በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ማቴዎስ 21:1-46

21  ወደ ኢየሩሳሌም በተቃረቡና በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደምትገኘው ወደ ቤተፋጌ በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ ሁለት ደቀ መዛሙርት ላከ፤  እንዲህም አላቸው:- “ወደዚያ ወደምታዩት መንደር ሂዱ፣ እዚያ እንደደረሳችሁም አንዲት የታሰረች አህያ ከነውርንጭላዋ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወደ እኔ አምጧቸው።  ማንም ሰው ቢጠይቃችሁ ‘ጌታ ይፈልጋቸዋል’ በሉት። በዚህ ጊዜ ወዲያውኑ ይልካቸዋል።”  ይህ የሆነውም በነቢዩ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው:-  “ለጽዮን ልጅ እንዲህ በሏት፣ ‘እነሆ ንጉሥሽ ገር ሆኖ በአህያይቱና የጭነት ከብት ግልገል በሆነው በውርንጭላው ላይ ተቀምጦ ይመጣል።’”  ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ።  አህያይቱንና ውርንጭላዋን አምጥተው መደረቢያቸውን በላያቸው ላይ አደረጉ፤ እሱም ተቀመጠባቸው።  ከሕዝቡ መካከል አብዛኞቹ መደረቢያቸውን በመንገዱ ላይ አነጠፉ፣ ሌሎች ደግሞ ከዛፎች ላይ ቅርንጫፎች እየቆረጡ በመንገዱ ላይ ያነጥፉ ጀመር።  ከፊት ከፊቱ የሚሄደውና ከኋላው የሚከተለው ሕዝብ “የዳዊትን ልጅ እባክህ አድነው! በይሖዋ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! በሰማይ የምትኖረው ሆይ፣ እባክህ አድነው!” ብሎ ይጮኽ ነበር። 10  ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ “ይህ ሰው ማን ነው?” በማለት መላ ከተማዋ ተናወጠች። 11  ሕዝቡም “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው!” እያለ ይናገር ነበር። 12  ኢየሱስም ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቶ በቤተ መቅደሱ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን መቀመጫዎችም ገለባበጠ። 13  እንዲህም አላቸው:- “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ እያደረጋችሁት ነው።” 14  ቤተ መቅደሱ ውስጥ እንዳለም ዓይነ ስውሮችና አንካሶች ወደ እሱ መጡ፤ እሱም ፈወሳቸው። 15  የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ያደረጋቸውን አስደናቂ ነገሮች እንዲሁም በቤተ መቅደሱ ውስጥ “የዳዊትን ልጅ እባክህ አድነው!” እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ ተቆጥተው 16  “እነዚህ የሚሉትን ትሰማለህ?” አሉት። ኢየሱስም “አዎ እሰማለሁ። ‘ከሕፃናትና ከሚጠቡ አፍ ምስጋና አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁም?” አላቸው። 17  ከዚያም ትቷቸው ከከተማዋ ከወጣ በኋላ ወደ ቢታንያ ሄደ፤ እዚያም አደረ። 18  በማለዳም ወደ ከተማዋ እየተመለሰ ሳለ ተራበ። 19  በመንገድ ዳርም አንድ የበለስ ዛፍ አየና ወደ እሷ ሄደ፤ ሆኖም ከቅጠል በቀር ምንም ስላላገኘባት “ከእንግዲህ ለዘላለም ፍሬ አይገኝብሽ” አላት። የበለስ ዛፏም ወዲያውኑ ደረቀች። 20  ደቀ መዛሙርቱ ግን ይህን ባዩ ጊዜ ተገርመው “የበለስ ዛፏ እንዲህ በአንዴ ልትደርቅ የቻለችው እንዴት ነው?” አሉ። 21  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው:- “እውነት እላችኋለሁ፣ እምነት ካላችሁና ካልተጠራጠራችሁ እኔ በበለስ ዛፏ ላይ ያደረግሁትን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት ይሆንላችኋል። 22  እምነት ካላችሁ በጸሎት የምትጠይቁትን ነገር ሁሉ ታገኛላችሁ።” 23  ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ እያስተማረ ሳለ የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ወደ እሱ መጥተው “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ይህን ሥልጣን የሰጠህስ ማን ነው?” አሉት። 24  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው:- “እኔም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ። መልሱን ከነገራችሁኝ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፤ 25  የዮሐንስ ጥምቀት ምንጩ ከየት ነው? ከሰማይ ወይስ ከሰው?” እነሱ ግን እርስ በርሳቸው እንዲህ ይባባሉ ጀመር:- “‘ከሰማይ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ 26  ‘ከሰው’ ብንል ደግሞ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ስለሚያየው ሕዝቡን እንፈራለን።” 27  ስለዚህ ለኢየሱስ “አናውቅም” ብለው መለሱለት። እሱ ደግሞ እንዲህ አላቸው:- “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም። 28  “እስቲ ምን ትላላችሁ? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ወደ መጀመሪያው ሄዶ ‘ልጄ ሆይ፣ ዛሬ ወደ ወይኑ እርሻ ሄደህ ሥራ’ አለው። 29  ልጁም መልሶ ‘እሺ አባዬ፣ እሄዳለሁ’ አለው፤ ግን አልሄደም። 30  ሁለተኛውንም ቀርቦ እንደዚሁ አለው። ልጁም መልሶ ‘አልሄድም’ አለው። በኋላ ግን ጸጸተውና ሄደ። 31  ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነሱም “ሁለተኛው” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ጋለሞቶች ወደ አምላክ መንግሥት በመግባት ረገድ እየቀደሟችሁ ነው። 32  ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ መጣ እናንተ ግን አላመናችሁትም። ይሁን እንጂ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ጋለሞቶች አመኑት፤ እናንተ ይህን ካያችሁ በኋላ እንኳ ጸጸት ተሰምቷችሁ እሱን ለማመን አልፈለጋችሁም። 33  “ሌላም ምሳሌ ስሙ:- የወይን እርሻ ያለማ አንድ ሰው ነበር፤ እርሻውንም ዙሪያውን አጠረው፣ በዚያም የወይን መጭመቂያ ቆፈረ እንዲሁም ማማ ሠራ፤ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። 34  ፍሬው የሚሰበሰብበት ወቅት ሲደርስ ድርሻውን እንዲያመጡለት ባሪያዎቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። 35  ገበሬዎቹ ግን ባሪያዎቹን ወስደው አንዱን ደበደቡት፣ ሌላውን ገደሉት፣ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። 36  ከበፊቶቹ የሚበዙ ሌሎች ባሪያዎች በድጋሚ ላከ፤ ይሁንና እነዚህንም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። 37  በመጨረሻም ‘መቼም ልጄን ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከው። 38  ገበሬዎቹ ልጁን ሲያዩት እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው። ኑ እንግደለው፣ ርስቱንም እንውረስ!’ ተባባሉ። 39  ስለዚህ ያዙትና ከወይኑ እርሻ አውጥተው ገደሉት። 40  እንግዲህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ሲመጣ እነዚህን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?” 41  እነሱም “ክፉዎች ስለሆኑ የከፋ ጥፋት ያደርስባቸዋል፤ ከዚያም የወይን እርሻውን ፍሬውን በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት። 42  ኢየሱስም እንዲህ አላቸው:- “በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ‘የማዕዘን ራስ ድንጋይ* የሆነው ግንበኞች የናቁት ድንጋይ ነው። ይህ የይሖዋ ሥራ ነው፤ ይህም ለዓይናችን ድንቅ ነው’ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁም? 43  የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል የምላችሁ ለዚህ ነው። 44  በተጨማሪም በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል። ድንጋዩ የሚወድቅበት ሰው ሁሉ ደግሞ ይደቅቃል።” 45  የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ ስለ እነሱ እንደተናገረ ገባቸው። 46  ምንም እንኳ ሊይዙት ይፈልጉ የነበረ ቢሆንም ሕዝቡ እንደ ነቢይ ያየው ስለነበር ሕዝቡን ፈሩ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ማቴ 21:42 * እዚህ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል ሁለት የሕንፃ ግድግዳዎች የሚገናኙበት ማዕዘን አናት ላይ የሚቀመጥ ድንጋይን ያመለክታል።