በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ኤፌሶን 4:1-32

4  እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንኩ እኔ ከተጠራችሁበት ጥሪ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤  በፍጹም ትሕትናና ገርነት፣ በትዕግሥት እንዲሁም እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ፤  አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።  በተጠራችሁ ጊዜ በአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤  አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት አለ፤  ደግሞም ከሁሉ በላይ የሆነ፣ በሁሉም አማካኝነት የሚሠራና በሁሉም ላይ የሚሠራ የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።  ደግሞም ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል፤ ይህንም የተቀበልነው ክርስቶስ ነፃ ስጦታውን በወሰነው መጠን መሠረት ነው።  ስለዚህ እንዲህ ይላል:- “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮኞችን ወሰደ፤ ወንዶችንም እንደ ስጦታ አድርጎ ሰጠ።”  ታዲያ “ወደ ላይ ወጣ” የሚለው አነጋገር ወደ ታች ይኸውም ወደ ምድር ወረደ ማለትም ካልሆነ በቀር ምን ማለት ነው? 10  ሁሉንም ነገር ወደ ሙላት ያደርስ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ያው ወደ ታች የወረደው ራሱ ነው። 11  እንዲሁም አንዳንዶቹን ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹን ነቢያት፣ አንዳንዶቹን ወንጌላውያን፣ አንዳንዶቹን ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች አድርጎ ሰጠ፤ 12  ይህንም ያደረገው ቅዱሳንን እንዲያስተካክሉ፣ ሌሎችን እንዲያገለግሉና የክርስቶስን አካል እንዲገነቡ ነው፤ 13  ይህም ሁላችንም በእምነትና ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም ወደሚገኘው አንድነት እንዲሁም ሙሉ ሰው ወደ መሆንና ክርስቶስ ወዳለበት የሙላት ደረጃ እስክንደርስ ነው። 14  በመሆኑም ከእንግዲህ ሕፃናት መሆን የለብንም፤ በማዕበል የምንነዳ ይመስል በማንኛውም የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎች የማታለያ ዘዴና በተንኮል በተወጠነ አሳሳች ሐሳብ የምንንገዋለልና ወዲያና ወዲህ የምንል መሆን የለብንም። 15  ከዚህ ይልቅ እውነትን በመናገር በሁሉም ነገር ወደ እሱ ይኸውም ራስ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ በፍቅር እንደግ። 16  እሱን መሠረት በማድረግ፣ የአካል ክፍሎች ሁሉ አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሚያሟላው በእያንዳንዱ መገጣጠሚያ አማካኝነት እርስ በርስ ተስማምተው እየተገጣጠሙና እያንዳንዱ የአካል ክፍል እንደ አቅሙ በሚያከናውነው የሥራ ድርሻ መሠረት እርስ በርስ ተደጋግፈው እየሠሩ፣ አካሉ እንዲያድግና በፍቅር ራሱን እንዲያንጽ ያደርጉታል። 17  ስለዚህ አሕዛብ በአእምሯቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ እናንተም ከእንግዲህ እንዳትመላለሱ በጌታ እናገራለሁ እንዲሁም እመሠክራለሁ፤ 18  እነሱ በውስጣቸው ካለው ድንቁርና የተነሳና ከልባቸው መደንደን የተነሳ አእምሯቸው ጨልሟል፤ እንዲሁም ከአምላክ ከሚገኘው ሕይወት ርቀዋል። 19  የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለደነዘዘ በስግብግብነት ማንኛውንም ዓይነት ርኩሰት ለመፈጸም ራሳቸውን ለብልግና* አሳልፈው ሰጥተዋል። 20  እናንተ ግን ክርስቶስን የተማራችሁት እንደዚህ አይደለም፤ 21  ከዚህ ይልቅ በኢየሱስ ውስጥ ካለው እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ እሱን ሰምታችሁታል፤ በእሱም አማካኝነት ተምራችኋል፤ 22  ስለዚህ ከቀድሞ አኗኗራችሁ ጋር የሚስማማውንና አታላይ በሆነው ምኞቱ እየተበላሸ የሚሄደውን አሮጌውን ስብዕናችሁን አውልቃችሁ መጣል አለባችሁ፤ 23  ይልቁንም አእምሯችሁን በሚያሠራው ኃይል እየታደሳችሁ መሄድ አለባችሁ፤ 24  እንዲሁም እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል። 25  ስለዚህ አሁን ውሸትን ስላስወገዳችሁ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ* ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ ምክንያቱም ሁላችንም የአንድ አካል ክፍሎች ነን። 26  ተቆጡ፤ ነገር ግን ኃጢአት አትሥሩ፤ ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ፤ 27  ዲያብሎስም ስፍራ እንዲያገኝ አትፍቀዱለት። 28  የሚሰርቅ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ከዚህ ይልቅ ለተቸገረ ሰው ሊሰጥ የሚችለው ነገር እንዲኖረው በእጆቹ መልካም ተግባር እያከናወነ በትጋት ይሥራ። 29  እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል ማንኛውም መልካም ቃል እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ። 30  በተጨማሪም በቤዛው ነፃ ለምትወጡበት ቀን የታተማችሁበትን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑ። 31  የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ መካከል ይወገድ። 32  ይልቁንም አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ኤፌ 4:19 ገላትያ 5:19 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ኤፌ 4:25 * “ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።