በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ--አዲስ ዓለም ትርጉም በ2013 ተሻሽሎ የወጣውን ተመልከት

ዮሐንስ 4:1-54

4  ጌታ፣ እሱ ከዮሐንስ ይበልጥ ብዙ ደቀ መዛሙርት እያፈራና እያጠመቀ መሆኑን ፈሪሳውያን እንደሰሙ አወቀ፤  እርግጥ ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም፤  እሱም ይህን ባወቀ ጊዜ ይሁዳን ለቆ እንደገና ወደ ገሊላ ሄደ።  ሆኖም በሰማርያ በኩል ማለፍ ነበረበት።  ስለሆነም ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው መሬት አጠገብ ወዳለችው ሲካር ወደተባለች የሰማርያ ከተማ መጣ።  ደግሞም በዚያ የያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ ነበረ። ኢየሱስም ከጉዞው የተነሳ ደክሞት ስለነበር በውኃ ጉድጓዱ አጠገብ ተቀመጠ። ጊዜው ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር።  አንዲት የሰማርያ ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም “የምጠጣው ውኃ ስጪኝ” አላት።  (ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማይቱ ሄደው ነበር።)  በዚህ ጊዜ ሳምራዊቷ ሴት “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለ እኔን ሳምራዊቷን ሴት እንዴት የምጠጣው ውኃ ስጪኝ ትለኛለህ?” አለችው። (ይህን ያለችው አይሁዳውያን ከሳምራውያን ጋር ምንም ግንኙነት ስላልነበራቸው ነው።) 10  ኢየሱስም መልሶ “የአምላክን ነፃ ስጦታ ብታውቂና ‘የምጠጣው ውኃ ስጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ አንቺ ራስሽ ትጠይቂው ነበር፤ እሱም ሕያው ውኃ ይሰጥሽ ነበር” አላት። 11  እሷም እንዲህ አለችው:- “ጌታዬ፣ አንተ ውኃ መቅጃ እንኳ የለህም፤ ጉድጓዱ ደግሞ ጥልቅ ነው። ታዲያ ይህን ሕያው ውኃ ከየት ታገኛለህ? 12  አንተ ይህን የውኃ ጉድጓድ ከሰጠንና እሱ ራሱ ከልጆቹና ከከብቶቹ ጋር ከዚህ ጉድጓድ ከጠጣው ከአባታችን ከያዕቆብ አትበልጥም፤ ትበልጣለህ እንዴ?” 13  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላት:- “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል። 14  እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ፈጽሞ አይጠማም፤ ከዚህ ይልቅ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ ይሆናል።” 15  ሴትየዋም “ጌታዬ፣ እንዳልጠማም ሆነ ውኃ ለመቅዳት ወደዚህ ቦታ እንዳልመላለስ ይህን ውኃ ስጠኝ” አለችው። 16  እሱም “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ተመለሽ” አላት። 17  ሴትየዋም መልሳ “ባል የለኝም” አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት:- “‘ባል የለኝም’ ማለትሽ ትክክል ነው። 18  ምክንያቱም አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁን አብሮሽ ያለው ሰው ደግሞ ባልሽ አይደለም። ስለዚህ የተናገርሽው እውነት ነው።” 19  ሴትየዋም እንዲህ አለችው:- “ጌታዬ፣ አንተ ነቢይ እንደሆንክ አሁን ተረዳሁ። 20  አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ አምልኳቸውን ያካሂዱ ነበር፤ እናንተ ግን ሰዎች አምልኳቸውን ማካሄድ ያለባቸው በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ።” 21  ኢየሱስም እንዲህ አላት:- “አንቺ ሴት፣ እመኚኝ፤ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም አብን የማታመልኩበት ሰዓት እየመጣ ነው። 22  እናንተ የማታውቁትን ታመልካላችሁ፤ እኛ ግን መዳን የሚመጣው በአይሁድ በኩል ስለሆነ የምናውቀውን እናመልካለን። 23  ይሁንና እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩበት ሰዓት እየመጣ ነው፤ ያም ሰዓት አሁን ነው፤ ምክንያቱም አብ እንዲህ ዓይነት ሰዎች እንዲያመልኩት ይፈልጋል። 24  አምላክ መንፈስ ነው፤ የሚያመልኩትም በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል።” 25  ሴትየዋም “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ አውቃለሁ። እሱ ሲመጣ ሁሉንም ነገር ግልጥልጥ አድርጎ ይነግረናል” አለችው። 26  ኢየሱስም “እያነጋገርኩሽ ያለሁት እኔ እሱ ነኝ” አላት። 27  በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡ፤ ከሴት ጋር ሲነጋገር አይተውም ይደነቁ ጀመር። ይሁን እንጂ “ምን ፈልገህ ነው?” ወይም “ከእሷ ጋር የምትነጋገረው ለምንድን ነው?” ያለው ማንም አልነበረም። 28  ሴትየዋም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማይቱ በመሄድ ለሰዎቹ እንዲህ አለቻቸው:- 29  “ያደረግኩትን ሁሉ የነገረኝን ሰው መጥታችሁ እዩ። ምናልባት ይህ ሰው ክርስቶስ ይሆን እንዴ?” 30  እነሱም ከከተማይቱ ወጥተው ወደ እሱ ይመጡ ጀመር። 31  ይህ በእንዲህ እንዳለ ደቀ መዛሙርቱ “ረቢ፣ ብላ እንጂ” እያሉ ጎተጎቱት። 32  እሱ ግን “እናንተ የማታውቁት የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው።  33  ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ እርስ በርሳቸው “መቼም ምግብ ያመጣለት የለም፤ ይኖር ይሆን እንዴ?” ይባባሉ ጀመር። 34  ኢየሱስም እንዲህ አላቸው:- “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው። 35  እናንተ መከር ሊገባ ገና አራት ወር ይቀረዋል ትሉ የለም? እነሆ እላችኋለሁ:- ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ። አሁንም ቢሆን እንኳ 36  አጫጁ ደሞዙን እየተቀበለና ለዘላለም ሕይወት ፍሬ እየሰበሰበ ነው፤ ስለዚህ ዘሪውም ሆነ አጫጁ በአንድነት ደስ ይላቸዋል። 37  ከዚህም የተነሳ ‘አንዱ ይዘራል፣ ሌላኛውም ያጭዳል’ የሚለው አባባል በእርግጥም እውነት ነው። 38  እኔም ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ። ሌሎች በደከሙበት እናንተ የድካማቸው ፍሬ ተቋዳሾች ሆናችሁ።” 39  ሴትየዋ “ያደረግኩትን ሁሉ ነገረኝ” ብላ ስለመሠከረች ከዚያች ከተማ ብዙ ሳምራውያን በእሱ አመኑ። 40  በመሆኑም ሳምራውያኑ ወደ እሱ በመጡ ጊዜ አብሯቸው እንዲቆይ ይለምኑት ጀመር፤ እሱም በዚያ ሁለት ቀን ቆየ። 41  ስለሆነም ሌሎች ብዙ ሰዎች ከተናገረው ቃል የተነሳ አመኑ፤ 42  ሴትየዋንም “ከእንግዲህ የምናምነው አንቺ ስለነገርሽን ብቻ አይደለም፤ ምክንያቱም እኛ ራሳችን ሰምተናል፤ እንዲሁም ይህ ሰው በእርግጥ የዓለም አዳኝ እንደሆነ አውቀናል” ይሏት ጀመር። 43  ከሁለቱ ቀናት በኋላ ከዚያ ተነስቶ ወደ ገሊላ ሄደ። 44  ይሁንና ኢየሱስ ራሱ፣ ነቢይ በገዛ አገሩ እንደማይከበር መሥክሮ ነበር። 45  ገሊላ በደረሰ ጊዜም የገሊላ ሰዎች በጥሩ ሁኔታ ተቀበሉት፤ ምክንያቱም በኢየሩሳሌም በበዓሉ ላይ ተገኝተው በዚያ ያከናወናቸውን ነገሮች ሁሉ አይተው ነበር። 46  ከዚያም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ወደለወጠባት በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ቃና በድጋሚ መጣ። በዚህ ጊዜ በቅፍርናሆም ልጁ የታመመበት የንጉሡ አገልጋይ የሆነ አንድ ሰው ነበር። 47  ይህ ሰው ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መምጣቱን ሲሰማ ወደ እሱ ሄደና ወደ ቅፍርናሆም ወርዶ በሞት አፋፍ ላይ ያለውን ልጁን እንዲፈውስለት ይለምነው ጀመር። 48  ኢየሱስ ግን “መቼም እናንተ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ካላያችሁ ፈጽሞ አታምኑም” አለው። 49  የንጉሡ አገልጋይም “ጌታዬ፣ ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ ውረድ” አለው። 50  ኢየሱስም “ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት ይኖራል” አለው። ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ሄደ። 51  ሆኖም ገና ሰውየው ወደዚያ እየወረደ ሳለ ባሪያዎቹ አገኙትና ልጁ መዳኑን ነገሩት። 52  በመሆኑም ልጁ ስንት ሰዓት ላይ እንደተሻለው ይጠይቃቸው ጀመር። እነሱም “ትናንት ሰባት ሰዓት ላይ ትኩሳቱ ለቀቀው” አሉት። 53  ስለዚህ አባትየው ልጁ የዳነው ልክ ኢየሱስ “ልጅህ በሕይወት ይኖራል” ባለው ሰዓት ላይ መሆኑን አወቀ። እሱና መላው ቤተሰቡም አመኑ። 54  ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ ሲመጣ ያከናወነው ሁለተኛው ምልክት ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች