በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ሉቃስ 21:1-38

21  ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች በመዋጮ ዕቃዎቹ ውስጥ መባቸውን ሲከቱ አየ።  ከዚያም አንዲት ድሃ መበለት በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች በዚያ ስትከት አየ፤  እንዲህም አለ:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ይህች መበለት ድሃ ብትሆንም እንኳ ከሁሉ የበለጠ የከተተችው እሷ ነች።  ምክንያቱም ሁሉም መባ የከተቱት ከትርፋቸው ነው፤ ይህች ሴት ግን በድሃ አቅሟ ያላትን መተዳደሪያ ሁሉ ከተተች።”  በኋላም አንዳንዶች ቤተ መቅደሱ ውብ በሆኑ ድንጋዮችና ለአምላክ በተሰጡ ስጦታዎች እንዴት እንዳጌጠ በተናገሩ ጊዜ  “ይህ የምታዩት ነገር ሁሉ የሚፈርስበት ጊዜ ይመጣል፤ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ አይኖርም” አለ።  እነሱም “መምህር፣ እነዚህ ነገሮች በእርግጥ የሚፈጸሙት መቼ ነው? እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸው እንደማይቀር የሚያሳየው ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።  እሱም እንዲህ አለ:- “እንዳያሳስቷችሁ ተጠንቀቁ፤ ምክንያቱም ብዙዎች ‘እኔ እሱ ነኝ’ እንዲሁም ‘የሚጠበቀው ጊዜ ቀርቧል’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ። እነሱን አትከተሉ።  በተጨማሪም ስለ ጦርነትና ብጥብጥ ስትሰሙ አትሸበሩ። አስቀድሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸም አለባቸው፤ ፍጻሜው ግን ወዲያው አይመጣም።” 10  ከዚያም እንዲህ ይላቸው ጀመር:- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል፤ 11  በተጨማሪም ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ፤ በተለያየ ስፍራም ቸነፈርና የምግብ እጥረት ይሆናል፤ ደግሞም የሚያስፈሩ ነገሮች እንዲሁም ከሰማይ ታላላቅ ምልክቶች ይታያሉ። 12  “እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከመፈጸማቸው በፊት ግን ሰዎች ይይዟችኋል፣ ስደት ያደርሱባችኋል እንዲሁም ለምኩራብና ለወህኒ ቤት አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በስሜም ምክንያት በነገሥታትና በገዥዎች ፊት ያቀርቧችኋል። 13  ይህም ለመመሥከር የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትላችኋል። 14  ይሁንና የምትሰጡትን መልስ አስቀድማችሁ መዘጋጀት እንደማያስፈልጋችሁ ልብ በሉ፤ 15  ምክንያቱም ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ በአንድነት ሆነው ሊቋቋሙት ወይም ሊከራከሩት የማይችሉት አንደበትና ጥበብ እሰጣችኋለሁ። 16  ከዚህም በተጨማሪ ወላጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁ፣ ዘመዶቻችሁና ጓደኞቻችሁ እንኳ ሳይቀሩ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ አንዳንዶቻችሁንም ይገድላሉ፤ 17  በስሜም የተነሳ በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። 18  ይሁን እንጂ ከራሳችሁ ፀጉር አንዷ እንኳ በምንም ዓይነት አትጠፋም። 19  እናንተ በበኩላችሁ ከጸናችሁ ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ። 20  “በተጨማሪም ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ ስታዩ መጥፊያዋ እንደቀረበ እወቁ። 21  በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በከተማይቱ ውስጥ ያሉም ከዚያ ይውጡ፤ በገጠር ያሉም ወደ እሷ አይግቡ፤ 22  ምክንያቱም የተጻፈው ነገር ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይህ የፍትሕ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ነው። 23  በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! ምክንያቱም በምድሪቱ ላይ ታላቅ መከራ፣ በዚህ ሕዝብም ላይ ቁጣ ይመጣል፤ 24  በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ተማርከውም ወደየአገሩ ይወሰዳሉ፤ የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት እስኪፈጸሙ ድረስም ኢየሩሳሌም በአሕዛብ ትረገጣለች። 25  “እንዲሁም በፀሐይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ ምልክቶች ይታያሉ፤ በምድርም ላይ ሕዝቦች ከባሕሩ ድምፅና ነውጥ የተነሳ መውጫው ጠፍቷቸው ይጨነቃሉ፤ 26  የሰማያት ኃይላት ስለሚናወጡ ሰዎች ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ። 27  በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 28  ሆኖም እነዚህ ነገሮች መከሰት ሲጀምሩ መዳናችሁ እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ።” 29  ቀጥሎም እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው:- “የበለስ ዛፍንና ሌሎች ዛፎችን ሁሉ ተመልከቱ፤ 30  ዛፎቹ እንዳቆጠቆጡ ስታዩ በዚያን ጊዜ በጋ* እንደቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 31  ልክ እንደዚሁ እናንተም እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱ ስታዩ የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እወቁ። 32  እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪከሰቱ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም። 33  ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም። 34  “ይሁንና ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት፣ እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት 35  እንደ ወጥመድ ይመጣባችኋል። ምክንያቱም ይህ በመላው ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይደርስባቸዋል። 36  እንግዲያው መፈጸማቸው ከማይቀረው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ማምለጥና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ ሁልጊዜ ምልጃ እያቀረባችሁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።” 37  ኢየሱስ ቀን ቀን በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር፤ ሲመሽ ግን ወጥቶ ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ ያድር ነበር። 38  ሕዝቡም ሁሉ እሱን ለመስማት በማለዳ እሱ ወደሚገኝበት ወደ ቤተ መቅደስ ይመጡ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ሉቃስ 21:30 * በጳለስጢና ምድር ዕፅዋት የሚለመልሙት በበጋ ነው።