በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

2 ጴጥሮስ 2:1-22

2  ይሁን እንጂ በሕዝቡ መካከል ሐሰተኛ ነቢያት እንደነበሩ ሁሉ በእናንተም መካከል ሐሰተኛ አስተማሪዎች ይነሳሉ። እነዚህ ሰዎች ጥፋት የሚያስከትል ኑፋቄ በስውር ያስገባሉ፤ የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ሳይቀር ክደው በራሳቸው ላይ ፈጣን ጥፋት ያመጣሉ።  በተጨማሪም ብዙዎች እነሱ የሚፈጽሙትን የብልግና* ድርጊት ይከተላሉ፤ በእነሱም ምክንያት የእውነት መንገድ ይሰደባል።  እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች አስመሳይ ቃላት በመናገር እናንተን መጠቀሚያ ለማድረግ ይጎመጃሉ። ሆኖም ከብዙ ዘመን በፊት የተበየነባቸው ፍርድ አይዘገይም፤ ጥፋት እንደሚደርስባቸውም ጥርጥር የለውም።*  ደግሞም አምላክ ኃጢአት የሠሩትን መላእክት ከመቅጣት ወደኋላ አላለም፤ ከዚህ ይልቅ በድቅድቅ ጨለማ በተዋጠ ጉድጓድ ውስጥ ሆነው ፍርዳቸውን እንዲጠባበቁ ወደ እንጦሮጦስ* ጣላቸው።  እንዲሁም የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ ፈሪሃ አምላክ ባልነበራቸው ሰዎች በተሞላው ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ ባመጣ ጊዜ የጥንቱን ዓለም ከመቅጣት ወደኋላ አላለም።  በተጨማሪም ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸው ሰዎች ለወደፊቱ ምሳሌ እንዲሆን የሰዶምና የገሞራ ከተሞችን አመድ በማድረግ ፈርዶባቸዋል።  ሆኖም ለሕግ የማይገዙ ሰዎች በሚፈጽሙት ልቅ የሆነ ብልግና እጅግ እየተሳቀቀ ይኖር የነበረውን ጻድቁን ሎጥን አድኖታል።  ይህ ጻድቅ ሰው ዕለት ተዕለት በመካከላቸው ሲኖር በሚያየውና በሚሰማው መረን የለቀቀ ድርጊታቸው ጻድቅ ነፍሱ ትጨነቅ ነበር።  ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ፣ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድንና ዓመፀኛ ሰዎችን ደግሞ በፍርድ ቀን ለሚደርስባቸው ጥፋት እንዴት ጠብቆ እንደሚያቆይ ያውቃል። 10  በተለይ ደግሞ ሌሎችን ለማርከስ በመመኘት የፆታ ብልግና የሚፈጽሙትንና ሥልጣን ያላቸውን የሚንቁትን ለፍርድ ጠብቆ ያቆያቸዋል። ደፋሮችና በራሳቸው የሚመሩ ከመሆናቸውም በላይ የተከበሩትን አይፈሩም፣ እንዲያውም ይሳደባሉ። 11  ይሁንና መላእክት ከእነሱ የላቀ ብርታትና ኃይል ያላቸው ቢሆንም ለይሖዋ ካላቸው አክብሮት የተነሳ ኃይለ ቃል በመናገር አልነቀፏቸውም። 12  እነዚህ ሰዎች ግን ለመያዝና ለመገደል እንደተወለዱ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት ናቸው፤ ባላዋቂነታቸውና በሚሳደቡት ስድብ የተነሳ በራሳቸው የጥፋት ጎዳና ለጥፋት ይዳረጋሉ። 13  ክፉ ድርጊት በመፈጸም በራሳቸው ላይ ክፉ ነገር ያመጣሉ። በጠራራ ፀሐይ መፈንጠዝን እንደ ደስታ ይቆጥሩታል። እነዚህ ሰዎች እንደ ቆሻሻና እድፍ ናቸው፤ ከእናንተ ጋር በግብዣ ላይ ሲገኙ አታላይ በሆኑ ትምህርቶቻቸው ሌሎችን በማሳት እጅግ ይደሰታሉ። 14  አመንዝራ ዓይን ያላቸው በመሆኑ ኃጢአት ከመሥራት መታቀብ አይችሉም፤ ጸንተው ያልቆሙትን ነፍሳትም ያማልላሉ። መጎምጀት የለመደ ልብ አላቸው። የተረገሙ ልጆች ናቸው። 15  ቀናውን መንገድ ትተው በተሳሳተ ጎዳና ሄደዋል። ለጥቅም ሲል ክፉ ድርጊት መፈጸም የመረጠውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለዋል። 16  በለዓም ግን መመሪያውን በመጣሱ ተገሥጿል። መናገር የማትችል አህያ እንደ ሰው ተናግራ የነቢዩን የእብደት አካሄድ ገታች። 17  እነዚህ ሰዎች የደረቁ የውኃ ጉድጓዶችና በአውሎ ነፋስ የሚነዱ ደመናዎች ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማም ይጠብቃቸዋል። 18  በከንቱ ጉራ ይነዛሉ፤ በተሳሳተ ጎዳና ከሚመላለሱ ሰዎች መካከል አምልጠው በመውጣት ላይ ያሉትን በሥጋ ምኞትና በብልግና ያማልላሉ። 19  እነሱ ራሳቸው የመጥፎ ሥነ ምግባር ባሪያዎች ሆነው ሳሉ ነፃ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል። ነገር ግን ሰው ለተሸነፈለት ነገር ሁሉ ባሪያ ነው። 20  ስለ ጌታችንና አዳኛችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ባገኙት ትክክለኛ እውቀት ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ ተመልሰው በዚሁ ነገር ከተጠመዱና ከተሸነፉ ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የከፋ እንደሚሆንባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። 21  የጽድቅን መንገድ በትክክል ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደኋላ ከሚሉ ቀድሞውኑ ባያውቁት ይሻላቸው ነበር። 22  “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤ የታጠበች አሳማም ተመልሳ ጭቃ ላይ ትንከባለላለች” የሚለው እውነተኛ ምሳሌ በእነሱ ላይ ተፈጽሟል።

የግርጌ ማስታወሻዎች

2ጴጥ 2:2 ገላትያ 5:19 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
2ጴጥ 2:3 * ቃል በቃል፣ “ጥፋታቸው አያንቀላፋም።”
2ጴጥ 2:4 * “እንጦሮጦስ” አምላክ በኖኅ ዘመን ያመፁ መላእክትን የጣለበትን የተዋረደና እንደ እስር ቤት ያለ ሁኔታ ያመለክታል።