በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ--አዲስ ዓለም ትርጉም በ2013 ተሻሽሎ የወጣውን ተመልከት

ቲቶ 3:1-15

3  ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት እንዲገዙና እንዲታዘዙ እንዲሁም ለመልካም ሥራ ሁሉ ዝግጁዎች እንዲሆኑ ማሳሰብህን ቀጥል፤  ስለ ማንም ክፉ ነገር እንዳይናገሩ፣ ጠበኞች እንዳይሆኑ፣ ምክንያታዊ እንዲሆኑና ለሰው ሁሉ ገርነትን ሁሉ እንዲያሳዩ አሳስባቸው።  ምክንያቱም እኛ ራሳችን በአንድ ወቅት የማናመዛዝን፣ የማንታዘዝ፣ የምንታለል፣ ለተለያየ ምኞትና ሥጋዊ ደስታ የምንገዛ፣ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፣ የተጠላንና እርስ በርስ የምንጠላላ ነበርን።  ይሁን እንጂ አዳኛችን የሆነው አምላክ ለሰው ያለው ደግነትና ፍቅር በተገለጠ ጊዜ  እኛ በሠራነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን ወደ ሕይወት እንድንመጣ በማጠብና በመንፈስ ቅዱስ እኛን አዲስ በማድረግ በምሕረቱ አዳነን።  ይህን መንፈስ አዳኛችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በእኛ ላይ አትረፍርፎ አፈሰሰው፤  ይህንም ያደረገው በእሱ ጸጋ አማካኝነት ጻድቃን ተብለን ከተጠራን በኋላ ከዘላለም ሕይወት ተስፋ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ወራሾች እንድንሆን ነው።  ይህ ቃል የታመነ ነው፤ በአምላክ ያመኑ ሁሉ አእምሯቸውን ሁልጊዜ በመልካም ሥራዎች ማስጠመድ ይችሉ ዘንድ እነዚህን ነገሮች በተመለከተ ዘወትር አስረግጠህ እንድትናገር እፈልጋለሁ። እነዚህ ነገሮች መልካምና ለሰዎች ጠቃሚ ናቸው።  ሆኖም ሞኝነት ከሚንጸባረቅባቸው ጥያቄዎች፣ ከትውልድ ሐረግ ቆጠራ፣ ከጭቅጭቅና ሕጉን በተመለከተ ከሚነሳ ጠብ ራቅ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ምንም የማይጠቅሙና ከንቱዎች ናቸው። 10  ኑፋቄ የሚያስፋፋን ሰው በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜና ለሁለተኛ ጊዜ ከመከርከው በኋላ ከእሱ ራቅ፤ 11  እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከመንገድ የወጣና ኃጢአት እየሠራ ያለ እንዲሁም በራሱ ላይ እየፈረደ ያለ መሆኑን እወቅ። 12  አርጤማስን ወይም ቲኪቆስን ወደ አንተ ስልክ እኔ ወዳለሁበት ወደ ኒቆጶሊስ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ ምክንያቱም ክረምቱን በዚያ ለማሳለፍ ወስኛለሁ። 13  ሕጉን ጠንቅቆ የሚያውቀው ዜናስና አጵሎስ ምንም ነገር እንዳይጎድልባቸው ለጉዟቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር በሚገባ አሟላላቸው። 14  ይሁን እንጂ በጣም የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት እንዲችሉና ፍሬ ቢሶች እንዳይሆኑ የእኛም ሰዎች በመልካም ሥራ መጠመድን ይማሩ። 15  አብረውኝ ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ለእምነት ወዳጆቻችን ሰላምታ አቅርብልኝ። የአምላክ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻዎች