውን ላከ። 18  ይሁን እንጂ ሁሉም ሰበብ ያቀርቡ ጀመር።+ የመጀመሪያው ‘እርሻ ስለገዛሁ ሄጄ ማየት አለብኝ፤ ስለዚህ እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለው። 19  ሌላውም ‘አምስት ጥማድ በሬዎች ገዝቻለሁ፤ ልፈትናቸው ስለሆነ እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለ።+ 20  ሌላኛው ደግሞ ‘ገና ማግባቴ ስለሆነ መምጣት አልችልም’ አለ። 21  ባሪያውም መጥቶ ለጌታው ይህን ነገረው። በዚህ ጊዜ የቤቱ ጌታ ተቆጣ፤ ከዚያም ባሪያውን ‘ፈጥነህ ወደ ከተማው አውራ ጎዳናዎችና ስላች መንገዶች ሄደህ ድሆችን፣ ሽባዎችን፣ ዓይነ ስውራንንና አንካሶችን ወደዚህ አምጣቸው’ አለው። 22  በኋላም ባሪያው ‘ጌታዬ፣ ያዘዝከው ተፈጽሟል፤ ያም ሆኖ አሁንም ቦታ አለ’ አለው። 23  በመሆኑም ጌታው ባሪያውን እንዲህ አለው፦ ‘ቤቴ እንዲሞላ ወደ ጎዳናዎችና ወደ ስላች መንገዶች ሄደህ ያገኘሃቸውን ሰዎች በግድ አምጥተህ አስገባ።+ 24  እላችኋለሁ፣ ከእነዚያ ከተጋበዙት ሰዎች መካከል አንዳቸውም ያዘጋጀሁትን ራት አይቀምሱም።’”+ 25  ከዚያም እጅግ ብዙ ሕዝብ አብሮት እየተጓዘ ሳለ ወደ እነሱ ዞሮ እንዲህ አላቸው፦ 26  “ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ አባቱን፣ እናቱን፣ ሚስቱን፣ ልጆቹን፣ ወንድሞቹንና እህቶቹን ሌላው ቀርቶ የገዛ ራሱን ሕይወት* እንኳ የማይጠላ*+ ከሆነ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።+ 27  የራሱን የመከራ እንጨት* ተሸክሞ የማይከተለኝ ሁሉ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።+ 28  ለምሳሌ ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው? 29  እንዲህ ካላደረገ ግን መሠረቱን ከጣለ በኋላ ፍጻሜ ላይ ማድረስ ሊያቅተውና የሚያዩት ሰዎች ሁሉ ሊያፌዙበት ይችላሉ፤ 30  ‘ይህ ሰው መገንባት ጀምሮ ነበር፤ መጨረስ ግን አቃተው’ ይሉታል። 31  ወይም ደግሞ አንድ ንጉሥ ሌላን ንጉሥ ጦርነት ለመግጠም በሚነሳበት ጊዜ 20,000 ሠራዊት አስከትቶ የመጣበትን ንጉሥ በ10,000 ሠራዊት ሊቋቋመው ይችል እንደሆነ ለማወቅ በቅድሚያ ተቀምጦ አይማከርም? 32  መቋቋም የማይችል ከሆነ ሊገጥመው የሚመጣው ንጉሥ ገና ሩቅ ሳለ አምባሳደሮች* ልኮ እርቅ ለመፍጠር ይደራደራል። 33  እንደዚሁም ከእናንተ መካከል ያለውን ንብረት ሁሉ የማይሰናበት* ፈጽሞ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።+ 34  “ጨው ጥሩ ነገር እንደሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ጨው ራሱ የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን በምን መመለስ ይቻላል?+ 35  እንዲህ ያለ ጨው ለአፈር የሚሰጠው ጥቅም የለም፤ ማዳበሪያም ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ሰዎች ወደ ውጭ ይጥሉታል። ስለዚህ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

በሰውነት ውስጥ ከልክ በላይ ፈሳሽ እንዲጠራቀም የሚያደርግ በሽታ ነው።
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “አሳንሶ የማይወድ።”
ይህ ቃል አንድን ገዢ ወይም አገር በመወከል ቃል አቀባይ ሆኖ የሚያገለግልን ሰው ያመለክታል።
ወይም “የማይተው።”