በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

1 ዮሐንስ 4:1-21

4  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ በመንፈስ የተነገረን ቃል ሁሉ አትመኑ፤ ከዚህ ይልቅ በመንፈስ የተነገሩት ቃላት ከአምላክ የመነጩ መሆን አለመሆናቸውን መርምሩ፤ ምክንያቱም ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋል።  ከአምላክ የመነጨውን በመንፈስ የተነገረ ቃል በዚህ ማወቅ ትችላላችሁ:- ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚመሠክር በመንፈስ የተነገረ ቃል ሁሉ ከአምላክ የመነጨ ነው፤  ሆኖም ስለ ኢየሱስ የማይመሠክር በመንፈስ የተነገረ ቃል ሁሉ ከአምላክ የሚመነጭ አይደለም። ከዚህም በተጨማሪ ይህ በመንፈስ የተነገረ ቃል፣ ይመጣል ሲባል ከሰማችሁት ፀረ ክርስቶስ የሚመነጭ ነው፤ አሁንም እንኳ በዓለም ላይ ይገኛል።  ልጆቼ ሆይ፣ እናንተ ከአምላክ ወገን ናችሁ፤ እነሱንም አሸንፋችኋል፤ ምክንያቱም ከእናንተ ጋር አንድነት ያለው አምላክ፣ ከዓለም ጋር አንድነት ካለው ከዲያብሎስ ይበልጣል።  እነሱ የዓለም ወገን ናቸው፤ ከዓለም የሚመነጨውን ነገር የሚናገሩትና ዓለምም የሚሰማቸው ለዚህ ነው።  እኛ ከአምላክ ወገን ነን። ስለ አምላክ እውቀት ያለው ሰው ይሰማናል፤ ከአምላክ ወገን ያልሆነ ሰው አይሰማንም። በመንፈስ የተነገረውን የእውነት ቃልና በመንፈስ የተነገረውን የሐሰት ቃል ለይተን የምናውቀው በዚህ መንገድ ነው።  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እርስ በርስ መዋደዳችንን እንቀጥል፤ ምክንያቱም ፍቅር ከአምላክ ነው፤ ፍቅር የሚያሳይ ሁሉ ከአምላክ የተወለደ ሲሆን ስለ አምላክም እውቀት አለው።  ፍቅር የማያሳይ አምላክን አያውቅም፤ ምክንያቱም አምላክ ፍቅር ነው።  የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በሚከተለው መንገድ ተገልጧል፤ ምክንያቱም እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል። 10  ፍቅር የተገለጠው በዚህ መንገድ ነው፤ እኛ አምላክን ስለወደድነው ሳይሆን እሱ ስለወደደንና ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት እንዲሆን ልጁን ስለላከ ነው። 11  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ አምላክ የወደደን በዚህ መንገድ ከሆነ እኛም እርስ በርሳችን የመዋደድ ግዴታ አለብን። 12  መቼም ቢሆን አምላክን ያየው ማንም የለም። እርስ በርስ መዋደዳችንን ከቀጠልን አምላክ አብሮን ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ውስጥ ፍጹም ይሆናል። 13  እኛ ከእሱ ጋር ያለንን አንድነት ጠብቀን እንደምንኖርና እሱም ከእኛ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ እንደሚኖር በዚህ እናውቃለን፤ ምክንያቱም እሱ መንፈሱን ሰጥቶናል። 14  ከዚህም በተጨማሪ አብ ልጁን የዓለም አዳኝ አድርጎ እንደላከው እኛ ራሳችን አይተናል፤ ደግሞም እየመሠከርን ነው። 15  ማንም ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ልጅ መሆኑን የሚመሠክር ከሆነ አምላክ እንዲህ ካለው ሰው ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ይኖራል፤ እሱም ከአምላክ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ይኖራል። 16  ደግሞም አምላክ ከእኛ ጋር በተያያዘ ያለውን ፍቅር እኛ ራሳችን አውቀናል፤ እንዲሁም አምነናል። አምላክ ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር ከአምላክ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ይኖራል፤ አምላክም ከእሱ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ይኖራል። 17  በፍርድ ቀን የመናገር ነፃነት ይኖረን ዘንድ ፍቅር ከእኛ ጋር በተያያዘ ፍጹም የሆነው በዚህ መንገድ ነው፤ ምክንያቱም ልክ ኢየሱስ እንደሆነው ሁሉ እኛ ራሳችንም በዚህ ዓለም ውስጥ እንደዚሁ ነን። 18  በፍቅር ፍርሃት የለም፤ ሆኖም ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል፤ ምክንያቱም ፍርሃት ነፃነት ያሳጣል። ደግሞም የሚፈራ ሰው ፍጹም የሆነ ፍቅር የለውም። 19  እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም በበኩላችን ፍቅር እናሳያለን። 20  ማንም “አምላክን እወደዋለሁ” እያለ ወንድሙን የሚጠላ ከሆነ ይህ ሰው ውሸታም ነው። ምክንያቱም ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን አምላክ ሊወድ አይችልም። 21  እሱም አምላክን የሚወድ ወንድሙንም መውደድ ይገባዋል የሚል ትእዛዝ ሰጥቶናል።

የግርጌ ማስታወሻዎች