በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

1 ቆሮንቶስ 16:1-24

16  ለቅዱሳን የሚሰባሰበውን መዋጮ በተመለከተ ደግሞ በገላትያ ለሚገኙ ጉባኤዎች በሰጠሁት መመሪያ መሠረት እናንተም እንዲሁ አድርጉ።  መዋጮ የሚሰባሰበው እኔ በምመጣበት ጊዜ እንዳይሆን ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን እንደ ገቢው ሁኔታ የተወሰነ መጠን በቤቱ ያስቀምጥ።  በምመጣበት ጊዜ ግን መርጣችሁ የድጋፍ ደብዳቤ የምትጽፉላቸውን ሰዎች የልግስና ስጦታችሁን ኢየሩሳሌም እንዲያደርሱ እልካቸዋለሁ።  ይሁን እንጂ የእኔም መሄድ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ አብረውኝ ይሄዳሉ።  ይሁንና በመቄዶንያ በኩል ማለፌ ስለማይቀር በመቄዶንያ በኩል ሳልፍ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤  ወደምሄድበትም ቦታ የተወሰነ መንገድ እንድትሸኙኝ ምናልባት እናንተ ጋር እቆይ እንዲያውም ክረምቱን ከእናንተ ጋር አሳልፍ ይሆናል።  ምክንያቱም አሁን እንዲያው እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጎበኛችሁ አልፈልግም፤ ይሖዋ ቢፈቅድ እናንተ ጋር የተወሰነ ጊዜ እቆያለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።  ይሁንና እስከ ጴንጤቆስጤ በዓል ድረስ በኤፌሶን እቆያለሁ፤  ምክንያቱም ትልቅ የሥራ በር ተከፍቶልኛል፤ ሆኖም ብዙ ተቃዋሚዎች አሉ። 10  ይሁን እንጂ ጢሞቴዎስ ከመጣ በመካከላችሁ ያለ ፍርሃት እንዲቀመጥ አድርጉ፤ ምክንያቱም እሱም እንደ እኔ የይሖዋን ሥራ የሚሠራ ነው። 11  ስለዚህ ማንም አይናቀው። ከወንድሞች ጋር እየጠበቅኩት ስለሆነ ወደ እኔ እንዲመጣ የተወሰነ መንገድ ድረስ በሰላም ሸኙት። 12  ወንድማችንን አጵሎስን በተመለከተ ደግሞ ከወንድሞች ጋር ወደ እናንተ እንዲመጣ አጥብቄ ለምኜው ነበር፤ እሱ ግን በጭራሽ አሁን ለመምጣት አልፈለገም፤ ሆኖም ሁኔታው ሲመቻችለት ይመጣል። 13  ነቅታችሁ ኑሩ፣ በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ፣ ምንጊዜም ወንድ ሁኑ፣ ብርቱዎች ሁኑ። 14  የምታደርጉትን ነገር ሁሉ በፍቅር አድርጉ። 15  እንግዲህ ወንድሞች ይህን አሳስባችኋለሁ:- የእስጢፋናስ ቤተሰብ የአካይያ በኩራት እንደሆኑና ቅዱሳንን ለማገልገል ራሳቸውን እንደሰጡ ታውቃላችሁ። 16  እናንተም እንደ እነሱ ላሉትም ሆነ አብረው ለሚሠሩና ለሚደክሙ ሁሉ ዘወትር ተገዙ። 17  በእስጢፋናስና በፈርጡናጦስ እንዲሁም በአካይቆስ መኖር እጅግ ተደስቻለሁ፤ ምክንያቱም የእናንተ እዚህ አለመገኘት በእነሱ ተካክሷል። 18  እነሱ የእኔንም ሆነ የእናንተን መንፈስ አድሰዋል። ስለዚህ እንዲህ ላሉት ሰዎች እውቅና ልትሰጡ ይገባል። 19  በእስያ ያሉ ጉባኤዎች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። አቂላና ጵርስቅላ እንዲሁም በቤታቸው ያለው ጉባኤ በጌታ ከልብ የመነጨ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 20  ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። እርስ በርሳችሁ በተቀደሰ መሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ። 21  እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ የጻፍኩላችሁ ሰላምታ ይድረሳችሁ። 22  ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፣ ና! 23  የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። 24  በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ያለኝ ፍቅር ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻዎች