በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ተጨማሪ መረጃ

ክርስቲያን ሴቶች ራሳቸውን መሸፈን የሚኖርባቸው መቼ ነው? ለምንስ?

ክርስቲያን ሴቶች ራሳቸውን መሸፈን የሚኖርባቸው መቼ ነው? ለምንስ?

አንዲት ክርስቲያን ሴት አምልኮን የሚመለከቱ ጉዳዮች በምታከናውንበት ጊዜ ራሷን መሸፈን የሚኖርባት መቼ ነው? ለምንስ? ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ ስለዚህ ጉዳይ የሰጠውን መመሪያ እንመልከት። ለአምላክ ክብር የሚያመጣ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንድንችል የሚያስፈልገንን መመሪያ ሰጥቶናል። (1 ቆሮንቶስ 11:3-16) ጳውሎስ ልናስብባቸው የሚገቡ ሦስት ነገሮችን ማለትም (1) አንዲት ሴት ራሷን እንድትሸፍን የሚጠይቁባትን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች፣ (2) ራሷን እንድትሸፍን የሚያስገድዷትን ሁኔታዎች፣ እንዲሁም (3) ይህን መመሪያ እንድትታዘዝ የሚያነሳሷትን ምክንያቶች ገልጿል።

ራሷን እንድትሸፍን የሚጠይቁባት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች። ጳውሎስ ሁለት ነገሮችን ማለትም ጸሎትንና ትንቢት መናገርን ጠቅሷል። (ቁጥር 4, 5) ጸሎት ከይሖዋ ጋር የምንነጋገርበት የአምልኳችን ክፍል ነው። ትንቢት መናገር ደግሞ በዛሬው ጊዜ አንድ ክርስቲያን የሚያከናውነውን ማንኛውንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ተግባር ያመለክታል። ታዲያ ጳውሎስ አንዲት ሴት በምትጸልይበት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በምታስተምርበት ጊዜ ሁሉ ራሷን መሸፈን እንደሚገባት መናገሩ ነው? አይደለም። አንዲት ሴት ስትጸልይ ወይም ስታስተምር የሚኖረው ሁኔታ ራሷን መሸፈን ይኖርባት እንደሆነና እንዳልሆነ ይወስናል።

ራሷን እንድትሸፍን የሚያስገድዷት ሁኔታዎች። ጳውሎስ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የሚከናወንባቸውን ሁለት ቦታዎች ማለትም ቤተሰብንና ጉባኤን ጠቅሷል።  እንዲህ ብሏል:- “የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ [ነው]። . . . ራሷን ሳትሸፍን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራሷን ታዋርዳለች።” (ቁጥር 35) በቤተሰብ ውስጥ ይሖዋ ራስ አድርጎ የሾመው ባሏን ነው። ሚስት ለባሏ ሥልጣን የሚገባውን እውቅና ሳትሰጥ ይሖዋ ለእሱ የሰጠውን ኃላፊነት ብታከናውን ባሏን ማዋረድ ይሆንባታል። ለምሳሌ ባሏ በተገኘበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ቢኖርባት ራሷን በመሸፈን ለሥልጣኑ እውቅና እንደምትሰጥ ታሳያለች። ባሏ የተጠመቀም ሆነ አልሆነ የቤተሰቡ ራስ በመሆኑ ራሷን ትሸፍናለች። * ለአካለ መጠን ያልደረሰ የተጠመቀ ወንድ ልጇ በተገኘበት መጸለይ ወይም ማስተማር ቢኖርባት ራሷን ትሸፍናለች፤ ይህን የምታደርገው ልጇ የቤተሰቡ ራስ ስለሆነ ሳይሆን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ የተጠመቁ ወንዶች ላላቸው ሥልጣን አክብሮት እንዳላት ለማሳየት ነው።

ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ራሷን እንድትሸፍን የሚያስገድዷትን ሁኔታዎች በሚመለከት እንዲህ ብሏል:- “ማንም ሰው ሌላ ልማድ መከተል አለብን በሚል ለመከራከር ቢፈልግ እኛም ሆን የአምላክ ጉባኤ ከዚህ የተለየ ልማድ የለንም።” (ቁጥር 16) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የራስነት ሥልጣን የተሰጠው ለተጠመቁ ወንዶች ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:11-14፤ ዕብራውያን 13:17) አምላክ መንጋውን እንዲጠብቁ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች አድርጎ የሚሾመው ወንዶችን ብቻ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 20:28) ይሁን እንጂ አንዲት ክርስቲያን ሴት ብቃት ያለው የተጠመቀ ወንድ ሊያከናውን የሚገባውን ሥራ እንድትሠራ የሚጠይቅ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ለምሳሌ ብቃት ያለው የተጠመቀ ወንድ ባለመኖሩ ምክንያት የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ መምራት ይኖርባት ይሆናል። ወይም አንድን የተጠመቀ ወንድም ጋብዛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ትመራ ይሆናል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች ክርስቲያን ጉባኤ ከሚያከናውናቸው ተግባሮች መካከል የሚመደቡ በመሆናቸው ወንዶች ሊሠሩት የሚገባውን ሥራ በማከናወን ላይ መሆኗን ለማሳየት የራስ መሸፈኛ ታደርጋለች።

በሌላ በኩል ግን ከአምልኮ ጋር የተያያዙት ብዙዎቹ ሥራዎች አንዲት ሴት ራሷን እንድትሸፍን አይጠይቁባትም። ለምሳሌ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ስትሰጥ፣ ከባሏ ወይም ከሌላ የተጠመቀ ወንድ ጋር ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል፣ ወይም ያልተጠመቁ ልጆቿን ስታስጠና ወይም ከእነሱ ጋር ስትጸልይ ራሷን መሸፈን አያስፈልጋትም። እርግጥ ነው፣ በዚህ ዙሪያ ሊነሱ የሚችሉ ሌሎች ጥያቄዎች ይኖራሉ። በእነዚህ ጊዜያት አንዲት እህት ምን ማድረግ እንዳለባት  እርግጠኛ ካልሆነች ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ትችላለች። * አሁንም እርግጠኛ መሆን ካልቻለችና ሕሊናዋ ራሷን እንድትሸፍን ከነገራት በፎቶ ግራፉ ላይ እንደሚታየው ራሷን ብትሸፍን ምንም ስህተት የለበትም።

ራሷን እንድትሸፍን የሚያነሳሷት ምክንያቶች። “በመላእክት ምክንያት ሴት በሥልጣን ሥር መሆኗን የሚያሳይ ምልክት በራሷ ላይ ታድርግ” በሚለው በቁጥር 10 ላይ አንዲት ክርስቲያን ራሷን እንድትሸፍን የሚያስገድዷትን ሁለት ምክንያቶች እናገኛለን። በመጀመሪያ ደረጃ “በሥልጣን ሥር መሆኗን የሚያሳይ ምልክት” የሚለውን ሐረግ ልብ በል። አንዲት ክርስቲያን ሴት ራሷን መሸፈኗ ይሖዋ በጉባኤ ውስጥ ላሉ የተጠመቁ ወንዶች ለሰጠው ሥልጣን አክብሮት እንዳላት የምታሳይበት አንዱ መንገድ ነው። በዚህ መንገድ ለይሖዋ አምላክ ያላትን ፍቅርና ታማኝነት ታሳያለች። “በመላእክት ምክንያት” የሚለው ሐሳብ ደግሞ ሌላውን ምክንያት ይጠቁመናል። አንዲት ሴት ራሷን በመሸፈን ኃያላን የሆኑትን እነዚህን መንፈሳዊ ፍጡራን የሚጠቅም ነገር ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

መላእክት በመላው የይሖዋ ድርጅት ውስጥ፣ በሰማይም ሆነ በምድር መለኮታዊ ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ተከብሮ የማየት ፍላጎት አላቸው። በዚህ ረገድ ፍጹማን ያልሆኑ የሰው ልጆች የሚያሳዩት ምሳሌነት ይጠቅማቸዋል። እነሱም ቢሆኑ ለይሖዋ ዝግጅት መገዛት አለባቸው። ጥቂት የማይባሉ መላእክት በዚህ ፈተና ወድቀዋል። (ይሁዳ 6) መላእክት አንዲት ክርስቲያን ሴት በጉባኤ ውስጥ ካለ የተጠመቀ ወንድ የበለጠ ተሞክሮ፣ እውቀትና ማስተዋል ቢኖራትም ለሥልጣኑ በደስታ እንደምትገዛ ሊመለከቱ ይችላሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ሴቷ ወደፊት የክርስቶስን መንግሥት የምትወርስ በመንፈስ የተቀባች ክርስቲያን ልትሆን ትችላለች። ይህች ሴት በዚያን ወቅት መላእክት እንኳ ካላቸው የበለጠ ቦታ በመያዝ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ትገዛለች። ይህ ለመላእክት ጥሩ ምሳሌ ነው! ሁሉም እህቶች ታማኝ፣ ተገዥና ታዛዥ በመሆን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ታማኝ መላእክት አርዓያ መሆን መቻላቸው እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

^ አን.3 አንዲት ክርስቲያን ሴት ባሏ በሕመም ምክንያት መናገር ስለተሳነው ወይም በመሳሰሉት ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር አማኝ ባሏ ባለበት ጮክ ብላ አትጸልይም።

^ አን.2 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሐምሌ 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 26-27ን እንዲሁም የየካቲት 15, 1977 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 125-128ን ተመልከት።