በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ገላትያ 1:1-24

1  ከሰዎች ወይም በሰው ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም እሱን ከሞት ባስነሳውና አባታችን በሆነው አምላክ አማካኝነት ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣  አብረውኝም ካሉት ወንድሞች ሁሉ፣ በገላትያ ላሉት ጉባኤዎች:-  አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።  ኢየሱስ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ አሁን ካለው ክፉ ሥርዓት ያድነን ዘንድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ፤  ከዘላለም እስከ ዘላለም ለአምላክ ክብር ይሁን። አሜን።  በክርስቶስ ጸጋ ከጠራችሁ ከእሱ እንዲህ በፍጥነት እየራቃችሁ መሄዳችሁና ለሌላ ዓይነት ምሥራች ጆሯችሁን መስጠት መጀመራችሁ ደንቆኛል።  እርግጥ ሌላ ዓይነት ምሥራች አይደለም፤ ሆኖም እናንተን ግራ የሚያጋቡና ስለ ክርስቶስ የሚናገረውን ምሥራች ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ።  ይሁን እንጂ ከእኛ መካከል አንዱ ወይም ከሰማይ የወረደ መልአክ፣ ከሰበክንላችሁ ምሥራች የተለየ ሌላ ምሥራች ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።  ከላይ እንደተናገርነው፣ አሁንም ደግሜ እላለሁ፣ ማንም ይሁን ማን ከተቀበላችሁት የተለየ ሌላ ምሥራች ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። 10  አሁን እኔ ለማሳመን እየጣርኩ ያለሁት ሰውን ነው ወይስ አምላክን? ወይስ ሰዎችን ለማስደሰት እየፈለግኩ ነው? ገና አሁንም ሰዎችን እያስደሰትኩ ከሆነ የክርስቶስ ባሪያ አይደለሁም ማለት ነው። 11  ወንድሞች፣ እኔ የሰበኩላችሁ ምሥራች ከሰው የመነጨ ምሥራች እንዳልሆነ ላሳውቃችሁ እወዳለሁ፤ 12  ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በራእይ ገለጠልኝ እንጂ የተቀበልኩትም ሆነ የተማርኩት ከሰው አይደለም። 13  በእርግጥ፣ ቀድሞ በአይሁድ ሃይማኖት ሳለሁ ምን ዓይነት ሰው እንደነበርኩ ሰምታችኋል፤ የአምላክን ጉባኤ ከልክ በላይ አሳድድና አጠፋ ነበር፤ 14  ለአባቶቼ ወግ እጅግ ከፍተኛ ቅንዓት ስለነበረኝ ከወገኖቼ መካከል በእኔ ዕድሜ ካሉት ከብዙዎቹ የበለጠ በአይሁድ ሃይማኖት የላቀ እድገት እያደረግኩ ነበር። 15  ሆኖም ከእናቴ ማህፀን እንድለይ ያደረገኝና በጸጋው አማካኝነት የጠራኝ አምላክ 16  ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች ለአሕዛብ አውጅ ዘንድ ልጁን በእኔ አማካኝነት ለመግለጥ በወደደ ጊዜ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር ለመማከር አልሄድኩም። 17  በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት ከእኔ በፊት ሐዋርያት ወደሆኑትም አልሄድኩም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ ዓረብ አገር ሄድኩ፤ እንደገናም ተመልሼ ወደ ደማስቆ መጣሁ። 18  ከዚያም ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ለመጠየቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤ ከእሱም ጋር አሥራ አምስት ቀን ተቀመጥኩ። 19  ሆኖም ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በስተቀር ከሐዋርያት መካከል ሌላ ማንንም አላየሁም። 20  እንግዲህ እየጻፍኩላችሁ ያለሁትን ነገር በተመለከተ እነሆ በአምላክ ፊት እናገራለሁ፣ እየዋሸሁ አይደለሁም። 21  ከዚያ በኋላ በሶርያና በኪልቅያ ወዳሉ ክልሎች ሄድኩ። 22  ሆኖም በይሁዳ ያሉ የክርስቲያን ጉባኤዎች በአካል አይተውኝ አያውቁም ነበር፤ 23  ይሁንና “ከዚህ ቀደም ያሳድደን የነበረው ሰው በፊት ሊያጠፋው ይፈልግ ስለነበረው እምነት የሚገልጸውን ምሥራች አሁን እየሰበከ ነው” የሚል ወሬ ብቻ ይሰሙ ነበር። 24  ስለዚህ በእኔ ምክንያት አምላክን ከፍ ከፍ ያደርጉ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች