በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

2 ቆሮንቶስ 11:1-33

11  በመጠኑ ምክንያታዊነት ቢጎድለኝ እንድትታገሡኝ እፈልጋለሁ። ደግሞም እየታገሣችሁኝ ነው!  በአምላካዊ ቅናት እቀናላችኋለሁ፤ ምክንያቱም እኔ ራሴ እንደ አንዲት ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንድ ባል አጭቻችኋለሁ።  ሆኖም እባቡ ሔዋንን በተንኮሉ እንዳታለላት ሁሉ እናንተም አእምሯችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ልታሳዩ የሚገባውን ቅንነትና ንጽሕና በሆነ መንገድ እንዳታጡ እፈራለሁ።  ምክንያቱም አንድ ሰው መጥቶ እኛ የሰበክንላችሁን ሳይሆን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ ወይም ከተቀበላችሁት መንፈስ የተለየ መንፈስ ብትቀበሉ ወይም ከተቀበላችሁት ምሥራች የተለየ ሌላ ምሥራች ብትቀበሉ እንዲህ ያለውን ሰው ዝም ብላችሁ ትቀበሉታላችሁ ማለት ነው።  እኔ ከእናንተ ምርጥ ሐዋርያት በምንም ነገር የማንስ አይመስለኝም።  የተዋጣልኝ ተናጋሪ ባልሆን እንኳ እውቀት የሚጎድለኝ ግን አይደለሁም፤ ይህንም በሁሉም ነገር በብዙ መንገድ አሳይተናችኋል።  ወይስ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ የአምላክን ምሥራች ለእናንተ ያለ ዋጋ በደስታ መስበኬ እንደ ኃጢአት ተቆጥሮብኝ ይሆን?  እናንተን ለማገልገል ከሌሎች ጉባኤዎች እርዳታ በመቀበሌ እነሱን ዘርፌያለሁ፤  ከእናንተ ጋር ሳለሁ ተቸግሬ በነበረበት ጊዜ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን ነገር በሙሉ በሚገባ ስላሟሉልኝ ለማንም ሸክም አልሆንኩም። አዎ፣ እስካሁን ድረስ በእናንተ ላይ በምንም መንገድ ሸክም አልሆንኩም፤ ወደፊትም ሸክም አልሆንም። 10  የክርስቶስ እውነት በውስጤ እስካለ ድረስ በአካይያ ክልሎች ያለኝን ይህን ትምክህት ምንም ነገር ሊገታው አይችልም። 11  ይህን ያደረግኩት ለምንድን ነው? ስለማልወዳችሁ ነው? እንደምወዳችሁ አምላክ ያውቃል። 12  ከእኛ ጋር እኩል ለመሆን የሚፈልጉትና እኛም ሐዋርያት ነን ብለው የሚኩራሩት ሰዎች ለዚህ የሚሆን መሠረት እንዳያገኙ አሁን እያደረግኩት ያለሁትን ወደፊትም አደርጋለሁ። 13  ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለውጡ ሐሰተኛ ሐዋርያትና አታላይ ሠራተኞች ናቸው። 14  ይህም ምንም አያስደንቅም፤ ምክንያቱም ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ዘወትር ራሱን ይለዋውጣል። 15  ስለዚህ አገልጋዮቹም የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል በየጊዜው ራሳቸውን ቢለዋውጡ ምንም አያስገርምም። ሆኖም ፍጻሜያቸው እንደ ሥራቸው ይሆናል። 16  ማንም ሰው ምክንያታዊ እንዳልሆንኩ አድርጎ እንዳያየኝ ዳግመኛ እናገራለሁ። አሁንም እንደዚያ አድርጋችሁ የምትመለከቱኝ ከሆነ እኔም በመጠኑ እንድኩራራ ምክንያታዊነት የሚጎድለኝ ቢሆንም እንኳ ተቀበሉኝ። 17  የኩራት መለያ ባሕርይ በሆነው በትምክህት እንደዚህ የምናገረው የጌታን ምሳሌ በመከተል ሳይሆን ምክንያታዊነት እንደሚጎድለው ሰው ሆኜ ነው። 18  ብዙዎች በሥጋዊ ነገር ስለሚኩራሩ እኔም እኩራራለሁ። 19  እናንተ ምክንያታዊ ስለሆናችሁ ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰዎችን በደስታ ትታገሣላችሁ። 20  እንዲያውም ማንም እንደ ባሪያ ቢያደርጋችሁ፣ ማንም ያላችሁን ሙልጭ አድርጎ ቢወስድባችሁ፣ ማንም ያላችሁን ቢቀማችሁ፣ ማንም ራሱን ከፍ ከፍ ቢያደርግባችሁ ወይም ማንም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁ። 21  ይህን መናገር ለእኛ አሳፋሪ ነው፤ ምክንያቱም አንዳንዶች በሥልጣናችን በአግባቡ መጠቀም የማንችል ደካሞች እንደሆን አድርገው ያስባሉ። ሆኖም ምክንያታዊነት እንደሚጎድለው ሰው ልናገርና ማንም ሰው በሆነ ነገር የልብ ልብ የሚሰማው ከሆነ እኔም በዚያው ነገር የልብ ልብ ሊሰማኝ ይችላል። 22  ዕብራውያን ናቸው? እኔም ነኝ። እስራኤላውያን ናቸው? እኔም ነኝ። የአብርሃም ዘር ናቸው? እኔም ነኝ። 23  የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸው? እንደ እብድ ሰው ልናገርና እኔ ከሁሉ በላቀ ደረጃ የክርስቶስ አገልጋይ ነኝ:- ከሁሉም ይበልጥ በሥራ ብዙ ደክሜያለሁ፣ ብዙ ጊዜ ታስሬያለሁ፣ ብዙ ጊዜ ተደብድቤያለሁ፣ ብዙ ጊዜ ሞት አፋፍ ደርሻለሁ። 24  አይሁዳውያን ለአርባ ጅራፍ አንድ የቀረው አምስት ጊዜ ገርፈውኛል፤ 25  ሦስት ጊዜ በዱላ ተደብድቤያለሁ፣ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬያለሁ፣ ሦስት ጊዜ የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጥሞኛል፣ አንድ ሌሊትና አንድ ቀን በጥልቅ ባሕር ውስጥ ውዬ አድሬያለሁ፤ 26  ብዙ ጊዜ ተጉዣለሁ፣ ደግሞም በወንዝ ሙላት ለሚመጣ አደጋ፣ ወንበዴዎች ለሚያደርሱት አደጋ፣ የገዛ ወገኖቼ ለሚያመጡት አደጋ፣ ከአሕዛብ ለሚሰነዘር አደጋ፣ በከተማ ለሚያጋጥም አደጋ፣ በምድረ በዳ ለሚያጋጥም አደጋ፣ በባሕር ላይ ለሚያጋጥም አደጋና በሐሰተኛ ወንድሞች መካከል ለሚያጋጥም አደጋ ተጋልጬ ነበር፤ 27  ብዙ ጥሬያለሁ፣ ብዙ ደክሜያለሁ፣ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ ሳልተኛ አድሬያለሁ፣ ተርቤያለሁ፣ ተጠምቻለሁ፣ ብዙ ጊዜ ምግብ ሳልቀምስ ኖሬያለሁ፣ በብርድና በራቁትነት ተቆራምጃለሁ። 28  ከእነዚህ ውጫዊ ችግሮች በተጨማሪ ዕለት ዕለት የሚያስጨንቀኝ የጉባኤዎች ሁሉ ሐሳብ ነው። 29  ደካማ ማን ነው? እኔስ ድካም አይሰማኝም? የሚሰናከል ማን ነው? እኔስ አልናደድም? 30  መኩራራት ካስፈለገ ድክመቴን በሚያሳዩ ነገሮች እኩራራለሁ። 31  ለዘላለም የሚመሰገነው የጌታ ኢየሱስ አምላክና አባት እየዋሸሁ እንዳልሆነ ያውቃል። 32  በደማስቆ የንጉሥ አሬጣስ የበታች የሆነው ገዥ ሊይዘኝ ፈልጎ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር፤ 33  ሆኖም በግንቡ መስኮት በኩል በቅርጫት አውርደውኝ ከእጁ አመለጥኩ።

የግርጌ ማስታወሻዎች