በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ--አዲስ ዓለም ትርጉም በ2013 ተሻሽሎ የወጣውን ተመልከት

ማርቆስ 10:1-52

10  ከዚያም ተነስቶ ወደ ይሁዳ የድንበር አካባቢዎችና ወደ ዮርዳኖስ ማዶ መጣ፤ ብዙ ሰዎችም እንደገና ወደ እሱ ተሰበሰቡ፤ አሁንም እንደ ልማዱ ያስተምራቸው ጀመር።  በዚህ ጊዜ ፈሪሳውያን ቀርበው እሱን ለመፈተን፣ አንድ ሰው ሚስቱን እንዲፈታ ሕግ ይፈቅድለት እንደሆነ ጠየቁት።  እሱም መልሶ “ሙሴ ምን ብሎ ነው ያዘዛችሁ?” አላቸው።  እነሱም “ሙሴ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዷል” አሉት።  ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው:- “ሙሴ ይህን ትእዛዝ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና መሆኑን አይቶ ነው።  ይሁን እንጂ በፍጥረት መጀመሪያ ‘አምላክ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።  ከዚህም የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤  ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’፤ በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም።  ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን* ማንም ሰው አይለያየው።” 10  እንደገና ወደ ቤት በገባ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ጉዳይ ይጠይቁት ጀመር። 11  እሱም እንዲህ አላቸው:- “ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእሷ ላይ ያመነዝራል፤ 12  እንዲሁም አንዲት ሴት ባሏን ፈታ ሌላ ብታገባ ምንዝር ትፈጽማለች።” 13  ሰዎችም ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ትንንሽ ልጆችን ወደ እሱ ያመጡ ጀመር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው። 14  ኢየሱስ ይህን ሲያይ ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው:- “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነው። 15  እውነት እላችኋለሁ፣ የአምላክን መንግሥት እንደ አንድ ትንሽ ልጅ ሆኖ የማይቀበል ሁሉ ፈጽሞ ወደዚህ መንግሥት አይገባም።” 16  ልጆቹንም አቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ይባርካቸው ጀመር። 17  ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ ሰው እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጉልበቱ ተንበርክኮ “ጥሩ መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ሲል ጠየቀው። 18  ኢየሱስም እንዲህ አለው:- “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም። 19  ‘አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመሥክር፣ አታታል፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚሉትን ትእዛዛት ታውቃለህ።” 20  ሰውየውም “መምህር፣ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ስጠብቅ ኖሬያለሁ” አለው። 21  ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ ከዚያም “አንድ ነገር ይጎድልሃል፤ ሂድና ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከታዬ ሁን” አለው። 22  ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ አዘነ፤ ብዙ ንብረት ስለነበረውም እያዘነ ሄደ። 23  ኢየሱስ ዙሪያውን ከተመለከተ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት መግባት ምንኛ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል!” አላቸው። 24  ደቀ መዛሙርቱ ግን በንግግሩ ተገረሙ። ኢየሱስም እንደገና መልሶ እንዲህ አላቸው:- “ልጆች ሆይ፣ ወደ አምላክ መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው! 25  ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል።” 26  ደቀ መዛሙርቱ ይበልጥ በመገረም “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” አሉት። 27  ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ትኩር ብሎ በመመልከት “ይህ በሰዎች ዘንድ አይቻልም፤ በአምላክ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ ምክንያቱም በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል” አለ። 28  ጴጥሮስም “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን እየተከተልንህ ነው” አለው። 29  ኢየሱስም እንዲህ አለ:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ስለ እኔና ስለ ምሥራቹ ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን ትቶ፣ 30  አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እህቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና እርሻን መቶ እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት የማያገኝ ማንም የለም። 31  ይሁን እንጂ ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑ ደግሞ ፊተኞች ይሆናሉ።” 32  ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ ላይ እየተጓዙ ሳሉ ኢየሱስ ከፊት ከፊታቸው ይሄድ ነበር፤ እነሱም ተደነቁ፤ ይከተሉት የነበሩትም ፍርሃት አደረባቸው። እንደገና አሥራ ሁለቱን ገለል አድርጎ በመውሰድ የሚደርስበትን ነገር ይነግራቸው ጀመር:- 33  “እነሆ፣ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዝን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት አልፎ ይሰጣል፤ እነሱም ሞት ይፈርዱበታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፤ 34  ያፌዙበታል፣ ይተፉበታል፣ ይገርፉታል፣ ከዚያም ይገድሉታል፤ ሆኖም ከሦስት ቀን በኋላ ይነሳል።” 35  ሁለቱ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እሱ ቀርበው “መምህር፣ የምንለምንህን ነገር ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት። 36  እሱም “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 37  እነሱም “በክብርህ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” አሉት። 38  ኢየሱስ ግን “የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ወይም እኔ የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁ?” አላቸው። 39  እነሱም “እንችላለን” አሉት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቀውን ጥምቀትም ትጠመቃላችሁ። 40  በቀኜ ወይም በግራዬ የመቀመጡ ጉዳይ ግን ለተዘጋጀላቸው የሚሰጥ እንጂ በእኔ ፈቃድ የሚሆን አይደለም።” 41  የቀሩት አሥሩ ይህን ሲሰሙ በያዕቆብና በዮሐንስ ላይ ይቆጡ ጀመር። 42  ሆኖም ኢየሱስ ወደ እሱ ከጠራቸው በኋላ እንዲህ አላቸው:- “የአሕዛብ ገዥ ተደርገው የሚታዩ ሰዎች በእነሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ፣ ታላላቆቻቸውም በኃይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ። 43  በእናንተ መካከል እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ግን አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባዋል፤ 44  እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ሊሆን ይገባዋል። 45  ምክንያቱም የሰው ልጅ እንኳ የመጣው ለማገልገልና በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም።” 46  ከዚያም ወደ ኢያሪኮ መጡ። እሱና ደቀ መዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጡ ዓይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ በመንገዱ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። 47  እሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን ሲሰማ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” እያለ ይጮኽ ጀመር። 48  በዚህ ጊዜ ብዙዎች ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” እያለ ይበልጥ መጮኹን ቀጠለ። 49  ኢየሱስም ቆመና “ጥሩት” አለ። እነሱም ዓይነ ስውሩን ሰው “አይዞህ፣ ተነስ፣ እየጠራህ ነው” አሉት። 50  እሱም መደረቢያውን ጥሎ ዘሎ በመነሳት ወደ ኢየሱስ ሄደ። 51  ኢየሱስም መልሶ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለው። ዓይነ ስውሩም “ራቦኒ፣* የዓይኔ ብርሃን እንዲመለስ አድርግልኝ” አለው። 52  ኢየሱስም “ሂድ፣ እምነትህ አድኖሃል” አለው። ወዲያውም የዓይኑ ብርሃን ተመለሰለት፤ በመንገድም ይከተለው ጀመር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ማር 10:9 ማቴዎስ 19:6 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ማር 10:51 * “መምህር” ማለት ነው።