በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ዮሐንስ 9:1-41

9  በመንገድ እያለፈ ሳለም ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነ አንድ ሰው አየ።  ደቀ መዛሙርቱም “ረቢ፣ ይህ ሰው ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደው ማን በሠራው ኃጢአት ነው? በራሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ?” ሲሉ ጠየቁት።  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ:- “እሱም ሆነ ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም፤ ይህ የሆነው ግን የአምላክ ሥራ በእሱ ላይ እንዲገለጥ ነው።  የላከኝን የእሱን ሥራ ቀን ሳለ መሥራት አለብን፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል።  በዓለም እስካለሁ ድረስ የዓለም ብርሃን ነኝ።”  ይህን ካለ በኋላ መሬት ላይ እንትፍ ብሎ በምራቁ ከሸክላ አፈር ጭቃ አበጀ፤ ከዚያም ጭቃውን በሰውየው ዓይኖች ላይ ቀባ፤  ሰውየውንም “ሄደህ በሰሊሆም (ትርጉሙ ‘አፈትልኮ ወጣ’ ማለት ነው) ገንዳ ውስጥ ታጠብ” አለው። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም ተመልሶ መጣ።  ስለዚህ ጎረቤቶቹና ቀደም ሲል ሲለምን ያዩት የነበሩ ሰዎች “ይህ ሰው ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለም እንዴ?” ይሉ ጀመር።  አንዳንዶች “አዎ፣ እሱ ነው” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “አይ፣ እሱን ይመስላል እንጂ እሱ አይደለም” ይሉ ነበር። ሰውየው ግን “እኔው ነኝ” ይል ነበር። 10  በመሆኑም “ታዲያ እንዴት ዓይኖችህ ተከፈቱ?” ይሉት ጀመር። 11  እሱም “ኢየሱስ የተባለው ሰው ጭቃ ለውሶ ዓይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም ሄደህ ታጠብ’ አለኝ። እኔም ሄጄ ታጠብኩ፤ ዓይኔም በራልኝ” ሲል መለሰ። 12  በዚህ ጊዜ “ሰውየው የት አለ?” አሉት። እሱም “እኔ አላውቅም” አለ። 13  እነሱም ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። 14  እንደ አጋጣሚ ሆኖ ኢየሱስ ጭቃውን የለወሰበትና የሰውየውን ዓይኖች የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበር። 15  በዚህ ጊዜ ፈሪሳውያኑም እንዴት ማየት እንደቻለ ይጠይቁት ጀመር። እሱም “ሰውየው ዓይኖቼን ጭቃ ቀባ፤ እኔም ታጠብኩ፤ ከዚያም ማየት ቻልኩ” አላቸው። 16  ስለዚህ ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር ከአምላክ የመጣ ሰው አይደለም” ይሉ ጀመር። ሌሎቹ ደግሞ “ኃጢአተኛ የሆነ ሰው እንዲህ ያሉ ምልክቶችን እንዴት ሊፈጽም ይችላል?” ይሉ ጀመር። በመሆኑም በመካከላቸው ክፍፍል ተፈጠረ። 17  ስለዚህ ዓይነ ስውሩን ሰው በድጋሚ “አንተስ ይህ ሰው ዓይኖችህ እንዲበሩ በማድረጉ ስለ እሱ ምን ትላለህ?” አሉት። ሰውየውም “እሱ ነቢይ ነው” አለ። 18  ይሁን እንጂ አይሁዳውያኑ ዓይኖቹ የበሩለትን ሰው ወላጆች እስከጠሩበት ጊዜ ድረስ ሰውየው ዓይነ ስውር እንደነበረና በኋላ ዓይኑ እንደበራለት አላመኑም ነበር። 19  ወላጆቹንም “ዓይነ ስውር ሆኖ ተወልዷል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነው? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” ሲሉ ጠየቋቸው። 20  ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ:- “ይህ ልጃችን እንደሆነና ዓይነ ስውር ሆኖ እንደተወለደ እናውቃለን። 21  አሁን ግን እንዴት ሊያይ እንደቻለ የምናውቀው ነገር የለም፤ ዓይኖቹን ማን እንደከፈተለትም አናውቅም። እሱን ጠይቁት፤ ሙሉ ሰው ነው። ስለ ራሱ መናገር ያለበት እሱ ነው።” 22  ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁዳውያኑን ስለፈሩ ነው፤ ምክንያቱም አይሁዳውያን ኢየሱስን ክርስቶስ ነው ብሎ የመሠከረ ማንኛውም ሰው ከምኩራብ እንዲገለል አስቀድመው ወስነው ነበር። 23  ወላጆቹ “ሙሉ ሰው ነው። እሱን ጠይቁት” ያሉት ለዚህ ነበር። 24  ስለዚህ ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ለሁለተኛ ጊዜ ጠርተው “እውነቱን በመናገር አምላክን አክብር፤ እኛ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እናውቃለን” አሉት። 25  እሱም መልሶ “ኃጢአተኛ ይሁን አይሁን የማውቀው ነገር የለም። እኔ የማውቀው ዓይነ ስውር እንደነበርኩና አሁን ግን ማየት እንደቻልኩ ነው” አለ። 26  በዚህ ጊዜ “ምንድን ነው ያደረገልህ? ዓይንህን የከፈተልህ እንዴት ነው?” አሉት። 27  እሱም “ነገርኳችሁ እኮ፤ እናንተ ግን አትሰሙም። እንደገና መስማት የፈለጋችሁት ለምንድን ነው? እናንተም የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን ፈለጋችሁ እንዴ?” ሲል መለሰላቸው። 28  እነሱም ሰውየውን በመስደብ እንዲህ አሉት:- “የዚያ ሰው ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን። 29  አምላክ ሙሴን እንዳነጋገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደመጣ አናውቅም።” 30  ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “ከየት እንደመጣ አለማወቃችሁ በጣም የሚያስገርም ነገር ነው፤ ያም ሆነ ይህ ዓይኖቼን ከፍቶልኛል። 31  አምላክ ኃጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ ፈሪሃ አምላክ ያለውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን ሁሉ ግን ይሰማዋል። 32  ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዓይኖች የከፈተ አለ ሲባል ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተሰምቶ አይታወቅም። 33  ይህ ሰው ከአምላክ ባይሆን ኖሮ ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልም ነበር።” 34  እነሱም መልሰው “አንተ ሁለመናህ በኃጢአት ተበክሎ የተወለድክ! እኛን ልታስተምር ትፈልጋለህ?” አሉት። ከዚያ በኋላም አባረሩት! 35  ኢየሱስም ሰውየውን እንዳባረሩት ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ “በሰው ልጅ ላይ እምነት አለህ?” አለው። 36  ሰውየውም “ጌታዬ፣ አምንበት ዘንድ እሱ ማን ነው?” ሲል መለሰ። 37  ኢየሱስም “አይተኸዋል፤ ደግሞም እያነጋገረህ ያለው እሱ ነው” አለው። 38  በዚህ ጊዜ “ጌታ ሆይ፣ በእሱ አምናለሁ” አለ። ከዚያም ሰገደለት። 39  ኢየሱስም “የማያዩ ማየት እንዲችሉ፣ የሚያዩም እንዲታወሩ፣ ለዚህ ፍርድ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ” አለ። 40  ከእሱ ጋር የነበሩ ፈሪሳውያንም ይህን ሰምተው “እኛ መቼም ዕውሮች አይደለንም፤ ነን እንዴ?” አሉት። 41  ኢየሱስም “ዕውሮች ብትሆኑማ ኖሮ ኃጢአት ባልኖረባችሁ ነበር። አሁን ግን እናንተ ‘እናያለን’ ትላላችሁ። ስለዚህ ኃጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል” አላቸው።

የግርጌ ማስታወሻዎች