በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

1 ተሰሎንቄ 5:1-28

5  እንግዲህ ወንድሞች፣ ጊዜያትንና ወቅቶችን በተመለከተ ምንም ነገር እንዲጻፍላችሁ አያስፈልግም።  ምክንያቱም የይሖዋ ቀን የሚመጣው ልክ ሌባ በሌሊት በሚመጣበት ዓይነት መንገድ መሆኑን እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ።  “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” ሲሉ የምጥ ጣር እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል፤ ደግሞም በምንም ዓይነት አያመልጡም።  እናንተ ግን ወንድሞች፣ በጨለማ ውስጥ ስላልሆናችሁ ሌሊቱ ድንገት እንደሚነጋበት ሌባ ያ ቀን ድንገት አይደርስባችሁም፤  ምክንያቱም እናንተ ሁላችሁ የብርሃን ልጆችና የቀን ልጆች ናችሁ። እኛ የሌሊት ወይም የጨለማ ሰዎች አይደለንም።  ስለዚህ ነቅተን እንኑር እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታችንን እንጠብቅ እንጂ እንደ ሌሎቹ አናንቀላፋ።  ምክንያቱም የሚያንቀላፉ በሌሊት የማንቀላፋት ልማድ አላቸው፤ የሚሰክሩም በአብዛኛው የሚሰክሩት በሌሊት ነው።  የብርሃን ሰዎች የሆንነው እኛ ግን የማመዛዘን ችሎታችንን እንጠብቅ እንዲሁም የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር እንልበስ፤ የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንድፋ፤  ምክንያቱም አምላክ የመረጠን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳን እንድናገኝ ነው እንጂ ለቁጣ አይደለም። 10  እሱ በሕይወት ብንኖርም ሆነ በሞት ብናንቀላፋ ከእሱ ጋር እንድንኖር ለእኛ ሞቶልናል። 11  ስለዚህ አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርሳችሁ መጽናናታችሁንና እርስ በርስ መተናነጻችሁን ቀጥሉ። 12  እንግዲህ ወንድሞች፣ በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩና በጌታ ሥራ አመራር እየሰጧችሁ ያሉትን እንዲሁም ምክር እየለገሷችሁ ያሉትን እንድታከብሯቸው እንለምናችኋለን፤ 13  በተጨማሪም በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ በፍቅር የላቀ አክብሮት እንድታሳዩአቸው እንለምናችኋለን። እርስ በርስ ባላችሁ ግንኙነት ሰላማውያን ሁኑ። 14  በሌላ በኩል ደግሞ ወንድሞች፣ ይህን እናሳስባችኋለን:- በሥርዓት የማይሄዱትን ገሥጿቸው፤ የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ። 15  ማንም ሰው በማንም ላይ በክፉ ፋንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርሳችሁም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሁሉ ምንጊዜም መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ተጣጣሩ። 16  ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ። 17  ያለማቋረጥ ጸልዩ። 18  ስለ ሁሉም ነገር አመስግኑ። ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ አምላክ ለእናንተ ያለው ፈቃድ ይህ ነው። 19  የመንፈስን እሳት አታጥፉ። 20  ትንቢትን አትናቁ። 21  ሁሉንም ነገር መርምሩ፤ መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ። 22  ከማንኛውም ዓይነት ክፋት ራቁ። 23  የሰላም አምላክ ራሱ ሙሉ በሙሉ ይቀድሳችሁ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ መንፈሳችሁ፣ ነፍሳችሁና አካላችሁ በማንኛውም ረገድ ጤናማ ሆኖ ከነቀፋ ነፃ በሆነ መንገድ ተጠብቆ ይቆይ። 24  የጠራችሁ ታማኝ ነው፤ ደግሞም ይህን ያደርገዋል። 25  ወንድሞች፣ ስለ እኛ መጸለያችሁን አታቋርጡ። 26  ወንድሞችን ሁሉ በተቀደሰ መሳሳም ሰላም በሏቸው። 27  ይህ ደብዳቤ ለወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አደራ እላችኋለሁ። 28  የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻዎች