በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

የሐዋርያት ሥራ 14:1-28

14  በኢቆንዮን ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁድ ምኩራብ ገቡ፤ በዚያም ጥሩ ንግግር ስለሰጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያንና ግሪካውያን አማኞች ሆኑ።  ሆኖም ያላመኑት አይሁዳውያን ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን ሰዎች በማነሳሳት በወንድሞች ላይ ጥላቻ እንዲያድርባቸው አደረጉ።  በመሆኑም በይሖዋ ሥልጣን በድፍረት እየተናገሩ በዚያ ረዘም ላለ ጊዜ ቆዩ፤ እሱም ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች በእነሱ እጅ እንዲከናወኑ በማድረግ ስለ ጸጋው የሚነገረው መልእክት ትክክል መሆኑን ያረጋግጥላቸው ነበር።  ይሁንና የከተማው ሕዝብ ለሁለት ተከፈለ፤ አንዳንዶቹ ከአይሁዳውያን ጎን ሲቆሙ ሌሎቹ ደግሞ ከሐዋርያት ጎን ቆሙ።  አሕዛብና አይሁዳውያን ከገዥዎቻቸው ጋር ሆነው ሊያንገላቷቸውና በድንጋይ ሊወግሯቸው ቆርጠው በተነሱ ጊዜ  ጳውሎስና በርናባስ ይህን ስላወቁ ልስጥራና ደርቤ ወደሚባሉት የሊቃኦንያ ከተሞች እንዲሁም በዙሪያቸው ወዳለው አገር ሸሹ፤  በዚያም ምሥራቹን ማወጃቸውን ቀጠሉ።  በልስጥራም እግሩ የሰለለ አንድ ሰው ተቀምጦ ነበር፤ እሱም ከእናቱ ማህፀን ጀምሮ ሽባ የነበረ ሲሆን ፈጽሞ በእግሩ ሄዶ አያውቅም።  ይህ ሰው ጳውሎስ ሲናገር ያዳምጥ ነበር፤ ጳውሎስም ትኩር ብሎ አየውና ለመዳን የሚያበቃ እምነት እንዳለው ተመልክቶ 10  ከፍ ባለ ድምፅ “ተነስና ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም” አለው። እሱም ዘሎ ተነሳና መራመድ ጀመረ። 11  ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “አማልክት በሰው አምሳል ሆነው ወደ እኛ ወርደዋል!” በማለት በሊቃኦንያ ቋንቋ ተናገሩ። 12  በርናባስን ዙስ፣ ጳውሎስን ደግሞ ዋና ተናጋሪ ስለነበር ሄርሜስ ብለው ይጠሯቸው ጀመር። 13  በከተማዋ ፊት ለፊት ያለው የዙስ ቤተ መቅደስ ካህን ኮርማዎችና የአበባ ጉንጉኖች ወደ ከተማዋ መግቢያ በማምጣት ከሕዝቡ ጋር ሆኖ መሥዋዕት ሊሠዋላቸው ፈለገ። 14  ይሁን እንጂ ሐዋርያቱ በርናባስና ጳውሎስ ይህን ሲሰሙ መደረቢያቸውን ቀደዱ፤ ሮጠውም ሕዝቡ መሃል በመግባት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው 15  እንዲህ አሉ:- “እናንተ ሰዎች፣ እንዲህ የምታደርጉት ለምንድን ነው? እኛም እንደ እናንተው ድክመት ያለብን ሰዎች ነን፤ ምሥራች እያወጅንላችሁ ያለነው እናንተም ይህን ከንቱ ነገር ትታችሁ ሰማይን፣ ምድርንና ባሕርን እንዲሁም በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ወደፈጠረው ሕያው አምላክ እንድትመለሱ ነው። 16  ባለፉት ትውልዶች ሕዝቦች ሁሉ በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ ፈቀደላቸው፤ 17  ይሁንና መልካም ነገሮች በማድረግ ለራሱ ምሥክር ከማቅረብ ወደኋላ አላለም፤ ከሰማይ ዝናብ በማዝነብ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት የተትረፈረፈ ምግብ ያቀርብላችኋል፣ ልባችሁንም በደስታ ይሞላዋል።” 18  ይህንንም ተናግረው ሕዝቡ እንዳይሠዋላቸው ያስጣሉት በብዙ ችግር ነበር። 19  ሆኖም አይሁዳውያን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጥተው ሕዝቡን አግባቡ፤ ጳውሎስንም በድንጋይ ከወገሩት በኋላ የሞተ መስሏቸው ጎትተው ከከተማዋ አወጡት። 20  ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በከበቡት ጊዜ ግን ተነስቶ ወደ ከተማይቱ ገባ። በማግስቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤ ሄደ። 21  በዚያች ከተማ ምሥራቹን ሰብከው በርካታ ደቀ መዛሙርት ካፈሩ በኋላ ወደ ልስጥራ፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ፤ 22  ደቀ መዛሙርቱን በማጠናከርና በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ በማበረታታት “ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ውስጥ ማለፍ አለብን” አሏቸው። 23  ከዚህም በተጨማሪ በየጉባኤው ሽማግሌዎችን ሾሙላቸው፤ ከጾሙና ከጸለዩም በኋላ ላመኑበት ለይሖዋ አደራ ሰጧቸው። 24  ከዚያም በጵስድያ በኩል አልፈው ወደ ጵንፍልያ መጡ፤ 25  በጴርጌ ቃሉን ከተናገሩ በኋላ ወደ አታሊያ ወረዱ። 26  ከዚያም ተነስተው በመርከብ ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ አንጾኪያ ጳውሎስና በርናባስ አሁን ሙሉ በሙሉ ያጠናቀቁትን ሥራ እንዲያከናውኑ ለአምላክ ጸጋ በአደራ የተሰጡባት ስፍራ ነበረች። 27  እዚያም ደርሰው ጉባኤውን አንድ ላይ ከሰበሰቡ በኋላ አምላክ በእነሱ አማካኝነት ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች እንዲሁም ለአሕዛብ የእምነትን በር እንደከፈተላቸው ይተርኩላቸው ጀመር። 28  በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ረዘም ያለ ጊዜ አሳለፉ።

የግርጌ ማስታወሻዎች