በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ሉቃስ 8:1-56

8  ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከና እያወጀ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ይጓዝ ነበር። አሥራ ሁለቱም ከእሱ ጋር ነበሩ፤  በተጨማሪም ከክፉ መናፍስትና ከበሽታ የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች አብረውት ነበሩ፤ ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፣  የሄሮድስ ቤት አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሴቶች የነበሩ ሲሆን በንብረታቸው ያገለግሏቸው ነበር።  ኢየሱስን ተከትለው አብረውት ከከተማ ወደ ከተማ ከሚሄዱት ጋር እጅግ ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡ ጊዜ እንዲህ ሲል በምሳሌ ተናገረ:-  “አንድ ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። በሚዘራበት ጊዜም አንዳንዱ መንገድ ዳር ወድቆ ተረጋገጠ፤ የሰማይ ወፎችም መጥተው ለቀሙት።  አንዳንዱም ዐለት ላይ ወደቀ፤ ከበቀለም በኋላ እርጥበት ስላላገኘ ደረቀ።  አንዳንዱ ደግሞ በእሾህ መካከል ወደቀ፤ አብሮት ያደገውም እሾህ አንቆ አስቀረው።  ሌላው ደግሞ ጥሩ አፈር ላይ ወደቀ፤ ከበቀለም በኋላ መቶ እጥፍ አፈራ።” ይህን ከተናገረ በኋላ ድምፁን ከፍ አድርጎ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።  ደቀ መዛሙርቱ ግን የዚህን ምሳሌ ትርጉም ይጠይቁት ጀመር። 10  እሱም እንዲህ አለ:- “ለእናንተ የአምላክን መንግሥት ቅዱስ ሚስጥሮች የመረዳት ችሎታ ተሰጥቷችኋል፤ ለቀሩት ግን በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ ይኸውም እያዩ እንዳያስተውሉ እንዲሁም እየሰሙ ትርጉሙን እንዳይረዱ ነው። 11  እንግዲህ የምሳሌው ትርጉም ይህ ነው:- ዘሩ የአምላክ ቃል ነው። 12  በመንገድ ዳር የወደቁት ቃሉን የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚያ በኋላ ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። 13  በዐለት ላይ የወደቁት ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነዚህ ግን ሥር የላቸውም፤ ለጊዜው አምነው ቢቀበሉም በፈተና ወቅት ይወድቃሉ። 14  በእሾህ መካከል የወደቁት ቃሉን የሚሰሙ ናቸው፤ ሆኖም በዚህ ዓለም የኑሮ ጭንቀት፣ ሀብትና ሥጋዊ ደስታ ተውጠው ሙሉ በሙሉ ይታነቃሉ፤ ለፍሬም አይበቁም። 15  በጥሩ አፈር ላይ የወደቁት ደግሞ ቃሉን በመልካምና በጥሩ ልብ ሰምተው በውስጣቸው በማኖር በጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። 16  “መብራት አብርቶ በዕቃ የሚከድን ወይም አልጋ ሥር የሚያስቀምጥ ሰው የለም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ ቤት የሚገቡ ሁሉ ብርሃን እንዲያገኙ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል። 17  በመሆኑም ተሸሽጎ የማይገለጥ፣ ተሰውሮም የማይታወቅና ይፋ የማይወጣ ነገር የለም። 18  ስለዚህ እንዴት እንደምታዳምጡ በጥሞና አስቡ፤ ምክንያቱም ላለው ተጨማሪ ይሰጠዋል፤ የሌለው ግን እንዳለው አድርጎ የሚያስበው ነገር እንኳ ይወሰድበታል።” 19  ከዚህ በኋላ እናቱና ወንድሞቹ እሱ ወዳለበት መጡ፤ ሆኖም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ወደ እሱ ሊቀርቡ አልቻሉም። 20  ይሁንና “እናትህና ወንድሞችህ ሊያገኙህ ፈልገው ውጭ ቆመዋል” ተብሎ ተነገረው። 21  እሱም መልሶ “እናቴና ወንድሞቼ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው” አላቸው። 22  አንድ ቀን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ጀልባ ከተሳፈሩ በኋላ “ወደ ሐይቁ ማዶ እንሻገር” አላቸው። ከዚያም ጉዞ ጀመሩ። 23  እየተጓዙ ሳሉም ኢየሱስ እንቅልፍ ወሰደው። በዚህ ጊዜ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በሐይቁ ላይ ተነሳ፤ ጀልባዋም በውኃ መሞላት ስለጀመረች አደጋ ላይ ወደቁ። 24  በመጨረሻ ሄደው “መምህር፣ መምህር ማለቃችን እኮ ነው!” በማለት ቀሰቀሱት። እሱም ተነስቶ ነፋሱንና የሚናወጠውን ውኃ ገሠጸ፤ በዚህ ጊዜ ነፋሱና ውኃው ረጭ አለ፤ ጸጥታም ሰፈነ። 25  ከዚያም “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው። እነሱ ግን በፍርሃት ተውጠውና በጣም ተደንቀው እርስ በርሳቸው “ነፋስንና ውኃን እንኳ የሚያዝ፣ እነሱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ። 26  ከዚያም በገሊላ ማዶ ወደሚገኘው ጌርጌሴኖን ወደተባለው አገር የባሕር ዳርቻ ደረሱ። 27  ኢየሱስ ወደ የብስ በወረደ ጊዜ ግን አጋንንት ያደሩበት አንድ የዚያች ከተማ ሰው አገኘው። ይህ ሰው ልብሱን ከጣለ ብዙ ጊዜው ነበር፤ የሚኖረውም በቤት ውስጥ ሳይሆን በመቃብር ስፍራ ነበር። 28  ኢየሱስንም ባየው ጊዜ እየጮኸ በፊቱ ተደፋ፤ በታላቅ ድምፅም “የልዑል አምላክ ልጅ ኢየሱስ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለኝ? እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ” አለ። 29  (ይህንም ያለው ኢየሱስ ርኩሱ መንፈስ ከሰውየው እንዲወጣ እያዘዘው ስለነበረ ነው። ርኩሱ መንፈስ ሰውየውን ለረጅም ጊዜ ይዞት ነበር፤ በተደጋጋሚ በሰንሰለትና በእግር ብረት እየታሰረ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም የታሰረበትን ሰንሰለት ይበጣጥስ ነበር፤ ጋኔኑም ሰው ወደማይኖርባቸው ቦታዎች ይነዳው ነበር።) 30  ኢየሱስ “ስምህ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። እሱም ብዙ አጋንንት ገብተውበት ስለነበር “ሌጌዎን” አለው። 31  አጋንንቱም ወደ ጥልቁ እንዲሄዱ እንዳያዛቸው አጥብቀው ለመኑት። 32  በዚያም በተራራው ላይ ብዛት ያለው የአሳማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ ስለዚህ ወደ አሳማዎቹ ይገቡ ዘንድ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት። እሱም ፈቀደላቸው። 33  በዚህ ጊዜ አጋንንቱ ከሰውየው ወጥተው አሳማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ የአሳማውም መንጋ ከገደሉ አፋፍ እየተንደረደረ በመውረድ ሐይቁ ውስጥ ገብቶ ሰጠመ። 34  እረኞቹ ግን የሆነውን ነገር ሲያዩ ሸሽተው በመሄድ ያዩትን በከተማውና በገጠሩ አወሩ። 35  በዚህ ጊዜ ሕዝቡ የሆነውን ነገር ለማየት ወጥተው ወደ ኢየሱስ መጡ፤ አጋንንት የወጡለትም ሰው ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት ኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጦ ባገኙት ጊዜ ፍርሃት አደረባቸው። 36  የተፈጸመውን ነገር ያዩ ሰዎች አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው እንዴት ጤናማ ሊሆን እንደቻለ አወሩላቸው። 37  ስለዚህ ከጌርጌሴኖን አገር የመጡት ሕዝብ በሙሉ ታላቅ ፍርሃት ስላደረባቸው ከዚያ እንዲሄድላቸው ለመኑት። እሱም ጀልባዋ ላይ ተሳፍሮ ተመልሶ ሄደ። 38  አጋንንት የወጡለት ሰው ግን አብሮት ይሆን ዘንድ ደጋግሞ ለመነው፤ ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ሰውየውን አሰናበተው:- 39  “ወደ ቤትህ ተመለስ፤ አምላክ ያደረገልህንም ነገር ተናገር።” ሰውየው እንደተባለው ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር በከተማው ሁሉ እያወጀ ሄደ። 40  ሕዝቡ እየጠበቁት ስለነበር ኢየሱስ በተመለሰ ጊዜ ሁሉም በደስታ ተቀበሉት። 41  በዚያን ጊዜ የምኩራብ አለቃ የሆነ ኢያኢሮስ የሚባል አንድ ሰው መጣ። ኢየሱስ እግር ላይም ወድቆ ወደ ቤቱ እንዲሄድለት ይለምነው ጀመር፤ 42  ይህን ልመና ያቀረበው አሥራ ሁለት ዓመት ገደማ የሆናት አንድያ ልጁ ለሞት ተቃርባ ስለነበር ነው። እየተጓዘም ሳለ ሕዝቡ እየተጋፋ ያጨናንቀው ነበር። 43  ለአሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የኖረች አንዲት ሴት ነበረች፤ ይህችን ሴት ሊፈውሳት የቻለ አንድም ሰው አልነበረም፤ 44  ከኋላም መጥታ የልብሱን ዘርፍ ነካች፤ ይፈሳት የነበረውም ደም በቅጽበት ቆመ። 45  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “የነካኝ ማን ነው?” አለ። ሁሉም በካዱ ጊዜ፣ ጴጥሮስ “መምህር፣ ሕዝቡ ከቦህ እየተጋፋህ ነው የሚሄደው” አለው። 46  ኢየሱስ ግን “ኃይል ከእኔ እንደወጣ ስለታወቀኝ አንድ ሰው ነክቶኛል” አለ። 47  ሴትየዋም ሳይታወቅባት መሄድ እንዳልቻለች በተረዳች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ከዚያም ለምን እንደነካችውና እንዴት በቅጽበት እንደተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት ተናገረች። 48  እሱ ግን “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት። 49  ገና እየተናገረ ሳለ ከምኩራብ አለቃው ቤት የተላከ አንድ ሰው መጥቶ “ልጅህ ሞታለች፤ ከዚህ በኋላ መምህሩን አታስቸግረው” አለው። 50  ኢየሱስ ይህን ሲሰማ “አትፍራ፣ ብቻ እመን፤ ልጅህ ትድናለች” አለው። 51  ወደ ኢያኢሮስ ቤት በደረሰ ጊዜ ከጴጥሮስ፣ ከዮሐንስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከልጅቷ አባትና እናት በስተቀር ማንም አብሮት ወደ ውስጥ እንዲገባ አልፈቀደም። 52  በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ሁሉ ለልጅቷ እያለቀሱና በሐዘን ደረታቸውን እየደቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ “በቃ አታልቅሱ፣ ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። 53  ይህን ሲሰሙ ልጅቷ እንደሞተች ያውቁ ስለነበር በማፌዝ ይስቁበት ጀመር። 54  እሱ ግን እጇን በመያዝ ድምፁን ከፍ አድርጎ “አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!” አለ። 55  የልጅቷም መንፈስ ተመለሰ፤ ወዲያውም ተነሳች፤ የምትበላውም ነገር እንዲሰጧት አዘዘ። 56  ወላጆቿም የሚሆኑት ጠፋቸው፤ እሱ ግን የሆነውን ነገር ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።

የግርጌ ማስታወሻዎች