በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

የሐዋርያት ሥራ 15:1-41

15  አንዳንድ ሰዎች ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ወርደው “በሙሴ ሥርዓት መሠረት ካልተገረዛችሁ በቀር ልትድኑ አትችሉም” እያሉ ወንድሞችን ያስተምሩ ጀመር።  ይህም ጳውሎስንና በርናባስን ከሰዎቹ ጋር ወደ ጦፈ ክርክርና ጭቅጭቅ በመራቸው ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም ከመካከላቸው አንዳንድ ወንድሞች ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ጉዳዩን በዚያ ለሚገኙት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እንዲያቀርቡ ተወሰነ።  በዚህም መሠረት ጉባኤው የተወሰነ መንገድ ከሸኛቸው በኋላ እግረ መንገዳቸውን በፊንቄና በሰማርያ በኩል በማለፍ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች ወደ አምላክ መመለሳቸውን በዝርዝር ተናገሩ፤ ወንድሞችንም ሁሉ እጅግ ደስ አሰኟቸው።  ኢየሩሳሌም ሲደርሱም በዚያ የሚገኘው ጉባኤ እንዲሁም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ጥሩ አቀባበል አደረጉላቸው፤ እነሱም አምላክ በእነሱ አማካኝነት ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች ተረኩላቸው።  ከፈሪሳውያን ሃይማኖታዊ ቡድን ያመኑ አንዳንድ ሰዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው “እነዚህን ሰዎች መግረዝና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ማዘዝ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ተናገሩ።  ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ይህን ጉዳይ ለመመርመር ተሰበሰቡ።  ከብዙ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነስቶ እንዲህ አላቸው:- “ወንድሞች፣ አሕዛብ የምሥራቹን ቃል ከእኔ አፍ ሰምተው እንዲያምኑ አምላክ ገና ከመጀመሪያው ከእናንተ መካከል እኔን እንደመረጠኝ በሚገባ ታውቃላችሁ፤  ልብን የሚያውቀው አምላክ ለእኛ እንዳደረገው ሁሉ ለእነሱም መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሠከረላቸው።  በእኛና በእነሱ መካከልም ምንም ልዩነት አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው የተነሳ ልባቸውን አነጻ። 10  ታዲያ አባቶቻችንም ሆኑ እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርቱ ጫንቃ ላይ በመጫን ለምን አሁን አምላክን ትፈታተናላችሁ? 11  በአንጻሩ ግን እኛ የምንድነው በጌታ ኢየሱስ ጸጋ አማካኝነት እንደሆነ እናምናለን፤ እነሱም ቢሆኑ ይህንኑ ያምናሉ።” 12  በዚህ ጊዜ የተሰበሰበው ሰው ሁሉ ጸጥ አለ፤ በርናባስና ጳውሎስ አምላክ በእነሱ አማካኝነት በአሕዛብ መካከል ያከናወናቸውን በርካታ ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሲናገሩም ያዳምጥ ጀመር። 13  እነሱ ተናግረው ካበቁ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰ:- “ወንድሞች፣ ስሙኝ። 14  አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ትኩረቱን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ወደ እነሱ እንዳዞረ ስምዖን በሚገባ ተርኳል። 15  እንዲህ ተብሎ የተጻፈው የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል:- 16  ‘ከዚህ በኋላ ተመልሼ የፈረሰውን የዳዊትን ዳስ ዳግመኛ እገነባለሁ፤ ፍርስራሹንም ዳግም በመገንባት እንደገና አቆመዋለሁ፤ 17  ይህንም የማደርገው የቀሩት ሰዎች በስሜ ከተጠሩት ይኸውም ከአሕዛብ ከመጡት ሰዎች ጋር አንድ ላይ ሆነው ይሖዋን ከልብ እንዲፈልጉ ነው በማለት እነዚህን ነገሮች የሚያከናውነው ይሖዋ ተናግሯል፤ 18  እነዚህንም ነገሮች ከጥንት ዘመን ጀምሮ ያውቃል።’ 19  ስለዚህ እንደኔ ከሆነ ወደ አምላክ እየተመለሱ ያሉትን አሕዛብ ባናስቸግራቸው ይሻላል፤ 20  ከዚህ ይልቅ በጣዖት ከረከሱ ነገሮች፣ ከዝሙት፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ እንዲሁም ከደም እንዲርቁ እንጻፍላቸው። 21  ምክንያቱም ከጥንት ዘመን ጀምሮ በየከተማው በሰንበት ቀናት ሁሉ በምኩራቦች ውስጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከሙሴ መጻሕፍት በማንበብ በውስጡ የሰፈረውን ቃል የሚሰብኩ ሰዎች ነበሩ።” 22  ከዚያም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከመላው ጉባኤ ጋር ሆነው ከመካከላቸው የተመረጡ ሰዎችን ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ለመላክ ወሰኑ፤ የተመረጡት ሰዎችም በወንድሞች መካከል ግንባር ቀደም የሆኑት በርስያን የሚባለው ይሁዳና ሲላስ ነበሩ፤ 23  በእነሱም እጅ የሚከተለውን ደብዳቤ ላኩ:- “ከወንድሞቻችሁ ከሐዋርያትና ከሽማግሌዎች፤ በአንጾኪያ፣ በሶርያና በኪልቅያ ለምትኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆናችሁ ወንድሞች፤ ሰላምታችን ይድረሳችሁ! 24  ከእኛ መካከል አንዳንዶች እኛ ምንም ሳናዛቸው በሚናገሩት ነገር እንዳስቸገሯችሁና እምነታችሁን ሊያናጉ እንደሞከሩ ስለሰማን 25  ሰዎች መርጠን ከተወደዱት ወንድሞቻችን ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር ወደ እናንተ ለመላክ በአንድ ልብ ወሰንን፤ 26  በርናባስና ጳውሎስ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ናቸው። 27  ስለዚህ ይህንኑ ነገር በቃልም እንዲነግሯችሁ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል። 28  ከሚከተሉት አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳንጭንባችሁ መንፈስ ቅዱስና እኛ ወስነናል፤ 29  ለጣዖት ከተሠዉ ነገሮች፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋና ከዝሙት ራቁ። ከእነዚህ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ከራቃችሁ መልካም ይሆንላችኋል። ደህና ሁኑ!” 30  የተላኩትም ሰዎች ከተሰናበቱ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ እዚያ የሚገኙትንም ሁሉ በአንድነት ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጧቸው። 31  እነሱም ካነበቡት በኋላ ባገኙት ማበረታቻ እጅግ ተደሰቱ። 32  ይሁዳና ሲላስም ራሳቸው ነቢያት ስለነበሩ ብዙ ቃል በመናገር ወንድሞችን አበረታቷቸው እንዲሁም አጠናከሯቸው። 33  በዚያም የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደ ላኳቸው ሰዎች እንዲመለሱ ወንድሞች በሰላም አሰናበቷቸው። 34*  —— 35  ይሁን እንጂ ጳውሎስና በርናባስ እያስተማሩና ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ሆነው የይሖዋን ቃል ምሥራች እየሰበኩ በአንጾኪያ ቆዩ። 36  ከተወሰኑ ቀናት በኋላም ጳውሎስ በርናባስን “የይሖዋን ቃል በሰበክንባቸው ከተሞች ሁሉ ያሉት ወንድሞች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ የግድ ተመልሰን ልንጎበኛቸው ይገባል” አለው። 37  በርናባስ፣ ማርቆስ ተብሎ የሚጠራው ዮሐንስ አብሯቸው እንዲሄድ ወስኖ ነበር። 38  ጳውሎስ ግን ማርቆስ ከጵንፍልያ ተለይቷቸው ስለነበረና ያከናውኑት ወደነበረው ሥራ አብሯቸው ስላልሄደ አሁን እሱን ይዞ መሄዱ ተገቢ መስሎ አልታየውም። 39  በዚህ ምክንያት በመካከላቸው ኃይለኛ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ ተለያዩ፤ ስለዚህ በርናባስ ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። 40  ጳውሎስ ደግሞ ሲላስን መረጠ፤ ወንድሞችም ለይሖዋ ጸጋ በአደራ ከሰጡት በኋላ ከዚያ ተነስቶ ሄደ። 41  ጉባኤዎችንም እያበረታታ በሶርያና በኪልቅያ አለፈ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ሥራ 15:34 ማቴዎስ 17:21 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።