በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 15

ከሥራህ እርካታን ማግኘት ትችላለህ

ከሥራህ እርካታን ማግኘት ትችላለህ

‘ሰው ሁሉ ከሚደክምበት ነገር እርካታን ማግኘት አለበት።መክብብ 3:13

1-3. (ሀ) ብዙ ሰዎች ስለ ሥራቸው ምን ይሰማቸዋል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥራ ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ይመክራል? በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

በዛሬው ጊዜ ሥራ ለብዙዎች የሚያስደስት ነገር አይደለም። በርካታ ሰዎች ደስ በማይሰኙበት ሥራ ላይ ቀኑን ሙሉ ደፋ ቀና እያሉ ስለሚውሉ በየዕለቱ ወደ ሥራ የሚሄዱት ግዴታ ስለሆነባቸው ብቻ ነው። ይህን የመሰለ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ሥራቸውን በጥሩ መንፈስ ለመሥራት ብሎም ከሥራቸው እርካታ ለማግኘት ምን ማድረግ ይችላሉ?

2 መጽሐፍ ቅዱስ ለሥራ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረን ያበረታታናል። ሥራና ከሥራ የሚገኘው ፍሬ በረከት እንደሆኑ ይናገራል። ሰለሞን “ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ [የአምላክ] ችሮታ ነው” ሲል ጽፏል። (መክብብ 3:13) የሚወደንና ምንጊዜም የሚበጀንን የሚያስብልን አምላካችን ይሖዋ በሥራችን እንድንረካና በድካማችን ፍሬ እንድንደሰት ይፈልጋል። ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ከፈለግን እሱ ስለ ሥራ ያለው አመለካከት ሊኖረንና በዚህ ረገድ የሰጠንን መሠረታዊ ሥርዓቶች ልንከተል ይገባል።መክብብ 2:24፤ 5:18

3 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ አራት ጥያቄዎችን እንመረምራለን:- ከሥራችን እርካታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ተገቢ የማይሆኑት ምን ዓይነት ሥራዎች ናቸው? ሰብዓዊ ሥራችን ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምናውለውን ጊዜ እንዳይሻማብን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ልንሠራ ከምንችላቸው ሥራዎች በሙሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የትኛው ነው? በመጀመሪያ ግን በመላው አጽናፈ  ዓለም ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ታላላቅ ሠራተኞች የሆኑት ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ የተዉትን ምሳሌ እንመልከት።

አቻ የማይገኝለት ሠራተኛና ዋና ሠራተኛ

4, 5. መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ውጤታማ ሠራተኛ መሆኑን የሚያመለክተው እንዴት ነው?

4 ይሖዋ አቻ የማይገኝለት ሠራተኛ ነው። ዘፍጥረት 1:1 ‘በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ’ ይላል። አምላክ ከምድር ጋር በተያያዘ ያከናወነውን የፍጥረት ሥራ ባጠናቀቀ ጊዜ “እጅግ መልካም ነበረ” በማለት ውጤቱን ገልጿል። (ዘፍጥረት 1:31) በሌላ አነጋገር በምድር ላይ በሠራቸው ሥራዎቹ ሙሉ በሙሉ ረክቷል ማለት ነው። ‘ደስተኛ አምላክ’ የሆነው ይሖዋ ውጤታማ ሥራ መሥራቱ እጅግ እንዳስደሰተው የተረጋገጠ ነው።1 ጢሞቴዎስ 1:11

5 ትጉ ሠራተኛ የሆነው አምላካችን መሥራቱን አያቆምም። ከምድር ጋር በተያያዘ ያከናወነውን የፍጥረት ሥራ ካጠናቀቀ ከረጅም ጊዜ በኋላ ኢየሱስ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 5:17) አብ ሲሠራ የነበረው ነገር ምንድን ነው? በሰማይ በሚገኘው ዙፋኑ ሆኖ ለሰው ልጆች አመራር ሲሰጥና እንክብካቤ ሲያደርግላቸው እንደቆየ የተረጋገጠ ነው። ከዚህም በላይ “አዲስ ፍጥረት” ማለትም ወደፊት ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚገዙ በመንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖችን አስገኝቷል። (2 ቆሮንቶስ 5:17) አምላክ እሱን የሚወዱ ሰዎች በአዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ የማድረግ ዓላማ አለው፤ ባለፉት ዘመናት ይህን ዓላማውን ወደ ፍጻሜ ለማድረስ የሚያስችለውን መንገድ ሲያመቻች ቆይቷል። (ሮም 6:23) ይሖዋ ይህ ሥራ ባስገኘው ውጤት እንደተደሰተ ምንም ጥርጥር የለውም። አምላክ ወደ ራሱ የሳባቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ተቀብለው ከእሱ ፍቅር ሳይወጡ ለመኖር የሚያስችላቸውን ማስተካከያ አድርገዋል።ዮሐንስ 6:44

6, 7. ኢየሱስ ተግቶ በመሥራት ረገድ ምን የረጅም ጊዜ ታሪክ አስመዝግቧል?

6 ኢየሱስ ትጉ ሠራተኛ በመሆን የረዥም ዘመን ታሪክ አስመዝግቧል። ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት “በሰማያትና በምድር ያሉ” ነገሮች በሙሉ በተፈጠሩበት ጊዜ የአምላክ “ዋና ባለሙያ [“ሠራተኛ፣”  የ1954 ትርጉም]” ሆኖ አገልግሏል። (ምሳሌ 8:22-31፤ ቆላስይስ 1:15-17) ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜም ታታሪ ሠራተኛ ነበር። ገና በወጣትነቱ የአናጺነት ሙያ ተምሮ ስለነበር “አናጺው” * ተብሎ ተጠርቷል። (ማርቆስ 6:3) ይህ ሥራ በተለይ የእንጨት መሰንጠቂያዎች፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ መሣሪያዎች፣ እንዲሁም የግንባታ ሸቀጣሸቀጦች የሚሸጡባቸው መደብሮች ባልነበሩበት በዚያ ዘመን በጣም አድካሚና የተለያዩ ችሎታዎችን የሚጠይቅ ነበር። ኢየሱስ ለሥራ የሚያስፈልገውን እንጨት ለማግኘት ወደ ጫካ ሄዶ ዛፍ ሲቆርጥና የቆረጠውን እንጨት ወደሚሠራበት ቦታ ተሸክሞ ሲያመጣ ይታይህ። ቤት ለመሥራት የጣሪያውን ማገር ሲያዋቅርና በሮቹን፣ አልፎ ተርፎም የቤት ዕቃዎቹን ሲሠራ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ኢየሱስ፣ የተዋጣለት ሥራ ለመሥራት መትጋት ከፍተኛ እርካታ እንደሚያስገኝ ከራሱ ተሞክሮ እንደተመለከተ ጥርጥር የለውም።

7 ኢየሱስ አገልግሎቱን በማከናወን ረገድም ትጉ ሠራተኛ ነበር። ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በዚህ በጣም አስፈላጊ ሥራ ተጠምዶ ነበር። በተቻለው መጠን ለብዙ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ለማዳረስ ሲል ማልዶ በመነሳትና ከመሸ በኋላም ጭምር በመሥራት ጊዜውን በሚገባ ተጠቅሞበታል። (ሉቃስ 21:37, 38፤ ዮሐንስ 3:2) “የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከና እያወጀ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ይጓዝ ነበር።” (ሉቃስ 8:1) ኢየሱስ ምሥራቹን ለሰዎች ለመስበክ ሲል አቧራማ በሆኑ ጎዳናዎች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች በእግሩ ተጉዟል።

8, 9. ኢየሱስ ከሠራው ሥራ እርካታ ያገኘው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ በትጋት ማገልገሉ እርካታ አስገኝቶለታል? አዎ! የመንግሥቱን የእውነት ዘር የዘራ ሲሆን ምድራዊ አገልግሎቱን ባጠናቀቀበት ጊዜ የዘራው ዘር አድጎ ለአጨዳ የደረሰ አዝመራ ሆኖ ነበር። የአምላክን ሥራ መሥራት ለኢየሱስ ብርታትና ጥንካሬ ያስገኝለት ስለነበር ይህን ሥራ ለማከናወን ሲል ምግቡን እንኳ ለመተው ፈቃደኛ ነበር። (ዮሐንስ  4:31-38) ምድራዊ አገልግሎቱን ባጠናቀቀበት ወቅት “እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርኩህ” ብሎ ለአባቱ አፉን ሞልቶ መናገር መቻሉ ምን ያህል አስደስቶት ሊሆን እንደሚችል አስብ።ዮሐንስ 17:4

9 በእርግጥም ከሥራ እርካታ በማግኘት ረገድ ከይሖዋና ከኢየሱስ የበለጠ ምሳሌ ሊገኝ አይችልም። ለይሖዋ ያለን ፍቅር ‘እሱን እንድንኮርጅ’ ያነሳሳናል። (ኤፌሶን 5:1) ለኢየሱስም ያለን ፍቅር ‘የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድንከተል’ ይገፋፋናል። (1 ጴጥሮስ 2:21) አሁን ደግሞ እኛም ከሥራችን እንዴት እርካታ ማግኘት እንደምንችል እንመርምር።

ከሥራችን እርካታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ማዋል ከድካምህ እርካታ እንድታገኝ ይረዳሃል

10, 11. ለሥራችን አዎንታዊ የሆነ አመለካከት እንድናዳብር ምን ሊረዳን ይችላል?

10 ሰብዓዊ ሥራ በአንድ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የራሱ የሆነ ቦታ አለው። ከምንሠራው ሥራ የተወሰነ እርካታ ማግኘት እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ ሥራችንን የማንወደው ከሆነ እርካታ ማግኘት አስቸጋሪ ይሆንብናል። እንዲህ ባለው ሁኔታ ከሥራችን እርካታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

11 አዎንታዊ አመለካከት በማዳበር። ያለንበትን ሁኔታ መለወጥ ሁልጊዜ ባይሳካልንም አመለካከታችንን ግን መለወጥ እንችላለን። አምላክ ለሥራ ባለው አመለካከት ላይ ማሰላሰላችን አዎንታዊ አመለካከት እንድናዳብር ይረዳናል። ለምሳሌ፣ የቤተሰብ ራስ ከሆንክ የምትሠራው ሥራ ምንም ያህል ዝቅተኛ መስሎ ቢታይ የቤተሰብህን ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችልህ አስብ። ቤተሰብህን መንከባከብ በአምላክ ዓይን እንደ ቀላል ነገር የሚታይ አይደለም። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን የማያቀርብ ሰው “እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ” እንደሆነ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ሥራህ ከአምላክ የተጣለብህን ኃላፊነት እንድትወጣ የሚያስችልህ መሆኑን መገንዘብህ በዓላማ እንድትሠራ የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ የሥራ ባልደረቦችህ የሌላቸውን እርካታ ያስገኝልሃል።

12. በሥራችን ትጉና ሐቀኛ መሆናችን በረከት የሚያስገኝልን በምን መንገዶች ነው?

 12 ትጉና ሐቀኛ በመሆን። ጠንክረን መሥራታችን እንዲሁም ሥራችንን እንዴት በጥሩ ሁኔታ ማከናወን እንደምንችል መማራችን በረከት ያስገኝልናል። ትጉ የሆኑና ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሠራተኞች አብዛኛውን ጊዜ በአሠሪዎቻቸው ዘንድ ይወደዳሉ። (ምሳሌ 12:24፤ 22:29) በተጨማሪም እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከአሠሪያችን ገንዘብ፣ የሥራ ሰዓት ወይም ዕቃ ባለመስረቅ ሐቀኞች መሆን ይገባናል። (ኤፌሶን 4:28) ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው ሐቀኝነት በረከት ያስገኛል። በሐቀኝነቱ የሚታወቅ ሠራተኛ እምነት ይጣልበታል። አሠሪያችን ትጉ ሠራተኞች መሆናችንን አስተዋለም  አላስተዋለ “ሐቀኛ ሕሊና” ያለን መሆኑ እንዲሁም የምንወደውን አምላክ ደስ እያሰኘን እንዳለን ማወቃችን ያስደስተናል።ዕብራውያን 13:18፤ ቆላስይስ 3:22-24

13. በሥራ ቦታ የምናሳየው ጥሩ ጠባይ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

13 ጠባያችን ለአምላክ ክብር ሊያመጣ እንደሚችል በመገንዘብ። በሥራ ቦታችን ጥሩ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የምናሳይ ከሆነ ሌሎች ይህን ማስተዋላቸው አይቀርም። ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል? ‘አዳኛችን የሆነውን አምላክ ትምህርት እናስውባለን።’ (ቲቶ 2:9, 10) አዎ፣ ጥሩ ጠባያችን ሌሎች ሰዎች አምልኳችን ያለውን ውበት እንዲመለከቱና ወደ አምላካችን እንዲሳቡ ሊያደርጋቸው ይችላል። በሥራ ቦታ በምታሳየው መልካም ጠባይ ምክንያት አንድ የሥራ ባልደረባህ እውነትን ቢቀበል ምን ሊሰማህ እንደሚችል አስብ! ከሁሉም በላይ መልካም ጠባይህ ለይሖዋ ክብር እንደሚያመጣ እንዲሁም ልቡን ደስ እንደሚያሰኝ ማወቅህ ትልቅ በረከት ነው።ምሳሌ 27:11፤ 1 ጴጥሮስ 2:12

በሥራ ምርጫ ረገድ አስተዋይ መሆን

14-16. ሥራን በሚመለከት ምርጫ በምናደርግበት ጊዜ ልናስብባቸው የሚገቡ ወሳኝ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?

14 መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውንና የሌላቸውን የሥራ ዓይነቶች በተመለከተ ዝርዝር መመሪያ አይሰጥም። ይህ ሲባል ግን ማንኛውንም ዓይነት ሥራ መሥራት እንችላለን ማለት አይደለም። ቅዱሳን መጻሕፍት አምላክ የሚደሰትባቸውን ውጤታማ የሆኑና በሐቅ ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች እንድንመርጥ፣ እሱ ከማይደሰትባቸው ሥራዎች ደግሞ እንድንርቅ ይረዱናል። (ምሳሌ 2:6) የሥራ ምርጫ በምናደርግበት ጊዜ ልናስብባቸው የሚገቡ ሁለት ወሳኝ ጥያቄዎች አሉ።

15 ይህን ሥራ መሥራት በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወገዘን ድርጊት እንደመፈጸም ይቆጠራል? የአምላክ ቃል መስረቅን፣ መዋሸትንና የአምልኮ ምሥሎችን መሥራትን በግልጽ ያወግዛል። (ዘፀአት 20:4፤ የሐዋርያት ሥራ 15:29፤ ኤፌሶን 4:28፤ ራእይ 21:8) እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እንድናደርግ የሚጠይቅብንን ማንኛውንም ዓይነት ሥራ አንሠራም። ለይሖዋ ያለን ፍቅር የአምላክን ትእዛዛት በሚያስጥሱን  ድርጊቶች እንድንካፈል በሚያደርጉን ሥራዎች ላይ እንዳንሰማራ ያደርገናል።1 ዮሐንስ 5:3

16 ይህን ሥራ መሥራት የአንድ መጥፎ ድርጊት ተባባሪ ወይም አራማጅ ያደርገናል? አንድ ምሳሌ እንመልከት። እንግዳ ተቀባይ ሆኖ መሥራት በራሱ ስህተት አይደለም። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ውርጃ በሚፈጸምበት ክሊኒክ ውስጥ እንግዳ ተቀባይ ሆኖ ቢሠራስ? ይህ የሥራ ምድብ ጽንስ በማስወረድ ድርጊት በቀጥታ እንዲካፈል እንደማይጠይቅበት የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ክርስቲያን ዘወትር በሚያከናውነው  ሥራ አማካኝነት ክሊኒኩ የአምላክ ቃል የሚከለክለውን ጽንስ የማስወረድ ተግባር እንዲፈጽም ድጋፍ እየሰጠ አይደለም? (ዘፀአት 21:22-24) ይሖዋን ስለምንወደው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያወግዛቸው ድርጊቶች ጋር በቅርብ የሚያገናኘንን ሥራ መሥራት አንፈልግም።

17. (ሀ) የሥራ ምርጫ በምናደርግበት ጊዜ ግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው? (“ ይህን ሥራ መሥራት ይኖርብኛል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) ሕሊናችን አምላክን የሚያስደስት ውሳኔ እንድናደርግ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

17 በአንቀጽ 15 እና 16 ላይ ለሚገኙት ሁለት ወሳኝ ጥያቄዎች የተሰጡትን መልሶች በጥንቃቄ ማመዛዘን ከሥራ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ለአብዛኞቹ ጥያቄዎች መፍትሔ ለማግኘት ያስችላል። ከዚህ በተጨማሪ የሥራ ምርጫ በምናደርግበት ጊዜ ከግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገቡ ሌሎች ነገሮች አሉ። * ታማኝና ልባም ባሪያ ሊያጋጥመን ለሚችለው  ለእያንዳንዱ ሁኔታ የሚሠራ መመሪያ እንዲያወጣልን ልንጠብቅ አንችልም። ማስተዋል የሚያስፈልገን እዚህ ላይ ነው። በምዕራፍ 2 ላይ እንደተማርነው የአምላክን ቃል በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንዴት ሥራ ላይ ማዋል እንደምንችል በማጥናት ሕሊናችንን ማሠልጠን ያስፈልገናል። ‘የማስተዋል ችሎታችንን’ በዚህ መንገድ “በማሠራት” ስናሠለጥነው ሕሊናችን አምላክን የሚያስደስትና ከእሱ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር የሚያስችለንን ውሳኔ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል።ዕብራውያን 5:14

ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

18. መንፈሳዊ ሚዛንን ጠብቆ መመላለስ ቀላል ያልሆነው ለምንድን ነው?

18 ‘በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን’ እንደሚመጣ የተነገረ ሲሆን በዚህ ዘመን መንፈሳዊ ሚዛንን ጠብቆ መመላለስ ቀላል አይደለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ሥራ ማግኘትም ሆነ በሥራ ገበታ ላይ መቆየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ጠንክረን መሥራታችን አስፈላጊ መሆኑን እንገነዘባለን። ይሁንና ጠንቃቆች ካልሆን በሥራ ቦታ የሚያጋጥመን ተጽዕኖ ወይም በዓለም እንደ ወረርሽኝ እየተስፋፋ ያለው ቁሳዊ አስተሳሰብ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ እንዳናተኩር እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” ለይተን በማወቅ ሚዛናችንን እንዴት መጠበቅ እንደምንችል እንመልከት።ፊልጵስዩስ 1:10

19. ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ልንታመንበት የሚገባ አምላክ ነው የምንለው ለምንድን ነው? በይሖዋ ላይ እንዲህ ያለ እምነት መጣላችን ምን እንድናስወግድ ይረዳናል?

19 ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታመን። (ምሳሌ 3:5, 6) ይሖዋ እምነት ሊጣልበት የሚገባው አምላክ ነው ቢባል አትስማማም? የሚንከባከበን እሱ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:7) የሚያስፈልገንን ከእኛ በላይ ያውቃል፤ በተጨማሪም እጁ አጭር አይደለም። (መዝሙር 37:25) ስለሆነም ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ሲል የሰጠንን ማሳሰቢያ መስማታችን ተገቢ ነው:- “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ አሁን ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ። ምክንያቱም [አምላክ] ‘ፈጽሞ አልተውህም፣ በምንም ዓይነት አልጥልህም’ ብሏል።” (ዕብራውያን 13:5)  በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ በርካታ ክርስቲያኖች አምላክ ለኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮችን የመስጠት ችሎታ እንዳለው ሊመሠክሩ ይችላሉ። ይሖዋ የሚያስፈልገንን እንደሚሰጠን ሙሉ በሙሉ ከታመንበት ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ስለማቅረብ ከልክ በላይ አንጨነቅም። (ማቴዎስ 6:25-32) ሰብዓዊ ሥራ ምሥራቹን እንደ መስበክና በስብሰባዎች ላይ እንደ መገኘት ያሉትን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ችላ  እንድንል እንዲያደርገን ፈጽሞ አንፈቅድም።ማቴዎስ 24:14፤ ዕብራውያን 10:24, 25

20. አጥርቶ የሚያይ ዓይን ይኑረን ሲባል ምን ማለት ነው? እንዲህ ያለውን አመለካከት ልታዳብር የምትችለውስ እንዴት ነው?

20 አጥርቶ የሚያይ ዓይን ይኑርህ። (ማቴዎስ 6:22, 23) አጥርቶ የሚያይ ዓይን ይኑረን ሲባል አኗኗራችንን ከሚያወሳስብ ነገር እንራቅ ማለት ነው። አንድ ክርስቲያን አጥርቶ የሚያይ ዓይን ካለው በአንድ ነገር ላይ ይኸውም የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ብቻ ያተኩራል። ዓይናችን ትክክለኛው ነገር ላይ ያነጣጠረ ከሆነ በጣም ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ ለማግኘት ወይም የተንደላቀቀ ኑሮ ለመኖር አንራወጥም። ወይም የማስታወቂያው ዓለም ‘ይህን ካላገኘህ ምኑን ኖርከው’ በማለት የሚያቀርባቸውን ቴክኖሎጂ ያፈራቸውን ምርጥ ነገሮች ለማግኘት አንሮጥም። ታዲያ አጥርቶ የሚያይ ዓይን እንዲኖርህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ አትግባ። ከመጠን ያለፈ ጊዜና ትኩረት የሚጠይቅ ዕቃና ንብረት በመሰብሰብ ሕይወትህን አታጨናንቅ። “ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ” ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን እንድንኖር የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተከተል። (1 ጢሞቴዎስ 6:8) በተቻለህ መጠን ሕይወትህን ቀላል ለማድረግ ጥረት አድርግ።

21. ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን መወሰን የሚኖርብን ለምንድን ነው? በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ መያዝ የሚገባው ምንድን ነው?

21 ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ መንፈሳዊ ነገሮችን ወስንና በውሳኔህ ጽና። በሕይወታችን ልናከናውን የምንችላቸው ነገሮች ውስን ስለሆኑ ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡትን ነገሮች መወሰን ይኖርብናል። እንዲህ ካላደረግን ያን ያህል አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮች ውድ የሆነውን ጊዜያችንን ይወስዱብንና ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ጊዜ እናጣለን። በሕይወታችን የመጀመሪያውን ቦታ ሊይዝ የሚገባው ምንድን ነው? በዚህ ዓለም ውስጥ ብዙዎች ጥሩ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ ለማግኘት ይጠቅማል ብለው ስለሚያስቡ ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል የመጀመሪያውን ቦታ ይሰጣሉ። ይሁንና ኢየሱስ ተከታዮቹን “ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት . . . መፈለጋችሁን ቀጥሉ” በማለት አበረታቷቸዋል። (ማቴዎስ 6:33) አዎ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ መንግሥት የመጀመሪያውን ቦታ እንሰጣለን።  አኗኗራችን ማለትም የምናደርጋቸው ምርጫዎች፣ የምናወጣቸው ግቦችና እንቅስቃሴዎቻችን የመንግሥቱ ጉዳዮች እንዲሁም የአምላክ ፈቃድ ከቁሳዊ ነገሮች ወይም ከሥራና ከትምህርት እንደሚበልጡብን የሚያሳዩ መሆን ይገባቸዋል።

በአገልግሎት በትጋት መካፈል

በሕይወታችን ውስጥ ለስብከቱ ሥራ የመጀመሪያውን ቦታ በመስጠት ለይሖዋ ፍቅር እንዳለን ልናሳይ እንችላለን

22, 23. (ሀ) የእውነተኛ ክርስቲያኖች ዋነኛ ሥራ ምንድን ነው? ይህ ሥራ በጣም አስፈላጊ መሆኑን እንደምናምን የምናሳየው እንዴት ነው? (“ ያደረግኩት ውሳኔ በሕይወቴ ደስታና እርካታ እንዳገኝ አስችሎኛል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) በሰብዓዊ ሥራ ረገድ ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?

22 ወደ ፍጻሜው በጣም እንደቀረብን ስለምናውቅ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች በተሰጠው ዋነኛ ሥራ ማለትም በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ እናተኩራለን። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም በዚህ ሕይወት አድን ሥራ መጠመድ እንፈልጋለን። ይህ ሥራ በጣም አስፈላጊ መሆኑን እንደምናምን የምናሳየው እንዴት ነው? አብዛኞቹ የአምላክ ሕዝቦች የጉባኤ አስፋፊዎች በመሆን የስብከቱን ሥራ በሙሉ ልባቸው ያከናውናሉ። አንዳንዶች ሁኔታቸውን በማስተካከል አቅኚዎች ወይም ሚስዮናውያን ሆነው ማገልገል ችለዋል። ብዙ ወላጆች መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን ስለሚገነዘቡ ልጆቻቸው የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን የዕድሜ ልክ ሥራቸው እንዲያደርጉ አበረታተዋቸዋል። ታዲያ እነዚህ ቀናተኛ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ከሥራቸው እርካታ አግኝተዋል? አዎ፣ አግኝተዋል! ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገል ደስታ፣ እርካታና ተቆጥሮ የማያልቅ በረከት የሚያስገኝ አስተማማኝ የሕይወት መንገድ ነው።ምሳሌ 10:22

23 ብዙዎቻችን ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ለማቅረብ ብዙ ሰዓት መሥራት ይጠበቅብናል። ይሖዋ ከሥራችን እርካታ እንድናገኝ እንደሚፈልግ አስታውስ። አመለካከታችንንም ሆነ ድርጊታችንን ከአምላክ አመለካከትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በማስማማት ከሥራችን እርካታ ማግኘት እንችላለን። እንግዲያው ሰብዓዊ ሥራችን ከዋነኛው ሥራችን፣ ማለትም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከማወጁ ሥራ እንዳያዘናጋን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። በሕይወታችን ውስጥ ለዚህ ሥራ የመጀመሪያውን ቦታ በመስጠት ለይሖዋ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። እንዲሁም ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር እንችላለን።

^ አን.6 “አናጺ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ቤቶችን ወይም የቤት ዕቃዎችን ወይም ማንኛውንም የእንጨት ሥራ የሚሠራን ሰው የሚያመለክት ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ስያሜ ነው።”

^ አን.17 ሥራን በሚመለከት ልናገናዝባቸው ስለሚገቡ ነገሮች ዝርዝር ሐሳብ ለማግኘት የሚያዝያ 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 28-30ን እና የሐምሌ 15, 1982 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 26ን ተመልከት።