በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ--አዲስ ዓለም ትርጉም በ2013 ተሻሽሎ የወጣውን ተመልከት

ሮም 11:1-36

11  እንግዲያው አምላክ ሕዝቡን ትቷል ማለት ነው? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በፍጹም! ምክንያቱም እኔም ራሴ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከአብርሃም ዘር የሆንኩ የቢንያም ነገድ ነኝ።  አምላክ መጀመሪያ እውቅና የሰጣቸውን ሰዎች አልተዋቸውም። ደግሞስ ቅዱስ መጽሐፉ ኤልያስ እስራኤልን በአምላክ ፊት በከሰሰበት ጊዜ የሆነውን ነገር በተመለከተ ምን እንደሚል አታውቁም?  “ይሖዋ ሆይ፣ ነቢያትህን ገድለዋል፤ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋል፤ እኔ ብቻ ቀረሁ፤ ነፍሴንም ይፈልጓታል።”  ይሁንና አምላክ የሰጠው መልስ ምን ነበር? “ለበኣል ያልተንበረከኩ ሰባት ሺህ ሰዎች ለራሴ አስቀርቻለሁ።”  ስለዚህ በዚህ መንገድ በአሁኑ ዘመንም በጸጋ ተመርጠው የተገኙ ቀሪዎች አሉ።  የተመረጡት በጸጋ ከሆነ በሥራ መሆኑ ቀርቷል፤ አለዚያ ጸጋው ጸጋ መሆኑ በቀረ ነበር።  እንግዲህ ምን ማለት እንችላለን? እስራኤል አጥብቆ ይፈልገው የነበረውን ነገር አላገኘም፤ የተመረጡት ግን አገኙት። የቀሩት ልባቸው ደነደነ፤  ይህም “አምላክ እስከ ዛሬ ድረስ ከባድ መንፈሳዊ እንቅልፍ ጣለባቸው፤ እንዳያዩ ዓይን ሰጣቸው፤ እንዳይሰሙም ጆሮ ሰጣቸው” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።  በተጨማሪም ዳዊት እንዲህ ብሏል:- “ማዕዳቸው ወጥመድና አሽክላ እንዲሁም እንቅፋትና ቅጣት ይሁንባቸው፤ 10  እንዳያዩ ዓይኖቻቸው ይጨልሙ፤ ጀርባቸውም ዘወትር ይጉበጥ።” 11  እንግዲያው የተሰናከሉት ሙሉ በሙሉ ወድቀው እንዲቀሩ ነው? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በፍጹም! ከዚህ ይልቅ እነሱ ሕጉን በመተላለፋቸው ለአሕዛብ የመዳን መንገድ ተከፈተ፤ ይህም የሆነው እነሱን ለማስቀናት ነው። 12  እነሱ ሕጉን መተላለፋቸው ለዓለም በረከት ከሆነና የእነሱ ማነስ ለአሕዛብ በረከት ካስገኘ ቁጥራቸው መሙላቱማ ምን ያህል ታላቅ በረከት ያስገኝ ይሆን! 13  አሁን ደግሞ የምናገረው ከአሕዛብ ወገን ለሆናችሁት ነው። የአሕዛብ ሐዋርያ እንደመሆኔ መጠን አገልግሎቴን አከብራለሁ፤ 14  ይህንም የማደርገው ሥጋዬ የሆኑትን በማስቀናት ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹን ማዳን እችል እንደሆነ ብዬ ነው። 15  የእነሱ መጣል ለዓለም እርቅ ካስገኘ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት ወደ ሕይወት መሻገር ማለት አይሆንም? 16  በተጨማሪም በኩራት ተደርጎ የተወሰደ የሊጡ ክፍል ቅዱስ ከሆነ ሊጡ በሙሉ ቅዱስ ነው፤ እንዲሁም ሥሩ ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹም ቅዱሳን ናቸው። 17  ይሁን እንጂ ከቅርንጫፎቹ መካከል አንዳንዶቹ ቢሰበሩና አንተ የዱር ወይራ ሆነህ ሳለህ በእነሱ መካከል ከተጣበቅክ እንዲሁም ከወይራው ዛፍ ሥር ከሚገኘው በረከት ተካፋይ ከሆንክ 18  በቅርንጫፎቹ ላይ አትኩራራ። በእነሱ ላይ የምትኩራራ ከሆነ ግን አንተን የተሸከመህ ሥሩ ነው እንጂ አንተ ሥሩን እንዳልተሸከምከው አስታውስ። 19  ይሁንና “ቅርንጫፎቹ የተሰበሩት እኔ በቦታቸው እንድጣበቅ ነው” ትል ይሆናል። 20  መልካም! እነሱ እምነት በማጣታቸው ተሰብረዋል፤ አንተ ግን በእምነት ቆመሃል። መፍራት እንጂ መታበይ አይገባህም። 21  ምክንያቱም አምላክ በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራ ለአንተም አይራራም። 22  ስለዚህ የአምላክን ደግነትና ጥብቅነት ተመልከት። በወደቁት ላይ ጥብቅ ይሆናል፤ አንተ ግን የአምላክ ደግነት የሚገባህ ሆነህ እስከተገኘህ ድረስ ደግነቱን ያሳይሃል፤ አለዚያ ግን አንተም ተቆርጠህ ትጣላለህ። 23  እነሱም ቢሆኑ እምነት የለሽ ሆነው በዚያው ካልቀጠሉ ተመልሰው ይጣበቃሉ፤ ምክንያቱም አምላክ ዳግመኛ ሊያጣብቃቸው ይችላል። 24  አንተ በተፈጥሮ የዱር ከሆነው የወይራ ዛፍ ተቆርጠህ ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ መንገድ በጓሮ የወይራ ዛፍ ላይ መጣበቅ ከቻልክ እነዚህ ተፈጥሯዊ የሆኑት ቅርንጫፎችማ በራሳቸው የወይራ ዛፍ ላይ መጣበቅ እንደሚችሉ የታወቀ ነው! 25  ወንድሞች፣ በራሳችሁ ዓይን ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ቅዱስ ሚስጥር ሳታውቁ እንድትቀሩ አልፈልግም:- የአሕዛብ ቁጥር እስኪሞላ ድረስ ከእስራኤላውያን መካከል ከፊሉ ደንዝዘዋል፤ 26  በዚህም መንገድ እስራኤል ሁሉ ይድናል። ይህም እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው ነው:- “አዳኝ ከጽዮን ይወጣል፤ የያዕቆብም ዘሮች የክፋት ድርጊታቸውን እንዲተዉ ያደርጋል። 27  ኃጢአታቸውን በማስወግድበት ጊዜ ከእነሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳንም ይህ ነው።” 28  እርግጥ ከምሥራቹ ጋር በተያያዘ ለእናንተ ጥቅም ሲባል የአምላክ ጠላቶች ናቸው፤ በአምላክ ምርጫ መሠረት ግን ለአባቶቻቸው ሲባል በአምላክ ዘንድ የተወደዱ ናቸው። 29  አምላክ በስጦታውና በጥሪው አይጸጸትምና። 30  በአንድ ወቅት እናንተ አምላክን የማትታዘዙ የነበረ ቢሆንም በእነሱ አለመታዘዝ ምክንያት አሁን ምሕረት እንዳገኛችሁ ሁሉ 31  አሁን ደግሞ እነሱ ራሳቸው ምሕረት ያገኙ ዘንድ አምላክን የማይታዘዙ ሆነዋል፤ ይህም ለእናንተ ምሕረት አስገኝቷል። 32  አምላክ ለሁሉም ምሕረት ያሳይ ዘንድ ሁሉም ያለመታዘዝ እስረኞች እንዲሆኑ ፈቅዷል። 33  የአምላክ ብልጽግናና ጥበብ እንዲሁም እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው! 34  ምክንያቱም “የይሖዋን ሐሳብ ማወቅ የቻለ ማን ነው? አማካሪውስ የሆነ ማን ነው?” 35  ወይስ “መልሶ ይከፍለው ዘንድ ለእሱ ያበደረ ማን ነው?” 36  ምክንያቱም ሁሉም ነገር የተገኘው ከእሱ፣ በእሱና ለእሱ ነው። ለዘላለም ክብር ለእሱ ይሁን። አሜን።

የግርጌ ማስታወሻዎች