በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ሮም 12:1-21

12  እንግዲህ ወንድሞች፣ ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ እንድታቀርቡ በአምላክ ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው።  በተጨማሪም የዚህን ሥርዓት የአኗኗር ዘይቤ መኮረጅ አቁሙ፤ ከዚህ ይልቅ ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።  እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእያንዳንዱ በሰጠው እምነት መጠን ጤናማ አእምሮ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ በተሰጠኝ ጸጋ መሠረት በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው እመክራለሁ።  በአንድ አካል ላይ ብዙ የአካል ክፍሎች አሉን፤ ይሁንና ሁሉም የአካል ክፍሎች አንድ ዓይነት ተግባር አያከናውኑም፤  ልክ እንደዚሁ እኛም ብዙ ብንሆንም እንኳ ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት አንድ አካል ነን፤ እርስ በርሳችንም አንዳችን የሌላው የአካል ክፍል ነን።  በመሆኑም በተሰጠን ጸጋ መሠረት የተለያዩ ስጦታዎች ስላሉን ስጦታችን ትንቢት መናገር ከሆነ በተሰጠን እምነት መሠረት ትንቢት እንናገር፤  ማገልገል ከሆነ ማገልገላችንን እንቀጥል፤ የሚያስተምርም ቢሆን ማስተማሩን ይቀጥል፤  የሚመክርም ቢሆን መምከሩን ይቀጥል፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚያስተዳድር በትጋት ያስተዳድር፤ የሚምር በደስታ ይማር።  ፍቅራችሁ ግብዝነት የሌለበት ይሁን። ክፉ የሆነውን ነገር ተጸየፉ፤ ጥሩ የሆነውን ነገር አጥብቃችሁ ያዙ። 10  በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ። 11  በሥራችሁ አትለግሙ። በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ። ይሖዋን እንደ ባሪያ አገልግሉ። 12  በተስፋው ደስ ይበላችሁ። መከራን በጽናት ተቋቋሙ። በጽናት ጸልዩ። 13  ለቅዱሳን እንደየችግራቸው ያላችሁን አካፍሉ። የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል አዳብሩ። 14  ስደት የሚያደርሱባችሁን መባረካችሁን ቀጥሉ፤ ባርኩ እንጂ አትርገሙ። 15  ደስ ከተሰኙ ሰዎች ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱ ሰዎች ጋር አልቅሱ። 16  ለራሳችሁ ያላችሁ ዓይነት አመለካከት ለሌሎችም ይኑራችሁ፤ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ አትመልከቱ፤ ትሕትና የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ ይኑራችሁ። ራሳችሁን ልባሞች አድርጋችሁ አትቁጠሩ። 17  ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አድርጉ። 18  ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። 19  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ይላል ይሖዋ” ተብሎ ስለተጻፈ ለአምላክ ቁጣ ዕድል ስጡ። 20  ነገር ግን “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ የሚጠጣ ነገር ስጠው፤ ይህን በማድረግ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ።” 21  በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።

የግርጌ ማስታወሻዎች