በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ማቴዎስ 16:1-28

16  ከዚያም ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ እሱ መጡ፤ ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት።  እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው:- “[ሲመሽ ‘ሰማዩ ስለ ቀላ ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤  ጠዋት ላይ ደግሞ ‘ሰማዩ ቢቀላም ዳመና ስለሆነ ዛሬ ብርድ ይሆናል፣ ዝናብም ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን መልክ በማየት መተርጎም ትችላላችሁ፤ የዘመኑን ምልክት ግን መተርጎም አትችሉም።]*  ክፉና አመንዝራ* ትውልድ ሁልጊዜ ምልክት ማየት ይፈልጋል፤ ሆኖም ከዮናስ ምልክት በስተቀር ምንም ምልክት አይሰጠውም።” ይህን ከተናገረ በኋላ ትቷቸው ሄደ።  ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕሩ ማዶ ተሻገሩ፤ በዚህ ጊዜ ዳቦ መያዝ ረስተው ነበር።  ኢየሱስ “ተጠንቀቁ፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው።  እነሱም እርስ በርሳቸው “ዳቦ ስላልያዝን ይሆናል” ይባባሉ ጀመር።  ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው:- “እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ ዳቦ ስላልያዝን ነው ብላችሁ ለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ?  አሁንም ነጥቡ አልገባችሁም? ወይስ አምስቱ ዳቦ ለአምስት ሺህዎቹ ሰዎች በቅቶ ከዚያ የተረፈውን ምን ያህል ቅርጫት እንዳነሳችሁ አታስታውሱም? 10  ወይስ ሰባቱ ዳቦ ለአራት ሺህዎቹ ሰዎች በቅቶ ከዚያ የተረፈውን በትላልቅ ቅርጫት ምን ያህል እንዳነሳችሁ ትዝ አይላችሁም? 11  ታዲያ የነገርኳችሁ ስለ ዳቦ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? እንግዲህ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።” 12  በዚህ ጊዜ ተጠንቀቁ ያላቸው ከዳቦ እርሾ ሳይሆን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንደሆነ ገባቸው። 13  ኢየሱስ ወደ ቂሳርያ ፊልጵስዩስ አካባቢ በመጣ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ነው ይሉታል?” ሲል ጠየቃቸው። 14  እነሱም “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት። 15  እሱም “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። 16  ስምዖን ጴጥሮስም “አንተ መሲሑ፣ የሕያው አምላክ ልጅ ነህ” ብሎ መለሰለት። 17  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው:- “የዮናስ ልጅ ስምዖን፣ ይህን የገለጠልህ ሥጋና ደም ሳይሆን በሰማያት ያለው አባቴ ስለሆነ የተባረክ ነህ። 18  ደግሞም እልሃለሁ፣ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚች ዐለት ላይ ጉባኤዬን እገነባለሁ፤ የሔዲስ* በሮችም አያሸንፏትም። 19  የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ እንዲሁም በምድር የምትፈታው ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” 20  ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን መሲሑ እሱ መሆኑን ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አዘዛቸው። 21  ከዚያን ጊዜ አንስቶ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንዳለበት እንዲሁም ሽማግሌዎች፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ብዙ መከራ እንደሚያደርሱበትና እንደሚገደል ብሎም በሦስተኛው ቀን እንደሚነሳ ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጽላቸው ጀመር። 22  በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ለብቻው ገለል አድርጎ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” እያለ ይገሥጸው ጀመር። 23  እሱ ግን ጀርባውን በመስጠት ጴጥሮስን “ከአጠገቤ ራቅ፣ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ ስለማታስብ እንቅፋት ሆነህብኛል” አለው። 24  ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው:- “ሊከተለኝ የሚፈልግ ካለ ራሱን ይካድ፣ የራሱን የመከራ እንጨት* ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ። 25  ምክንያቱም ነፍሱን ማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ለእኔ ሲል ነፍሱን የሚያጣ ግን ያገኛታል። 26  አንድ ሰው ዓለሙን ሁሉ የራሱ ቢያደርግ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ለነፍሱ ምትክ የሚሆን ምን ነገር ሊሰጥ ይችላል? 27  የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣል፤ ከዚያም ለእያንዳንዱ እንደ ምግባሩ ይከፍለዋል። 28  እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት መካከል አንዳንዶች የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ፈጽሞ ሞትን አይቀምሱም።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ማቴ 16:3 * ይህ ሐሳብ በቅንፍ ውስጥ የተቀመጠው በእጅ በተጻፉ አንዳንድ የጥንት ቅጂዎች ውስጥ የማይገኝ መሆኑን ለማመልከት ነው፤ ሆኖም በአንዳንዶቹ ውስጥ ይገኛል።
ማቴ 16:4 * ወይም፣ “ለአምላክ ታማኝ ያልሆነ።”
ማቴ 16:18 * ከተጨማሪው መረጃ ላይ 8ኛውን ርዕስ ተመልከት።
ማቴ 16:24 * ከተጨማሪው መረጃ ላይ 6ኛውን ርዕስ ተመልከት።