በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ--አዲስ ዓለም ትርጉም በ2013 ተሻሽሎ የወጣውን ተመልከት

2 ቆሮንቶስ 1:1-24

1  በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፣ በቆሮንቶስ ለሚገኘው የአምላክ ጉባኤ እንዲሁም በመላው አካይያ ለሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ:-  አባታችን ከሆነው ከአምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።  ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት የተባረከ ይሁን፤  አምላክ እኛን እያጽናናበት ባለው ማጽናኛ በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል እሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።  ስለ ክርስቶስ ብለን የምንቀበለው መከራ ብዙ እንደሆነ ሁሉ በክርስቶስ በኩል የምናገኘው ማጽናኛም እንደዚሁ ብዙ ነው።  እኛ መከራ መቀበላችን ለእናንተ መጽናኛና መዳን ያስገኛል፤ ማጽናኛ ማግኘታችን ደግሞ በእኛ ላይ የደረሰው መከራ በእናንተም ላይ ሲደርስ እንድትጸኑ የሚያደርግ ማጽናኛ ይሆንላችኋል።  ስለዚህ እናንተን በተመለከተ ያለን ተስፋ የማይናወጥ ነው፤ ይህም የሆነው መከራውን ከእኛ ጋር እንደምትካፈሉ ሁሉ መጽናኛውንም እንደምትካፈሉ ስለምናውቅ ነው።  ወንድሞች፣ በእስያ አውራጃ ስለደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንፈልጋለን፤ ከአቅማችን በላይ የሆነ ከባድ መከራ ደርሶብን ስለነበር በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እንኳ ተሟጦ ነበር።  እንዲያውም በውስጣችን የሞት ፍርድ እንደተፈረደብን ሆኖ ተሰምቶን ነበር። ይህም በራሳችን ሳይሆን ሙታንን በሚያስነሳው አምላክ እንድንታመን ነው። 10  እንዲህ ካለ ለሞት የሚዳርግ ሁኔታ አድኖናል፤ ደግሞም ያድነናል፤ ወደፊትም እንደሚያድነን በእሱ ተስፋ እናደርጋለን። 11  እናንተም ስለ እኛ ምልጃ በማቅረብ ልትረዱን ትችላላችሁ። ይህን ማድረጋችሁ ብዙዎች በሚያቀርቡት ልመና የተነሳ ለሚደረግልን ደግነት ብዙ ሰዎች ስለ እኛ የምስጋና ጸሎት እንዲያቀርቡ ያነሳሳቸዋል። 12  የምንመካበት ነገር ይህ ነው፤ በዓለም ውስጥ በተለይም በእናንተ መካከል በቅድስናና በአምላካዊ ቅንነት እንደኖርን ሕሊናችን ይመሠክራል፤ ይህንም ያደረግነው በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን በአምላክ ጸጋ ነው። 13  በሚገባ ከምታውቁት ወይም ደግሞ አምናችሁ ከተቀበላችሁት ነገር በስተቀር ሌላ ምንም ነገር አንጽፍላችሁም፤ ይህንም እስከ መጨረሻው አምናችሁ እንደምትቀበሉት ተስፋ አደርጋለሁ፤ 14  በተጨማሪም በእኛ መመካት እንደምትችሉ በተወሰነ መጠን አምናችሁ እንደተቀበላችሁ ሁሉ እኛም በጌታችን በኢየሱስ ቀን በእናንተ እንመካለን። 15  በመሆኑም በዚህ በመተማመን ዳግመኛ እንድትደሰቱ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እናንተ ለመምጣት ቀደም ሲል አቅጄ ነበር፤ 16  ከእናንተ ጋር ለአጭር ጊዜ ከቆየሁ በኋላ ወደ መቄዶንያ ለመሄድና ከመቄዶንያ ወደ እናንተ ለመመለስ ከዚያም የተወሰነ መንገድ ከሸኛችሁኝ በኋላ ወደ ይሁዳ ለመሄድ አስቤ ነበር። 17  እንዲህ ዓይነት እቅድ አውጥቼ የነበረው እንዲሁ ሳላስብበት ይመስላችኋል? ወይስ ማንኛውንም ነገር ሳቅድ በሥጋዊ ስሜት ተነድቼ በማቀድ አንዴ “አዎ፣ አዎ” መልሼ ደግሞ “አይ፣ አይ” የምል ይመስላችኋል? 18  ከዚህ ይልቅ አምላክ እምነት የሚጣልበት እንደሆነ ሁሉ እኛ ለእናንተ የምንናገረው ቃልም አዎ ከሆነ አይ ማለት ሊሆን አይችልም። 19  ምክንያቱም እኛ ማለትም እኔ፣ ስልዋኖስና* ጢሞቴዎስ የሰበክንላችሁ የአምላክ ልጅ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ አዎ ሆኖ እያለ አይደለም ሊሆን አይችልም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ ጋር በተያያዘ አዎ፣ አዎ ሆኗል። 20  አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች የቱንም ያህል ብዙ ቢሆኑም በእሱ አማካኝነት አዎ ሆነዋል። ስለዚህ እኛ ለአምላክ ክብር እንድንሰጥ በእሱ አማካኝነት ለአምላክ “አሜን” እንላለን። 21  ይሁንና እናንተም ሆናችሁ እኛ የክርስቶስ እንደሆንን ዋስትና የሰጠንና የቀባን አምላክ ነው። 22  በተጨማሪም ማኅተሙን በእኛ ላይ ያተመ ሲሆን ወደፊት ለሚመጣው ነገርም መያዣ ሰጥቶናል፤ ይህም በልባችን ውስጥ ያለው መንፈስ ነው። 23  ወደ ቆሮንቶስ እስካሁን ያልመጣሁት ለባሰ ሐዘን እንዳልዳርጋችሁ ብዬ ነው፤ ይህ እውነት ካልሆነ አምላክ በገዛ ነፍሴ ላይ ይመሥክርብኝ። 24  ጸንታችሁ የቆማችሁት በራሳችሁ እምነት ስለሆነ እኛ ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር አብረን የምንሠራ ነን እንጂ በእምነታችሁ ላይ የምናዝ አይደለንም።

የግርጌ ማስታወሻዎች

2ቆሮ 1:19 * ወይም፣ “ሲላስ።”