በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

1 ጴጥሮስ 1:1-25

1  የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጴጥሮስ፤ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢቲኒያ ተበትነው ለሚገኙ ጊዜያዊ ነዋሪዎች ለሆኑ የአምላክ ምርጦች  ይኸውም አባት የሆነው አምላክ አስቀድሞ ባወቀው መሠረት ለተመረጡት፣ በመንፈስ ለሚቀደሱት እንዲሁም ለኢየሱስ ክርስቶስ ታዛዥ ለሚሆኑትና በደሙ ለሚረጩት:- ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።  የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ምክንያቱም እሱ በታላቅ ምሕረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት ለሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ወልዶናል፤  እንዲሁም ለማይበሰብስ፣ ለማይረክስና ለማይጠፋ ርስት ወልዶናል። ይህም በሰማይ ለእናንተ ተጠብቆላችኋል፤  እናንተንም አምላክ በዘመኑ መጨረሻ ለሚገለጠው መዳን በእምነት አማካኝነት በኃይሉ እየጠበቃችሁ ነው።  አሁን ለአጭር ጊዜ በተለያዩ ፈተናዎች ለማዘን ብትገደዱም እንኳ በእነዚህ ሁሉ ነገሮች የተነሳ እጅግ እየተደሰታችሁ ነው፤  እነዚህ ፈተናዎች የሚደርሱባችሁ በእሳት የተፈተነ ቢሆንም እንኳ ሊጠፋ ከሚችለው ወርቅ እጅግ የላቀ ዋጋ ያለው ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ግርማንና ክብርን ያስገኝ ዘንድ ነው።  እሱን አይታችሁት ባታውቁም እንኳ ትወዱታላችሁ። አሁን እያያችሁት ባይሆንም እንኳ በእሱ ላይ ያላችሁን እምነት በተግባር እያሳያችሁና በቃላት ሊገለጽ በማይችል ታላቅ ደስታ እጅግ ሐሴት እያደረጋችሁ ነው፤  ምክንያቱም የእምነታችሁን የመጨረሻ ውጤት ይኸውም የነፍሳችሁን መዳን ታገኛላችሁ። 10  ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ የተነበዩት ነቢያት ይህንኑ መዳን በተመለከተ ትጋት የተሞላበት ምርምርና ጥልቅ ጥናት አካሂደዋል። 11  በውስጣቸው ያለው መንፈስ በክርስቶስ ላይ ስለሚደርሱት መከራዎችና ከዚያ በኋላ ስለሚከናወኑት ክብራማ ነገሮች አስቀድሞ ሲመሠክር ስለ የትኛው ወቅት ወይም ስለ ምን ዓይነት ወቅት እያመለከተ እንዳለ መመርመራቸውን ቀጥለው ነበር። 12  እነሱ ራሳቸውን እያገለገሉ እንዳልሆነ ተገልጦላቸው ነበር። ከዚህ ይልቅ ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ምሥራቹን ባበሰሩላችሁ ሰዎች አማካኝነት የተነገሯችሁን ነገሮች በማቅረብ እናንተን እያገለገሉ ነበር። መላእክትም እነዚሁኑ ነገሮች በቅርበት ለማየት ይጓጓሉ። 13  በመሆኑም አእምሯችሁን ዝግጁ በማድረግ ለሥራ ታጠቁ፤ የማስተዋል ስሜታችሁን በሚገባ ጠብቁ፤ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ለእናንተ በሚታደለው ጸጋ ላይ አድርጉ። 14  ታዛዥ ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ እውቀት ባልነበራችሁ ጊዜ ትከተሉት በነበረው ምኞት መሠረት መቀረጻችሁን ተዉ፤ 15  ከዚህ ይልቅ የጠራችሁ ቅዱስ አምላክ፣ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም ራሳችሁ በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ 16  ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ልትሆኑ ይገባል” ተብሎ ተጽፏል። 17  በተጨማሪም ምንም ሳያዳላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት የምትጠሩ ከሆነ መጻተኛ ሆናችሁ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ በፍርሃት ኑሩ። 18  ምክንያቱም እናንተ ከቀድሞ አባቶቻችሁ በወግና ልማድ ከወረሳችሁት ፍሬ ቢስ አኗኗር ነፃ የወጣችሁት ሊበላሹ በሚችሉ ነገሮች ይኸውም በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። 19  ከዚህ ይልቅ ነፃ የወጣችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም ባለ ውድ ደም ያውም በክርስቶስ ደም ነው። 20  እርግጥ እሱ አስቀድሞ የታወቀው ዓለም ከመመሥረቱ በፊት ነው፤ ሆኖም ለእናንተ ሲባል በዘመናት መጨረሻ ላይ እንዲገለጥ ተደረገ፤ 21  እናንተም እምነታችሁና ተስፋችሁ በአምላክ ላይ ይሆን ዘንድ እሱን ከሞት ባስነሳውና ክብር ባጎናጸፈው አምላክ ያመናችሁት በእሱ አማካኝነት ነው። 22  እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን ስላነጻችሁ ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ ሊኖራችሁና እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ልትዋደዱ ይገባል። 23  ሕያው በሆነውና ጸንቶ በሚኖረው አምላክ ቃል አማካኝነት እንደ አዲስ የተወለዳችሁት በሚበሰብስ ሳይሆን በማይበሰብስ የሚያፈራ ዘር ነው። 24  ምክንያቱም “ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነው፤ ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ 25  የይሖዋ ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” ለእናንተም እንደ ምሥራች ሆኖ የተሰበከላችሁ “ቃል” ይህ ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች