በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ--አዲስ ዓለም ትርጉም በ2013 ተሻሽሎ የወጣውን ተመልከት

ሉቃስ 18:1-43

18  ከዚያም ተስፋ ሳይቆርጡ ዘወትር የመጸለይን አስፈላጊነት በተመለከተ አንድ ምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፤  እንዲህም አላቸው:- “በአንዲት ከተማ አምላክን የማይፈራና ሰውን የማያከብር አንድ ዳኛ ነበር።  በዚያች ከተማ አንዲት መበለት የነበረች ሲሆን በየጊዜው ወደ እሱ እየሄደች ‘ከባላጋራዬ ጋር ለምከራከርበት ክስ ፍትሐዊ ፍርድ ፍረድልኝ’ ትለው ነበር።  ይሁንና ዳኛው ለተወሰነ ጊዜ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፤ በኋላ ግን በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ:- ‘ምንም እንኳ አምላክን የማልፈራ፣ ሰውንም የማላከብር ብሆን  ይህች መበለት ሁልጊዜ እየመጣች ስለምታስቸግረኝ እንደምንም ብዬ ፍትሕ እንድታገኝ ማድረግ አለብኝ፤ አለበለዚያ በየጊዜው እየመጣች አሳሬን ታበላኛለች።’”  ከዚያም ጌታ እንዲህ አለ:- “ምንም እንኳ ዳኛው ዓመፀኛ ቢሆንም ምን እንዳለ ልብ በሉ!  ታዲያ አምላክ ትዕግሥት የሚያሳያቸው ቢሆንም እንኳ ቀንና ሌሊት ወደ እሱ የሚጮኹት ምርጦቹ ፍትሕ እንዲያገኙ አያደርግም?  እላችኋለሁ፣ በፍጥነት ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል። የሆነ ሆኖ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ በእርግጥ እምነት ያገኝ ይሆን?”  ጻድቃን ነን ብለው በማሰብ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎችን በንቀት ዓይን ለሚመለከቱ ደግሞ የሚከተለውን ምሳሌ ተናገረ:- 10  “ሁለት ሰዎች ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፤ አንደኛው ፈሪሳዊ፣ ሌላኛው ደግሞ ቀረጥ ሰብሳቢ ነበር። 11  ፈሪሳዊው ቆሞ በልቡ እንዲህ ሲል ይጸልይ ጀመር:- ‘አምላክ ሆይ፣ እንደ ሌሎች ሰዎች ቀማኛ፣ ዓመፀኛ፣ አመንዝራ፣ በተለይ ደግሞ እንደዚህ ቀረጥ ሰብሳቢ ስላላደረግከኝ አመሰግንሃለሁ። 12  በሳምንት ሁለቴ እጾማለሁ፣ ከማገኘውም ነገር ሁሉ አሥራት አወጣለሁ።’ 13  ቀረጥ ሰብሳቢው ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ለማየትም እንኳ አልደፈረም፤ ከዚህ ይልቅ ‘አምላክ ሆይ፣ እኔን ኃጢአተኛውን ምሕረት አድርግልኝ’ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር። 14  እላችኋለሁ፣ ከዚያኛው ሰው ይልቅ ይኼኛው ሰው ይበልጥ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ምክንያቱም ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይደረጋል።” 15  ሰዎችም ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሕፃናትን ወደ እሱ ያመጡ ጀመር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ይህን ሲያዩ ገሠጿቸው። 16  ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሕፃናቱን ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አለ:- “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው። ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነው። 17  እውነት እላችኋለሁ፣ የአምላክን መንግሥት እንደ አንድ ትንሽ ልጅ ሆኖ የማይቀበል ሁሉ ፈጽሞ ወደዚህ መንግሥት አይገባም።” 18  ከአይሁድ አለቆችም አንዱ “ጥሩ መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት መውረስ የምችለው ምን ባደርግ ነው?” ሲል ጠየቀው። 19  ኢየሱስም እንዲህ አለው:- “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም። 20  ‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመሥክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚሉትን ትእዛዛት ታውቃለህ።” 21  ሰውየውም “እነዚህን ሁሉ ከልጅነት ጀምሮ ስጠብቅ ኖሬያለሁ” አለ። 22  ኢየሱስ ይህን ከሰማ በኋላ “አሁንም አንድ የሚቀርህ ነገር አለ፤ ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ ለድሆች አከፋፍል፤ በሰማያትም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከታዬ ሁን” አለው። 23  ሰውየው በጣም ሀብታም ስለነበረ ይህን ሲሰማ እጅግ አዘነ። 24  ኢየሱስም ሰውየውን ተመልክቶ እንዲህ አለ:- “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት መግባት ምንኛ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል! 25  እንዲያውም ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል።” 26  ይህን የሰሙ ሰዎች “እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። 27  እሱም “በሰዎች ዘንድ የማይቻል ነገር በአምላክ ዘንድ ይቻላል” አለ። 28  ጴጥሮስ ግን “እነሆ፣ እኛ ያለንን ነገር ትተን ተከትለንሃል” አለ። 29  ኢየሱስም እንዲህ አላቸው:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ለአምላክ መንግሥት ሲል ቤትን ወይም ሚስትን ወይም ወንድሞችን ወይም ወላጆችን ወይም ልጆችን ትቶ፣ 30  አሁን በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ሳያገኝ የሚቀር ማንም የለም።” 31  ከዚያም አሥራ ሁለቱን ለብቻቸው ወስዶ እንዲህ አላቸው:- “እነሆ! ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዝን ነው፤ የሰውን ልጅ በተመለከተም በነቢያት የተጻፉት ነገሮች ሁሉ ይፈጸማሉ። 32  ለምሳሌ ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ ያፌዙበታል፣ ያንገላቱታል እንዲሁም ይተፉበታል፤ 33  ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፤ በሦስተኛው ቀን ግን ይነሳል።” 34  ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ መካከል አንዱንም አልተረዱም፤ የተናገረው ቃል ተሰውሮባቸው ነበር፤ የተባለውም ነገር አልገባቸውም። 35  ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ እየተቃረበ ሳለ አንድ ዓይነ ስውር በመንገዱ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። 36  ዓይነ ስውሩም ብዙ ሕዝብ በዚያ ሲያልፍ ሰምቶ ስለ ሁኔታው ይጠይቅ ጀመር። 37  ሰዎቹም “የናዝሬቱ ኢየሱስ በዚህ እያለፈ ነው!” ብለው ነገሩት። 38  በዚህ ጊዜ “ኢየሱስ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” እያለ ይጮኽ ጀመር። 39  ከፊት ከፊት የሚሄዱትም ሰዎች ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” እያለ ይበልጥ መጮኹን ቀጠለ። 40  ኢየሱስም ባለበት ቆመና ሰውየውን ወደ እሱ እንዲያመጡት አዘዘ። ሰውየው ወደ እሱ በቀረበ ጊዜም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቀው:- 41  “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” እሱም “ጌታ ሆይ፣ የዓይኔ ብርሃን እንዲመለስ አድርግልኝ” አለው። 42  ስለዚህ ኢየሱስ “የዓይንህ ብርሃን ይመለስልህ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው። 43  ወዲያውም የዓይኑ ብርሃን ተመለሰለት፤ አምላክን እያመሰገነም በመንገድ ይከተለው ጀመር። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ አምላክን አወደሱ።

የግርጌ ማስታወሻዎች