በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ--አዲስ ዓለም ትርጉም በ2013 ተሻሽሎ የወጣውን ተመልከት

ያዕቆብ 3:1-18

3  ወንድሞቼ ሆይ፣ እኛ የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ስለምታውቁ ከእናንተ መካከል ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ።  ምክንያቱም ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን። በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው መላ ሰውነቱን ጭምር መቆጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው።  ፈረሶች እንዲታዘዙልን አፋቸው ውስጥ ልጓም ካስገባን መላ ሰውነታቸውን ጭምር መቆጣጠር እንችላለን።  ጀልባዎችንም ተመልከቱ! ምንም እንኳ በጣም ትልቅና በኃይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የጀልባው ነጂ በትንሽ መቅዘፊያ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይመራቸዋል።  ልክ እንደዚሁም ምላስ ትንሽ የአካል ክፍል ሆና ሳለ ጉራዋን ትነዛለች። እነሆ፣ በጣም ሰፊ የሆነን ጫካ በእሳት ለማያያዝ ትንሽ እሳት ብቻ ይበቃል!  ምላስም እሳት ናት። ምላስ በአካል ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ የክፋት ዓለም ናት፤ ምክንያቱም መላ ሰውነትን ትበክላለች፤ እንዲሁም ተፈጥሯዊውን የሕይወት ሂደት ታቃጥላለች፤ እሷም በገሃነም* ትቃጠላለች።  ማንኛውም ዓይነት የዱር እንስሳ፣ ወፍ፣ በደረቱ የሚሳብ ፍጥረትና በባሕር ውስጥ የሚኖር ፍጥረት በሰዎች ሊገራ ይችላል፣ ደግሞም ተገርቷል።  ምላስን ግን ሊገራ የሚችል አንድም ሰው የለም። ምላስ ገዳይ መርዝ የሞላባት ለመቆጣጠር የምታስቸግር ጎጂ ነገር ናት።  በምላሳችን አባት የሆነውን ይሖዋን እንባርካለን፤ ይሁንና በዚችው ምላሳችን ደግሞ “በአምላክ አምሳል” የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። 10  ከአንድ አፍ በረከትና እርግማን ይወጣሉ። ወንድሞቼ፣ እነዚህ ነገሮች በዚህ ሁኔታ ሊቀጥሉ አይገባም። 11  አንድ ምንጭ ከዚያው ጉድጓድ ጣፋጭና መራራ ውኃ አያፈልቅም፤ ያፈልቃል እንዴ? 12  ወንድሞቼ፣ የበለስ ዛፍ ወይራን ወይም ደግሞ ወይን በለስን ሊያፈራ አይችልም፤ ይችላል እንዴ? እንዲሁም ከጨዋማ ውኃ ጣፋጭ ውኃ ሊገኝ አይችልም። 13  ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ ሰው ማን ነው? ሥራውን የሚያከናውነው ከጥበብ በመነጨ ገርነት መሆኑን በመልካም ምግባሩ ያሳይ። 14  ሆኖም በልባችሁ ውስጥ መራራ ቅናትና ምቀኝነት ካለ አትኩራሩ፤ እንዲሁም በእውነት ላይ አትዋሹ። 15  ይህ ከላይ የሚመጣ ጥበብ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምድራዊ፣ እንስሳዊና አጋንንታዊ ነው። 16  ምክንያቱም ቅናትና ምቀኝነት ባለበት ሁሉ ብጥብጥና መጥፎ ነገር ሁሉ አለ። 17  ከላይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም በአድልዎ ሰዎችን የማይለያይና ግብዝነት የሌለበት ነው። 18  ከዚህም በላይ ሰላም ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች የጽድቅን ዘር ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ይዘሩና የጽድቅ ፍሬ ያጭዳሉ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ያዕ 3:6 * ከተጨማሪው መረጃ ላይ 9ኛውን ርዕስ ተመልከት።