በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ--አዲስ ዓለም ትርጉም በ2013 ተሻሽሎ የወጣውን ተመልከት

ሮም 16:1-27

16  በክንክራኦስ ጉባኤ የምታገለግለውን እህታችንን ፌበንን ላስተዋውቃችሁ እወዳለሁ፤  ለቅዱሳን በሚገባ ሁኔታ በጌታ እንድትቀበሏትና ከእናንተ የምትፈልገውን ማንኛውንም ነገር በማድረግ እንድትረዷት እለምናችኋለሁ፤ ምክንያቱም እሷ ራሷ ለብዙዎች፣ ለእኔም ጭምር ከለላ ሆናለች።  በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩ ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤  እነሱ ስለ ነፍሴ ሲሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠዋል፤ እኔ ብቻ ሳልሆን የአሕዛብ ጉባኤዎችም ሁሉ ያመሰግኗቸዋል፤  በቤታቸው ላለው ጉባኤ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በእስያ ከመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ተከታዮች አንዱ የሆነውን የምወደውን ኤጲኔጦስን ሰላም በሉልኝ።  ለእናንተ ብዙ የደከመችውን ማርያምን ሰላም በሉልኝ።  ዘመዶቼ የሆኑትንና አብረውኝ የታሰሩትን እንዲሁም በሐዋርያት ዘንድ መልካም ስም ያተረፉትንና ከእኔ ቀደም ብለው የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑትን አንድሮኒኮስንና ዩኒያስን ሰላም በሉልኝ።  በጌታ ለምወደው ለአምጵልያጦስ ሰላምታዬን አቅርቡልኝ።  በክርስቶስ አብሮን የሚሠራውን ኡርባኖስንና የምወደውን እስጣኩስን ሰላም በሉልኝ። 10  በክርስቶስ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን አጵሌስን ሰላም በሉልኝ። ለአርስጦቡሉስ ቤተሰብ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 11  ዘመዴ የሆነውን ሄሮድዮንን ሰላም በሉልኝ። በጌታ የሆኑትን የናርኪሰስ ቤተሰቦች ሰላም በሉልኝ። 12  በጌታ ሆነው በትጋት የሚሠሩትን ጥራይፊናና ጥራይፎሳ የተባሉትን ሴቶች ሰላም በሉልኝ። በጌታ ሥራ ብዙ የደከመችውን የምንወዳትን ጰርሲስን ሰላም በሉልኝ። 13  በጌታ ሆኖ ለተመረጠው ለሩፎስ እንዲሁም ለእኔም እናት ለሆነችው ለእናቱ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 14  አሲንክሪጦስን፣ ፍሌጎንን፣ ሄርሜስን፣ ጳጥሮባን፣ ሄርማስንና ከእነሱ ጋር ያሉትን ወንድሞች ሰላም በሉልኝ። 15  ፊሎሎጎስንና ዩልያን፣ ኔርዩስንና እህቱን፣ ኦሊምጳስን እንዲሁም ከእነሱ ጋር ያሉትን ቅዱሳን ሁሉ ሰላም በሉልኝ። 16  እርስ በርሳችሁ በተቀደሰ መሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ። የክርስቶስ ጉባኤዎች በሙሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 17  እንግዲህ ወንድሞች፣ የተማራችሁትን ትምህርት በመጻረር ክፍፍል ከሚፈጥሩና ለእንቅፋት ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን ከሚያመጡ ሰዎች እንድትጠነቀቁ አሳስባችኋለሁ፤ ከእነሱ ራቁ። 18  እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ለጌታችን ለክርስቶስ ሳይሆን ለገዛ ሆዳቸው ባሪያዎች ናቸው፤ በለሰለሰ አንደበትና በሽንገላ ቃላት የየዋሆችን ልብ ያታልላሉ። 19  ታዛዥነታችሁ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ሆኗል። ስለዚህ እኔ በእናንተ እጅግ እደሰታለሁ። ይሁንና ለመልካም ነገር ጥበበኞች እንድትሆኑ፣ ለክፉ ነገር ደግሞ አላዋቂዎች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። 20  ሰላም የሚሰጠው አምላክ ግን በበኩሉ በቅርብ ጊዜ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ይጨፈልቀዋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። 21  የሥራ አጋሬ ጢሞቴዎስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ ዘመዶቼ የሆኑት ሉክዮስ፣ ያሶንና ሶሲጳጥሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 22  ይህን ደብዳቤ በጽሑፍ ያሰፈርኩት እኔ ጤርጥዮስም በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ። 23  እኔንም ሆነ መላውን ጉባኤ የሚያስተናግደው ጋይዮስ ሰላም ይላችኋል። የከተማይቱ የግምጃ ቤት ሹም ኤርስጦስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ ወንድሙ ቁአስጥሮስም ሰላም ይላችኋል። 24*  —— 25  አምላክ ለረጅም ዘመናት ተሰውሮ ከቆየው ቅዱስ ሚስጥር መገለጥ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እኔ በማውጀው ምሥራችና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚሰበከው መልእክት መሠረት ሊያጸናችሁ ይችላል፤ 26  አሁን ግን ሕዝቦች ሁሉ እምነት እንዲኖራቸውና እሱን እንዲታዘዙ ቅዱሱ ሚስጥር በዘላለማዊው አምላክ ትእዛዝ መሠረት ትንቢታዊ በሆኑ ቅዱሳን መጻሕፍት አማካኝነት በሕዝቦች ሁሉ መካከል እንዲገለጥና እንዲታወቅ ተደርጓል፤ 27  እሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ሮም 16:24 * እጅግ ጥንታዊ የሆኑት በእጅ የተጻፉ የግሪክኛ ቅጂዎች በቁጥር 20 መጨረሻ ላይ ካለው ሐሳብ ጋር የሚመሳሰሉትን “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን” የሚሉትን ቃላት አያካትቱም።