በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ተጨማሪ መረጃ

ገንዘብ ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን መፍታት

ገንዘብ ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን መፍታት

ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 6:1-8 ላይ በክርስቲያኖች መካከል ሊከሰት ስለሚችል የፍርድ ቤት ሙግት አብራርቷል። በቆሮንቶስ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ክሳቸውን “በዓመፀኛ ሰዎች ፊት ለማቅረብ ፍርድ ቤት ለመሄድ [መድፈራቸው]” እንዳሳዘነው ገልጿል። (ቁጥር 1) ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች በመካከላቸው የሚነሱ አለመግባባቶችን በጉባኤ ውስጥ በተቋቋመው ሥርዓት መሠረት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በዓለም ፍርድ ቤቶች መካሰሳቸው ተገቢ የማይሆንባቸውን ምክንያቶች ተናግሯል። በመጀመሪያ ይህን የመሰለ ምክር በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት መስጠት ያስፈለገው ለምን እንደሆነ እንመልከት። ከዚያም በዚህ መመሪያ ውስጥ ላይካተቱ የሚችሉ ሌሎች ሁኔታዎችን እንመለከታለን።

ገንዘብ ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከአንድ ክርስቲያን ጋር አለመግባባት ካጋጠመን በመጀመሪያ ደረጃ ችግሩን ለመፍታት መጣር የሚኖርብን በራሳችን መንገድ ሳይሆን በይሖዋ መንገድ መሆን ይገባዋል። (ምሳሌ 14:12) ኢየሱስ እንደተናገረው አለመግባባቱ ሥር ሰድዶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት በአፋጣኝ መፍታቱ በጣም ጥሩ ይሆናል። (ማቴዎስ 5:23-26) የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ክርስቲያኖች በመካከላቸው ከፍተኛ ጭቅጭቅ ተፈጥሮ ፍርድ ቤት እስከ መቆም ደርሰዋል። ጳውሎስ “እርስ በርስ ተካሳችሁ ፍርድ ቤት መሄዳችሁ ለእናንተ ትልቅ ሽንፈት ነው” ብሏል። ሽንፈት የሚሆነው ለምንድን ነው? ዋነኛው ምክንያት እንዲህ ማድረግ በጉባኤውና በምናመልከው አምላክ ስም ላይ ነቀፌታ ስለሚያስከትል ነው። በመሆኑም ጳውሎስ “ከዚህ ይልቅ እናንተ ራሳችሁ ብትበደሉ አይሻልም?” በማለት ያነሳውን ጥያቄ በቁም ነገር ልናስብበት ይገባል።—ቁጥር 7

ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ፣ አምላክ በጉባኤው በኩል አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል ግሩም ዝግጅት እንዳደረገ ጠቅሷል። ሽማግሌዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በጥልቀት መማራቸው ጥበብ አስገኝቶላቸዋል፤ በመሆኑም ጳውሎስ “አሁን በሕይወት ውስጥ በሚያጋጥሙ ጉዳዮች ላይ” ‘ወንድሞቻቸውን መዳኘት እንደሚችሉ’ ተናግሯል። (ቁጥር 3-5) ኢየሱስ፣ ስም እንደ ማጥፋትና እንደ ማታለል ባሉ ከባድ በደሎች ምክንያት የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት ደረጃ በደረጃ መወሰድ የሚገባቸውን ሦስት እርምጃዎች ተናግሯል። የመጀመሪያው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ብቻ ተገናኝተው ስምምነት ላይ ለመድረስ መጣር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ፣ የመጀመሪያው ጥረት ካልተሳካ አንድ ወይም ሁለት  ምሥክር ጨምሮ መነጋገር ነው። ይህም ካልተሳካ በሦስተኛ ደረጃ ጉዳዩን በሽማግሌዎች ወደሚወከለው ወደ ጉባኤ ማቅረብ ነው።—ማቴዎስ 18:15-17

እርግጥ ነው፣ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የግድ የሕግ ባለሞያ ወይም ነጋዴ መሆን አያስፈልጋቸውም፤ የሽማግሌነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንዲህ መሆን አይጠበቅባቸውም። ገንዘብ ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በወንድሞች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል ደንብም አያወጡም። ከዚህ ይልቅ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ሥራ ላይ እንዲያውሉና ሰላም ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ለመርዳት ይጥራሉ። ሁኔታው በጣም ውስብስብ ከሆነባቸው የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ወይም የይሖዋ ምሥክሮችን ቅርንጫፍ ቢሮ ሊያማክሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ጳውሎስ የሰጠው ምክር የማያካትታቸው ሌሎች ሁኔታዎች ይኖራሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

ራስ ወዳድነት የማይንጸባረቅባቸውና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚጠናቀቁ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ፍርድ ቤት መሄድ ሕጋዊ ግዴታ ወይም መደበኛ አሠራር የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የፍቺን ውሳኔ ለማስጸደቅ፣ ልጅን የማሳደግ መብት ለመጠየቅ፣ ከፍቺ በኋላ ተቆራጭ ለማስወሰን፣ የኢንሹራንስ ካሳ ለመጠየቅ፣ አንድ የንግድ ድርጅት ከስሮ ለሐራጅ ሲቀርብ ገንዘብ ከሚከፈላቸው ዕዳ ጠያቂዎች አንዱ ሆኖ ለመመዝገብና ኑዛዜን ሕጋዊ ለማድረግ ፍርድ ቤት መሄድ ሊያስፈልግ ይችላል። በተጨማሪም አንድ ወንድም ራሱን ከሕግ ተጠያቂነት ለማዳን ሲል ሌላውን ወገን መልሶ ለመክሰስ ሊገደድ ይችላል። *

ሙግት በመውደድ መንፈስ እስካልሆነ ድረስ፣ እንደነዚህ ላሉት ጉዳዮች ፍርድ ቤት መሄድ ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ ከሰጠው ምክር ጋር አይጋጭም። * ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን በማንኛውም ጊዜ በዋነኝነት የሚያሳስበው የይሖዋ ስም መቀደስ እንዲሁም የጉባኤው አንድነትና ሰላም መጠበቅ መሆን ይገባዋል። የክርስቶስ ተከታዮች ዋነኛ መታወቂያቸው ፍቅራቸው ነው፤ ፍቅር ደግሞ “የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።”—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5፤ ዮሐንስ 13:34, 35

^ አን.2 ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ባይሆንም እንኳ አንድ ክርስቲያን በሌላው ክርስቲያን ላይ አስገድዶ እንደመድፈር፣ ድብደባ፣ ነፍስ ግድያ ወይም ከባድ ስርቆት ያለ ከባድ ወንጀል ይፈጽም ይሆናል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲፈጸሙ ፍርድ ቤት ሊያስቆም የሚችል ቢሆንም እንኳ ተበዳዩ ወገን ጉዳዩን ለባለ ሥልጣናት ማሳወቁ የክርስትናን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደመጻረር ሊቆጠር አይችልም።

^ አን.3 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የመጋቢት 15, 1997 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 17-22ን እና የጥቅምት 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 25-28ን ተመልከት።