በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ዕብራውያን 1:1-14

1  በጥንት ዘመን በተለያዩ ጊዜያትና በብዙ መንገዶች በነቢያት አማካኝነት ለአባቶቻችን የተናገረው አምላክ  በእነዚህ ቀናት መጨረሻ የሁሉም ነገር ወራሽ አድርጎ በሾመውና የተለያዩ ሥርዓቶችን* በፈጠረበት ልጅ አማካኝነት ለእኛ ተናገረ።  እሱ የአምላክ ክብር ነጸብራቅና የማንነቱ ትክክለኛ አምሳያ ነው፤ እሱም በኃያል ቃሉ ሁሉም ነገር በሕልውና እንዲቀጥል ያደርጋል፤ እኛን ከኃጢአታችን የማንጻት ሥርዓት ከፈጸመ በኋላም ከፍ ባለ ስፍራ በግርማዊው ቀኝ ተቀምጧል።  ስለዚህ ከመላእክት እጅግ የላቀ ስም የወረሰ በመሆኑ ከእነሱ የተሻለ ሆኗል።  ለምሳሌ ያህል፣ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ” ደግሞም “እኔ ራሴ አባቱ እሆናለሁ፤ እሱ ራሱም ልጄ ይሆናል” ብሎ ከመላእክት መካከል ስለ የትኛው መልአክ ተናግሮ ያውቃል?  ሆኖም የበኩር ልጁን እንደገና ወደ ምድር የሚያመጣበትን ጊዜ በተመለከተ “የአምላክ መላእክት ሁሉ ይስገዱለት” ይላል።  በተጨማሪም ስለ መላእክት ሲናገር “መላእክቱንም መናፍስት፤ የሕዝብ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል ያደርጋል” ይላል።  ስለ ልጁ ሲናገር ግን እንዲህ ይላል:- “አምላክ ከዘላለም እስከ ዘላለም ዙፋንህ ነው፤ የመንግሥትህ በትርም የጽድቅ በትር ነው።  ጽድቅን ወደድክ፣ ዓመፅን ጠላህ። አምላክ ይኸውም አምላክህ ከመሰሎችህ ይበልጥ በደስታ ዘይት የቀባህ ለዚህ ነው።” 10  ደግሞም እንዲህ ይላል:- “ጌታ ሆይ፣ አንተ በመጀመሪያ የምድርን መሠረት ጣልክ፣ ሰማያትም የእጆችህ ሥራዎች ናቸው። 11  እነሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም ከላይ እንደሚደረብ ልብስ ያረጃሉ፤ 12  እንደ ካባ፣ ከላይ እንደሚደረብ ልብስም ትጠቀልላቸዋለህ፤ እነሱም ይለወጣሉ፣ አንተ ግን ያው ነህ፣ ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።” 13  ይሁንና “ጠላቶችህን ለእግርህ እንደ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” ብሎ ከመላእክት መካከል ስለ የትኛው መልአክ ተናግሮ ያውቃል? 14  ሁሉም መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ የሕዝብ አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት አይደሉም?

የግርጌ ማስታወሻዎች

ዕብ 1:2 * ወይም፣ “በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች።”