በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

2 ጢሞቴዎስ 4:1-22

4  በአምላክ ፊት እንዲሁም በመገለጡና በመንግሥቱ አማካኝነት በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ በተዘጋጀው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አጥብቄ አሳስብሃለሁ፤  ቃሉን ስበክ፣ አመቺ በሆነ ወቅትም ሆነ በአስቸጋሪ ወቅት በጥድፊያ ስሜት አገልግል፤ በብዙ ትዕግሥትና በማስተማር ጥበብ ገሥጽ፣ ውቀስ እንዲሁም አጥብቀህ ምከር።  ምክንያቱም ጤናማውን ትምህርት የማይታገሡበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ከራሳቸው ፍላጎት ጋር በሚስማማ ሁኔታ ጆሯቸውን እንዲኮረኩሩላቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ፤  እንዲሁም እውነትን ከመስማት ጆሯቸውን ይመልሳሉ፤ በአንጻሩ ግን ወደ ተረት ዞር ይላሉ።  አንተ ግን በሁሉም ነገር የማመዛዘን ችሎታህን ጠብቅ፣ መከራን በትዕግሥት ተቀበል፣ የወንጌላዊን ሥራ አከናውን እንዲሁም አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም።  ምክንያቱም እኔ በአሁኑ ጊዜ እንደ መጠጥ መሥዋዕት እየፈሰስኩ ነው፤ እንዲሁም ነፃ የምለቀቅበት ጊዜ በጣም ቀርቧል።  መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን እስከ መጨረሻ ሮጫለሁ፤ እምነትን ጠብቄያለሁ።  ከዚህ በኋላ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶ ይጠብቀኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ ቀን እንደ ሽልማት አድርጎ ይሰጠኛል፤ ይሁንና ለእኔ ብቻ ሳይሆን የእሱን መገለጥ ለሚናፍቁ ሁሉ ነው።  በቶሎ ወደ እኔ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ። 10  ምክንያቱም ዴማስ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሥርዓት ወዶ፣ ትቶኝ ወደ ተሰሎንቄ ሄዷል፤ ቄርቂስ ወደ ገላትያ፣ ቲቶ ደግሞ ወደ ድልማጥያ ሄደዋል። 11  አብሮኝ ያለው ሉቃስ ብቻ ነው። ማርቆስ ለአገልግሎት ስለሚጠቅመኝ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና። 12  ቲኪቆስን ግን ወደ ኤፌሶን ልኬዋለሁ። 13  ስትመጣ በጥሮአስ፣ ካርጶስ ጋር የተውኩትን ካባ እንዲሁም የመጽሐፍ ጥቅልሎቹን በተለይም ብራናዎቹን አምጣልኝ። 14  የነሐስ አንጥረኛው እስክንድር ብዙ ጉዳት አድርሶብኛል፤ ይሖዋ እንደ ሥራው ይከፍለዋል፤ 15  እሱ ቃላችንን በኃይል ስለሚቃወም አንተም ከእሱ ተጠንቀቅ። 16  የመጀመሪያ መከላከያዬን ባቀረብኩበት ወቅት ሁሉም ትተውኝ ሄዱ እንጂ ማንም ከእኔ ጎን የቆመ አልነበረም፤ ይህንም አይቁጠርባቸው፤ 17  ሆኖም የስብከቱ ሥራ በእኔ አማካኝነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸምና ሕዝቦች ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ አጠገቤ ቆሞ ኃይል ሰጠኝ፤ ከአንበሳ አፍም ዳንኩ። 18  ጌታ ከክፉ ሥራ ሁሉ ይታደገኛል፤ እንዲሁም አድኖኝ ለሰማያዊ መንግሥቱ ያበቃኛል። ለእሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን። አሜን። 19  ለጵርስቅላና ለአቂላ እንዲሁም ለኦኔሲፎሮስ ቤተሰብ ሰላምታ አቅርብልኝ። 20  ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀርቷል፤ ጢሮፊሞስ ግን ስለታመመ በሚሊጢን ትቼዋለሁ። 21  ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ። ኤውቡሉስ ሰላም ብሎሃል፤ እንዲሁም ጱዴስ፣ ሊኖስ፣ ቅላውዲያና ወንድሞች ሁሉ ሰላምታቸውን ልከውልሃል። 22  ጌታ ከምታሳየው መንፈስ ጋር ይሁን። ጸጋው ከእናንተ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻዎች