በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ትምህርት 3

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዳግመኛ የተገለጠው እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዳግመኛ የተገለጠው እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ 1870ዎቹ

የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ እትም፣ 1879

መጠበቂያ ግንብ በአሁኑ ጊዜ

ክርስቶስ ከሞተ በኋላ ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች መካከል የሐሰት አስተማሪዎች እንደሚነሱና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንደሚበክሉ መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) ከጊዜ በኋላ ይህ ትንቢት በትክክል ተፈጸመ። ሐሰተኛ አስተማሪዎች የኢየሱስን ትምህርቶች ከአረማውያን ሃይማኖት ጋር ስለቀላቀሉት እውነተኛ ያልሆነ ክርስትና ተፈጠረ። (2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4) ታዲያ በዛሬው ጊዜ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለን እውቀት ትክክለኛ መሆኑን እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?

ይሖዋ እውነቱን የሚገልጥበት ጊዜ ደረሰ። ይሖዋ ‘በፍጻሜው ዘመን እውነተኛው እውቀት እንደሚበዛ’ ተንብዮ ነበር። (ዳንኤል 12:4) እውነትን ይፈልጉ የነበሩ ጥቂት ሰዎች አብዛኞቹ የአብያተ ክርስቲያናት መሠረተ ትምህርቶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ እንደሌላቸው በ1870 ተገነዘቡ። ስለዚህም የመጀመሪያዎቹንና ያልተበረዙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ለመረዳት ምርምር ማድረግ ጀመሩ፤ ይሖዋም መንፈሳዊ ማስተዋል እንዲያገኙ በመርዳት ጥረታቸውን ባርኮላቸዋል።

ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማጥናት ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ያጠኑ የነበሩት በቀድሞ ዘመን የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ርዕስ በርዕስ ይወያዩ ነበር። ይህን ዘዴ ዛሬም ድረስ እንጠቀምበታለን። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ለመረዳት የሚያስቸግር የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲያጋጥማቸው ጉዳዩን ግልጽ የሚያደርጉ ሌሎች ጥቅሶችን ይመረምሩ ነበር። ከተቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ መደምደሚያ ላይ ሲደርሱ የደረሱበትን መደምደሚያ በጽሑፍ ያሰፍሩታል። በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን እንዲተረጉም ያደረጉ ሲሆን ይህም ስለ አምላክ ስምና መንግሥት፣ አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር ስላለው ዓላማሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ እንዲሁም ስለ ትንሣኤ ተስፋ እውነቱን ለማወቅ አስቻላቸው። ያደረጉት ምርምር ከተለያዩ የሐሰት እምነቶችና ልማዶች ነፃ አውጥቷቸዋል።—ዮሐንስ 8:31, 32

በ1879 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እውነቱን በስፋት የሚያሳውቁበት ጊዜ እንደደረሰ አስተዋሉ። ስለሆነም በዚያ ዓመት፣ ዛሬም የምናትመውን የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ የተባለውን መጽሔት ማዘጋጀት ጀመሩ። በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በ240 አገሮች ከ750 በሚበልጡ ቋንቋዎች ለሰዎች እንሰብካለን። በእርግጥም እውነተኛ እውቀት የዚህን ዘመን ያህል የበዛበት ጊዜ የለም!

  • ክርስቶስ ከሞተ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ምን ሆነ?

  • በአምላክ ቃል ውስጥ ያለው እውነት በዘመናችን ሊገለጥ የቻለው እንዴት ነው?