በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ--አዲስ ዓለም ትርጉም በ2013 ተሻሽሎ የወጣውን ተመልከት

1 ቆሮንቶስ 12:1-31

12  ወንድሞች፣ አሁን ደግሞ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች እንድታውቁ እፈልጋለሁ።  አሕዛብ በነበራችሁበት ጊዜ ድምፅ ወደሌላቸው ጣዖታት ዝም ብላችሁ ትነዱ እንደነበር ታውቃላችሁ።  ስለዚህ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ “ኢየሱስ የተረገመ ነው!” የሚል ማንም የለም፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ካልሆነ በቀር ማንም “ኢየሱስ ጌታ ነው!” ብሎ ሊናገር እንደማይችል እንድታውቁ እወዳለሁ።  ልዩ ልዩ ስጦታዎች አሉ፤ መንፈስ ግን ያው አንድ መንፈስ ነው፤  ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፤ ጌታ ግን ያው አንድ ጌታ ነው፤  በተጨማሪም ልዩ ልዩ አሠራሮች አሉ፤ ሆኖም የተለያዩ አሠራሮችን በመጠቀም በሁሉም ሰዎች ላይ የሚሠራው ያው አንድ አምላክ ነው።  ሆኖም መንፈስ በእያንዳንዱ ሰው አማካኝነት ጠቃሚ ለሆነ ዓላማ ይገለጣል።  ለምሳሌ ያህል፣ ለአንዱ በመንፈስ አማካኝነት በጥበብ የመናገር ችሎታ ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በዚያው መንፈስ በእውቀት የመናገር ችሎታ ይሰጠዋል፤  ለሌላው በዚያው መንፈስ እምነት ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በዚያው መንፈስ የመፈወስ ስጦታ ይሰጠዋል፤ 10  እንዲሁም ለሌላው ተአምራት የመሥራት፣ ለሌላው ትንቢት የመናገር፣ ለሌላው በመንፈስ መሪነት የተነገረን ቃል የመረዳት፣ ለሌላው በተለያዩ ልሳኖች የመናገር፣ ለሌላው ደግሞ ልሳኖችን የመተርጎም ችሎታ ይሰጠዋል። 11  ሆኖም ለእያንዳንዱ በግለሰብ ደረጃ እነዚህን ስጦታዎች እንደፈቀደ በማከፋፈል እነዚህን ሁሉ አሠራሮች የሚያከናውነው ያው አንድ መንፈስ ነው። 12  አካል አንድ ቢሆንም ብዙ የአካል ክፍሎች እንዳሉትና የዚህ አካል ክፍሎች በሙሉ ብዙ ቢሆኑም አንድ አካል እንደሆኑ ሁሉ ክርስቶስም እንደዚሁ ነው። 13  ምክንያቱም አይሁዳውያንም ሆን ግሪካውያን፣ ባሪያዎችም ሆን ነፃ ሰዎች ሁላችንም አንድ አካል ለመሆን በአንድ መንፈስ ተጠምቀናል፤ እንዲሁም ሁላችንም አንድ መንፈስ እንድንጠጣ ተሰጥቶናል። 14  በእርግጥ አካል አንድ ብቻ ሳይሆን ብዙ የአካል ክፍሎችን ያቀፈ ነው። 15  እግር “እኔ እጅ ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ አይቀርም። 16  እንዲሁም ጆሮ “እኔ ዓይን ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ አይቀርም። 17  አካል በሙሉ ዓይን ቢሆን ኖሮ እንዴት መስማት ይቻል ነበር? አካል በሙሉ ጆሮ ቢሆን ኖሮ እንዴት ማሽተት ይቻል ነበር? 18  ሆኖም አምላክ ለእያንዳንዱ የአካል ክፍል እሱ በፈለገው መንገድ በአካል ውስጥ ቦታ መድቦለታል። 19  ሁሉም አንድ ዓይነት የአካል ክፍል ቢሆን ኖሮ ሙሉ አካል ከየት ይገኝ ነበር? 20  አሁን ግን የአካል ክፍሎች ብዙ ቢሆኑም አካል ግን አንድ ነው። 21  ዓይን እጅን “አንተ አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም፤ ወይም ደግሞ ራስ እግርን “አንተ አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም። 22  ደካማ የሚመስሉት የአካል ክፍሎች እንዲያውም በጣም አስፈላጊ ናቸው፤ 23  ብዙም ክብር የላቸውም ብለን የምናስባቸውን የአካል ክፍሎች የበለጠ ክብር እንሰጣቸዋለን፤ በመሆኑም የምናፍርባቸው የአካል ክፍሎች ይበልጥ ክብር የተላበሱ ናቸው፤ 24  በአንጻሩ ደግሞ የማናፍርባቸው የአካል ክፍሎች ምንም አያስፈልጋቸውም። ይሁንና አምላክ ክብር የሚጎድለውን የአካል ክፍል ብዙ ክብር በማልበስ አካልን አዋህዷል፤ 25  ይህንም ያደረገው በአካል መካከል ክፍፍል እንዳይኖር፣ ከዚህ ይልቅ የአካል ክፍሎቹ እርስ በርሳቸው እኩል እንዲተሳሰቡ ነው። 26  አንድ የአካል ክፍል ቢሠቃይ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይሠቃያሉ፤ ወይም አንድ የአካል ክፍል ክብር ቢያገኝ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይደሰታሉ። 27  እንግዲህ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ክፍሎች ናችሁ። 28  አምላክ የተለያዩ የአካል ክፍሎችን ይኸውም አንደኛ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛ ነቢያትን፣ ሦስተኛ አስተማሪዎችን፣ ከዚያም ተአምር የሚፈጽሙትን፣ ከዚያም የመፈወስ ስጦታ ያላቸውን፣ ጠቃሚ አገልግሎት የሚያከናውኑትን፣ የመምራት ችሎታ ያላቸውንና በተለያዩ ልሳኖች የሚናገሩትን በጉባኤ ውስጥ መድቧል። 29  ሁሉም ሐዋርያት አይደሉም፤ ናቸው እንዴ? ሁሉም ነቢያት አይደሉም፤ ናቸው እንዴ? ሁሉም አስተማሪዎች አይደሉም፤ ናቸው እንዴ? ሁሉም ተአምር አይሠሩም፤ ይሠራሉ እንዴ? 30  ሁሉም የመፈወስ ስጦታ የላቸውም፤ አላቸው እንዴ? ሁሉም በልሳን አይናገሩም፤ ይናገራሉ እንዴ? ሁሉም ተርጓሚዎች አይደሉም፤ ናቸው እንዴ? 31  ነገር ግን ብልጫ ያላቸውን ስጦታዎች ለማግኘት ብርቱ ጥረት ማድረጋችሁን ቀጥሉ። ደግሞም ከሁሉ የላቀውን መንገድ አሳያችኋለሁ።

የግርጌ ማስታወሻዎች