በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ--አዲስ ዓለም ትርጉም በ2013 ተሻሽሎ የወጣውን ተመልከት

ገላትያ 5:1-26

5  ክርስቶስ ነፃ ያወጣን እንዲህ ዓይነት ነፃነት እንድናገኝ ነው። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ ዳግመኛ ራሳችሁን በባርነት ቀንበር አታስጠምዱ።  እነሆ እኔ ጳውሎስ፣ የምትገረዙ ከሆነ ክርስቶስ ለእናንተ ምንም እንደማይጠቅማችሁ ልነግራችሁ እወዳለሁ።  በተጨማሪም የሚገረዝ እያንዳንዱ ሰው መላውን ሕግ የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ዳግም እመሠክርለታለሁ።  በሕግ አማካኝነት ጻድቃን ተብላችሁ ለመጠራት የምትጥሩ ሁሉ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፤ ከጸጋውም ርቃችኋል።  እኛ ግን ተስፋ የምናደርገውን በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ በመንፈስ አማካኝነት በጉጉት እንጠባበቃለን።  ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ ጠቃሚ የሆነው፣ በፍቅር የሚመራ እምነት እንጂ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይደለም።  በአግባቡ ትሮጡ ነበር፤ ታዲያ ለእውነት መታዘዛችሁን እንዳትቀጥሉ እንቅፋት የሆነባችሁ ማን ነው?  እንዲህ ያለው ማግባቢያ እየጠራችሁ ካለው የመጣ አይደለም።  ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። 10  ከጌታ ጋር አንድነት ያላችሁ ሁሉ የተለየ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ እተማመናለሁ፤ ሆኖም እያወካችሁ ያለው ማንም ይሁን ማን ፍርዱን ይቀበላል። 11  ወንድሞች፣ እኔ አሁንም ስለ መገረዝ እየሰበክሁ ከሆነ እስካሁን ለምን ስደት ይደርስብኛል? እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ የመከራው እንጨት* እንቅፋት መሆኑ በቀረ ነበር። 12  ለውድቀት ሊዳርጓችሁ እየሞከሩ ያሉት ሰዎች ራሳቸው ከናካቴው ቢሰለቡ ደስታዬ ነው። 13  እርግጥ ነው ወንድሞች፣ የተጠራችሁት ነፃ እንድትወጡ ነው፤ ብቻ ይህን ነፃነት የሥጋችሁን ፍላጎት ለማነሳሳት አትጠቀሙበት፤ ይልቁንም አንዳችሁ ሌላውን በፍቅር አገልግሉ። 14  ምክንያቱም መላው ሕግ “ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ” በሚለው ቃል ተጠቃሏል። 15  ይሁንና እርስ በርሳችሁ መነካከሳችሁንና መባላታችሁን ካልተዋችሁ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። 16  እኔ ግን በመንፈስ መመላለሳችሁን ቀጥሉ እላለሁ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ የሥጋን ምኞት ከቶ አትፈጽሙም። 17  የሥጋ ፍላጎት ከመንፈስ ፍላጎት ጋር፣ የመንፈስ ፍላጎት ደግሞ ከሥጋ ፍላጎት ጋር አይጣጣምም፤ እነዚህ እርስ በርሳቸው ይቃረናሉ። ስለሆነም ማድረግ የምትፈልጉትን አታደርጉም። 18  በተጨማሪም በመንፈስ የምትመሩ ከሆነ በሕግ ሥር አይደላችሁም። 19  የሥጋ ሥራዎች የታወቁ ናቸው፤ እነሱም:- ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ብልግና፣* 20  ጣዖት አምልኮ፣ መናፍስታዊ ድርጊት፣ ጠላትነት፣ ጠብ፣ ቅናት፣ በቁጣ መገንፈል፣ የከረረ ጭቅጭቅ፣ መከፋፈል፣ መናፍቅነት፣ 21  ምቀኝነት፣ ሰካራምነት፣ መረን የለቀቀ ፈንጠዝያና እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው። እነዚህን በተመለከተ አስቀድሜ እንዳስጠነቀቅኳችሁ ሁሉ አሁንም አስጠነቅቃችኋለሁ፤ እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙ የአምላክን መንግሥት አይወርሱም። 22  በሌላ በኩል ግን የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ 23  ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚከለክል ሕግ የለም። 24  ከዚህም በተጨማሪ የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከመጥፎ ምኞቱና ፍላጎቱ ጋር ገድለውታል።* 25  በመንፈስ የምንኖር ከሆነ መንፈስ የሚሰጠንን አመራር በመከተል ዘወትር በሥርዓት እንመላለስ። 26  በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ገላ 5:11 * ከተጨማሪው መረጃ ላይ 6ኛውን ርዕስ ተመልከት።
ገላ 5:14 * “ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
ገላ 5:19 “አሴሊያ” የሚለው የግሪክኛ ቃል እፍረተ ቢስነትን ወይም ንቀትን በሚያንጸባርቅ ሁኔታ የአምላክን ሕጎች መጣስን ያመለክታል።
ገላ 5:24 * ቃል በቃል፣ “ሰቅለውታል።”