በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’

 ተጨማሪ መረጃ

ከአንድ የተወገደ ግለሰብ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረን ይገባል?

ከአንድ የተወገደ ግለሰብ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረን ይገባል?

አንድ የቅርብ ወዳጃችን ወይም ዘመዳችን ኃጢአት ሠርቶ ንስሐ ባለመግባቱ ምክንያት ከጉባኤ ሲወገድ ስሜታችን በእጅጉ ይጎዳል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጠውን መመሪያ በፈቃደኝነት መታዘዛችን ለአምላክ ያለን ፍቅር ምን ያህል ጥልቀት እንዳለው እንዲሁም ለአምላክ ዝግጅት ታማኝ የምንሆነው እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ያሳያል። * ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎችን እንመልከት።

ከአንድ የተወገደ ግለሰብ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረን ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ወንድም ተብሎ እየተጠራ ሴሰኛ ወይም ስግብግብ ወይም ጣዖት አምላኪ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካራም ወይም ቀማኛ ከሆነ ማንኛውም ሰው ጋር መግጠማችሁን [ተዉ] አልፎ ተርፎም እንዲህ ካለው ሰው ጋር ምግብ እንኳ [አትብሉ]።” (1 ቆሮንቶስ 5:11) “በክርስቶስ ትምህርት ጸንቶ የማይኖር” ሰውን አስመልክቶ ደግሞ “ፈጽሞ በቤታችሁ አትቀበሉት ወይም ሰላም አትበሉት። ምክንያቱም ሰላም የሚለው ሰው የክፉ ሥራው ተባባሪ ይሆናል” ይላል። (2 ዮሐንስ 9-11) ከተወገዱ ሰዎች ጋር መንፈሳዊም ሆነ ማኅበራዊ ግንኙነት አይኖረንም። የመስከረም 15, 1981 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) በገጽ 25 ላይ እንደሚከተለው ይላል:- “ተራ ሰላምታ ወደ ጭውውት ወይም ወዳጅነት ወደ መመሥረት ሊያመራ የሚችል የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆን ይችላል። ታዲያ የተወገደን ሰው ሰላም በማለት ይህንን የመጀመሪያ እርምጃ መውሰድ እንፈልጋለን?”

ግንኙነታችንን ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ ያን ያህል አስፈላጊ ነው? አዎ፣ ለዚህ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ እንዲህ ማድረግ ለአምላክና ለቃሉ ታማኝ የመሆን ጉዳይ ነው። ይሖዋን የምንታዘዘው፣ መታዘዝ ቀላል በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከባድ በሚሆንበት ጊዜም ጭምር ነው። ይሖዋ ፍትሐዊና አፍቃሪ እንደሆነ እንዲሁም ሕጎቹ ዘላቂ ጥቅም እንደሚያስገኙልን ስለምንገነዘብ ለእሱ ያለን ፍቅር ትእዛዛቱን በሙሉ እንድንታዘዝ ይገፋፋናል። (ኢሳይያስ 48:17፤ 1 ዮሐንስ 5:3) በሁለተኛ ደረጃ፣ ኃጢአት ሠርቶ ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ካልሆነ ሰው ጋር ያለንን ግንኙነት ማቋረጣችን እኛንም ሆነ መላውን ጉባኤ ከመንፈሳዊና ከሥነ ምግባራዊ ብክለት የሚጠብቅ  ከመሆኑም በላይ የጉባኤውን መልካም ስም ያስጠብቃል። (1 ቆሮንቶስ 5:6, 7) በሦስተኛ ደረጃ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ መከተላችን የተወገደውን ሰው ሊጠቅመው ይችላል። የፍርድ ኮሚቴው ያስተላለፈውን ውሳኔ መደገፋችን እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሽማግሌዎች እሱን ለመርዳት ያደረጉትን ጥረት ለመቀበል አሻፈረኝ ያለውን ሰው ልብ ሊነካ ይችላል። ከሚወዳቸው ወዳጆቹ መለየቱ ‘ወደ ልቦናው እንዲመለስና’ የሠራው ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ተሰምቶት ወደ ይሖዋ ለመመለስ የሚያስችለውን እርምጃ እንዲወስድ ሊያነሳሳው ይችላል።—ሉቃስ 15:17

የተወገደው ሰው የሥጋ ዘመዳችን ቢሆንስ? በጣም በሚቀራረብ ቤተሰብ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ እያንዳንዳቸው ለይሖዋ ሕጎች ያላቸው ታማኝነት ፈተና ላይ ሊወድቅ ይችላል። ከተወገደ ዘመዳችን ጋር ሊኖረን የሚገባው ግንኙነት ምን ዓይነት መሆን አለበት? ሊያጋጥም የሚችለውን እያንዳንዱን ሁኔታ ማንሳት አንችልም። ይሁን እንጂ በሁለት መሠረታዊ ሁኔታዎች ላይ እናተኩር።

አንዳንድ ጊዜ የተወገደው የቤተሰብ አባል የሚኖረው ከቤተሰቡ ጋር ሊሆን ይችላል። መወገዱ የቤተሰብ ዝምድናውን ስለማይሽረው ከቤተሰቡ ጋር ያለው የዕለት ተዕለት ግንኙነትና እንቅስቃሴ እንደነበረ ይቀጥላል። ሆኖም ግለሰቡ የተሳሳተ ጎዳና በመከተሉ በእሱና አማኝ በሆኑት የቤተሰቡ አባላት መካከል የነበረው መንፈሳዊ ዝምድና እንዲቋረጥ አድርጓል። በመሆኑም ታማኝ የሆኑት የቤተሰብ አባላት ከእሱ ጋር ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ግንኙነት ሊኖራቸው አይችልም። ለምሳሌ ቤተሰቡ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት በሚሰበሰብበት ጊዜ የተወገደው ግለሰብ በመካከላቸው ቢገኝ በጥናቱ ላይ ተሳትፎ ማድረግ አይችልም። ይሁን እንጂ የተወገደው ግለሰብ ገና ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ቢሆን ወላጆቹ አሁንም እሱን የማስተማርና የመገሠጽ ኃላፊነት አለባቸው። ስለሆነም ወላጆች ለልጃቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳ ልጃቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ። *ምሳሌ 6:20-22፤ 29:17

በሌላ በኩል ደግሞ የተወገደው የቤተሰብ አባል የሚኖረው ራሱን ችሎ ሌላ ቦታ ሊሆን ይችላል። ከቤተሰብ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ የግድ መገናኘት አስፈላጊ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ቢችሉም እንዲህ ያለው ግንኙነት መብዛት አይኖርበትም። ታማኝ የሆኑ ክርስቲያኖች ሰበብ አስባብ እየፈለጉ በቤታቸው  ከማይኖር የተወገደ ዘመዳቸው ጋር ለመገናኘት አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ ለይሖዋና ለድርጅቱ ያላቸው ታማኝነት ከውገዳ ጋር የተያያዙትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እንዲያከብሩ ያነሳሳቸዋል። ታማኝነታቸውን በመጠበቅ እንዲህ ያለውን ጥብቅ አቋም መውሰዳቸው ለተወገደው ግለሰብ እንደሚያስቡ የሚያሳይ በመሆኑ ከተሰጠው ተግሣጽ ጥቅም እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል። *ዕብራውያን 12:11

^ አን.1 ከውገዳ ጋር በተያያዘ የሚጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ራሳቸውን ከጉባኤ ባገለሉ ሰዎች ላይ ጭምር ይሠራሉ።

^ አን.2 በቤት ውስጥ የሚኖሩና ለአካለ መጠን ያልደረሱ የተወገዱ ልጆችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የጥቅምት 1, 2001 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16-17ን እና የኅዳር 15, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 20ን ተመልከት።

^ አን.3 ከተወገዱ ዘመዶች ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የነሐሴ 2002 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 3-4ን፣ የሚያዝያ 15, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 26-31ን እና የመስከረም 15, 1981 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 26-31ን ተመልከት።