በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

1 ጢሞቴዎስ 6:1-21

6  የአምላክ ስምና ትምህርት ፈጽሞ እንዳይሰደብ በባርነት ቀንበር ሥር ያሉ ሁሉ ጌቶቻቸው ሙሉ ክብር ሊሰጣቸው እንደሚገባ አድርገው ዘወትር ያስቡ።  በተጨማሪም አማኝ የሆኑ ጌቶች ያሏቸው ባሪያዎች ጌቶቻቸው ወንድሞች ስለሆኑ አይናቋቸው። ከዚህ ይልቅ እነሱ ከሚሰጡት ጥሩ አገልግሎት እየተጠቀሙ ያሉት፣ አማኞችና የተወደዱ ስለሆኑ በተሻለ ሁኔታ ያገልግሏቸው። እነዚህን ነገሮች ማስተማርህንና እነዚህን ማሳሰቢያዎች መስጠትህን ቀጥል።  አንድ ሰው የተለየ ትምህርት ቢያስተምርና ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጤናማ ቃላት ጋርም ሆነ ለአምላክ ማደርን ከሚያበረታታው ትምህርት ጋር የማይስማማ ቢሆን  ይህ ሰው በትዕቢት የተወጠረና ምንም የማያስተውል ነው፤ ይሁንና ስለ ቃላት ጥያቄ የማንሳትና የመከራከር አባዜ የተጠናወተው ነው። እንዲህ ካሉ ነገሮች ምቀኝነት፣ ጠብ፣ ስድብና መጥፎ ጥርጣሬ ይመነጫል፤  በተጨማሪም እንዲህ ያሉ ነገሮች፣ ለአምላክ ማደር ጥቅም ማግኛ እንደሆነ አድርገው በሚያስቡ፣ አእምሯቸው በተበላሸና እውነትን በተቀሙ ሰዎች መካከል እርባና በሌላቸው ጉዳዮች የከረረ ጭቅጭቅ ያስነሳሉ።  በእርግጥ፣ ባለው ነገር ለሚረካ ሰው ለአምላክ ማደር ትልቅ ትርፍ ያስገኛል።  ምክንያቱም ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለም፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም።  ስለዚህ ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።  ይሁን እንጂ ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ ፈተናና ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፤ እንዲሁም ሰዎችን ጥፋትና ብልሽት ውስጥ በሚዘፍቁ ከንቱና ጎጂ በሆኑ ብዙ ምኞቶች ይያዛሉ። 10  ምክንያቱም የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው፤ አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተጠምደው ከእምነት ጎዳና ስተው ወጥተዋል፤ እንዲሁም ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል። 11  የአምላክ ሰው ሆይ፣ አንተ ግን ከእነዚህ ነገሮች ሽሽ። ከዚህ ይልቅ ጽድቅን፣ ለአምላክ ማደርን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ጽናትንና ገርነትን ተከታተል። 12  መልካሙን የእምነት ተጋድሎ ተጋደል፤ የተጠራህለትንና በብዙ ምሥክሮች ፊት በጥሩ ሁኔታ በይፋ የተናገርክለትን የዘላለም ሕይወት አጥብቀህ ያዝ። 13  ሁሉንም ነገሮች ሕያው አድርጎ በሚያኖረው አምላክና ለጳንጥዮስ ጲላጦስ በይፋ ግሩም ምሥክርነት በሰጠው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት ይህን አዝሃለሁ:- 14  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ትእዛዙን ያለ እንከንና ያለ ነቀፋ ጠብቅ። 15  የነገሥታት ንጉሥ፣ እንዲሁም የጌቶች ጌታ የሆነው ደስተኛውና ብቸኛው ኃያል ገዥ ይህን መገለጥ በተወሰነለት ጊዜ ያሳያል፤ 16  ያለመሞትን ባሕርይ የተላበሰው እሱ ብቻ ነው፤ ሊቀረብ በማይችል ብርሃን ውስጥ ይኖራል፤ እሱን ያየ ወይም ሊያየው የሚችል አንድም ሰው የለም። ክብርና ዘላለማዊ ኃይል ለእሱ ይሁን። አሜን። 17  አሁን ባለው ሥርዓት ውስጥ ሀብታም የሆኑት ሰዎች፣ ራሳቸውን ከፍ አድርገው እንዳይመለከቱ እንዲሁም ተስፋቸውን አስተማማኝነት በሌለው ሀብት ላይ ሳይሆን ለእኛ ደስታ ሲል ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን አምላክ ላይ እንዲጥሉ እዘዛቸው፤ 18  በተጨማሪም መልካም ነገር እንዲያደርጉ፣ በመልካም ሥራዎች ባለጸጋ እንዲሆኑ እንዲሁም ለጋሶችና ለማካፈል ፈቃደኞች እንዲሆኑ እዘዛቸው፤ 19  እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀው መያዝ ይችሉ ዘንድ በዚህ መንገድ ለራሳቸው ውድ ሀብት ማከማቸታቸውን ይኸውም ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን መልካም መሠረት መጣላቸውን ይቀጥሉ። 20   ጢሞቴዎስ ሆይ፣ ቅዱስ የሆነውን ነገር ከሚጻረሩ ከንቱ ንግግሮችና በውሸት “እውቀት” ተብለው ከሚጠሩ እርስ በርሳቸው ከሚቃረኑ ሐሳቦች በመራቅ በአደራ የተሰጠህን ነገር ጠብቅ። 21  ምክንያቱም አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱ እውቀት እንዲታይላቸው ለማድረግ ሲጣጣሩ ከእምነት ጎዳና ወጥተዋል። የአምላክ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻዎች