“ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል።”ምሳሌ 13:20

1-3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ምን ሊታበል የማይችል ሐቅ ይናገራል? (ለ) በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን የሚችሉ ጓደኞችን መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው?

በአንዳንድ መንገዶች እኛ ሰዎች ልክ እንደ ስፖንጅ ነን ማለት ይቻላል። በዙሪያችን ያለውን ማንኛውንም ነገር መጥጠን የማስቀረት ባሕርይ አለን። የምንቀርባቸውን ሰዎች ዝንባሌ፣ አቋምና ጠባይ ሳይታወቀን በቀላሉ እንኮርጃለን።

2 መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል” በማለት ሊታበል የማይችል ሐቅ አስፍሮልናል። (ምሳሌ 13:20) ይህ ምሳሌ የሚናገረው ስለ ተራ ትውውቅ አይደለም። “የሚሄድ” የሚለው ቃል ረዘም ላለ ጊዜ የዘለቀን ወዳጅነት ያመለክታል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ ጽሑፍ ስለዚህ ጥቅስ አስተያየት ሲሰጥ “ከአንድ ሰው ጋር መሄድ ፍቅርና የስሜት ትስስር መኖሩን ያመለክታል” ብሏል። የምንወዳቸውን ሰዎች የመምሰል ዝንባሌ አለን ቢባል አትስማማም? በእርግጥም ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ስሜታዊ ትስስር ስለሚኖረን በበጎም ሆነ በመጥፎ ሊቀርጹን ይችላሉ።

3 ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ከፈለግን በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን የሚችሉ ጓደኞች መፈለግ ይኖርብናል። ይህን ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው? በአጭር አነጋገር አምላክ የሚወዳቸውን ሰዎች በመውደድና የእሱን ወዳጆች ወዳጆቻችን በማድረግ ነው። እስቲ አስበው! ይሖዋ የሚወደው ዓይነት ባሕርይ ካላቸው ሰዎች የተሻሉ ጓደኞች ማግኘት እንችላለን? አሁን አምላክ የሚወደው እንዴት ያሉ ሰዎችን እንደሆነ እንመርምር። ይሖዋ በዚህ ረገድ ምን አመለካከት እንዳለው  በሚገባ ከተገነዘብን በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን የሚችሉ ጓደኞችን መምረጥ አስቸጋሪ አይሆንብንም።

አምላክ የሚወዳቸው ሰዎች

4. ይሖዋ ወዳጆቹ የሚሆኑትን ሰዎች የመምረጥ መብት አለው የምንለው ለምንድን ነው? ይሖዋ አብርሃምን “ወዳጄ” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው?

4 ይሖዋ ወዳጆቹ የሚሆኑትን ሰዎች በጥንቃቄ ይመርጣል። ደግሞም ይህን የማድረግ መብት አለው። ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ነው፤ በመሆኑም የእሱ ወዳጅ መሆን ተወዳዳሪ የማይገኝለት ታላቅ መብት ነው። ታዲያ ወዳጆቹ እንዲሆኑ የሚመርጠው እንዴት ያሉ ሰዎችን ነው? ይሖዋ የሚመኩበትንና ሙሉ እምነት የሚጥሉበትን ሰዎች ይቀርባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ከፍተኛ እምነት እንደነበረው የሚታወቀውን አብርሃምን እንውሰድ። ለአንድ ሰብዓዊ አባት ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ከመጠየቅ የሚከብድ የእምነት ፈተና ሊኖር አይችልም። * ሆኖም አብርሃም “አምላክ ከሞት እንኳ ሳይቀር ሊያስነሳው እንደሚችል” ሙሉ እምነት ስለነበረው ‘ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ’ ፈቃደኛ ሆኗል። (ዕብራውያን 11:17-19) አብርሃም ይህን የመሰለ ትልቅ እምነትና ታዛዥነት ስላሳየ ይሖዋ “ወዳጄ” ብሎ በመጥራት ለእሱ ያለውን ፍቅር ገልጿል።ኢሳይያስ 41:8፤ ያዕቆብ 2:21-23

5. ይሖዋ እሱን በታማኝነት የሚታዘዙትን እንዴት ይመለከታቸዋል?

5 ይሖዋ ከታማኝነት ለሚመነጭ ታዛዥነት ትልቅ ቦታ ይሰጣል። አምላክ፣ ከምንም በላይ ለእሱ ታማኝ ለመሆን የሚመርጡ ሰዎችን ይወዳል። (2 ሳሙኤል 22:26) በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ በፍቅር ተነሳስተው እሱን ለመታዘዝ በሚመርጡ ሰዎች በጣም ይደሰታል። ምሳሌ 3:32 ወዳጅነቱ ‘ከቅኖች’ ጋር እንደሆነ  ይናገራል። ይሖዋ ብቃቶቹን በታማኝነት ለሚያሟሉ ሁሉ ‘በድንኳኑ’ እንዲያድሩ በደግነት ግብዣ ያቀርብላቸዋል። ይህም ማለት እሱን ለማምለክና በማንኛውም ጊዜ ወደ እሱ በጸሎት ለመቅረብ መብት ያገኛሉ።መዝሙር 15:1-5

6. ኢየሱስን እንደምንወድ እንዴት ልናሳይ እንችላለን? ይሖዋስ ልጁን ስለሚወዱ ሰዎች ምን ይሰማዋል?

6 ይሖዋ አንድያ ልጁ የሆነውን ኢየሱስን የሚወዱትን ይወዳል። ኢየሱስ “ማንም ሰው እኔን የሚወደኝ ከሆነ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፣ እኛም ወደ እሱ መጥተን መኖሪያችንን ከእሱ ጋር እናደርጋለን” ብሏል። (ዮሐንስ 14:23) ኢየሱስን እንደምንወድ እንዴት ማሳየት እንችላለን? ምሥራቹን እንድንሰብክና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠንን ተልእኮ ጨምሮ የኢየሱስን ትእዛዛት በመጠበቅ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 14:15, 21) በተጨማሪም ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም አቅማችን የፈቀደልንን ያህል በቃልም ሆነ በድርጊት ኢየሱስን በመምሰል ‘ፈለጉን በጥብቅ ስንከተል’ እንደምንወደው እናሳያለን። (1 ጴጥሮስ 2:21) ይሖዋ ለክርስቶስ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው የኢየሱስን ፈለግ ለመከተል ጥረት በሚያደርጉ ሰዎች ይደሰታል።

7. የይሖዋ ወዳጆች የሆኑ ሰዎችን ለጓደኝነት መምረጣችን አስተዋይነት የሆነው ለምንድን ነው?

7 ይሖዋ ወዳጆቹ እንዲኖሯቸው ከሚፈልጋቸው ባሕርያት መካከል እምነት፣ ታማኝነት፣ ታዛዥነት እንዲሁም ኢየሱስንና የአቋም ደረጃዎቹን መውደድ ይገኙበታል። እያንዳንዳችን ‘የቅርብ ጓደኞቼ እነዚህ ባሕርያት አሏቸው? ጓደኞቼ የይሖዋ ወዳጆች ናቸው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። የይሖዋ ወዳጆች የሆኑ ሰዎችን ለጓደኝነት መምረጣችን አስተዋይነት ነው። አምላካዊ ባሕርያትን የሚኮተኩቱና የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት የሚሰብኩ ሰዎች አምላክን ለማስደሰት ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ እንድንጸና በመርዳት በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይችላሉ።—“ ጥሩ ጓደኛ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

 ከአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ትምህርት ማግኘት

8. (ሀ) ኑኃሚንና ሩት፣ (ለ) ሦስቱ ወጣት ዕብራውያን፣ (ሐ) ጳውሎስና ጢሞቴዎስ ስለነበራቸው ወዳጅነት ከሚገልጸው ታሪክ ልብህን የሚነካው ምንድን ነው?

8 መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ወዳጆች በመምረጣቸው ምክንያት ስለተጠቀሙ ሰዎች የሚገልጹ በርካታ ታሪኮችን ይዞልናል። ኑኃሚንና ምራቷ ሩት፣ በባቢሎን ሳይነጣጠሉ የኖሩት ሦስቱ ወጣት ዕብራውያን፣ እንዲሁም ጳውሎስና ጢሞቴዎስ ስለነበራቸው ወዳጅነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበውን ታሪክ ማንበብ ትችላለህ። (ሩት 1:16፤ ዳንኤል 3:17, 18፤ 1 ቆሮንቶስ 4:17፤ ፊልጵስዩስ 2:20-22) ይሁን እንጂ ጎላ ብሎ የሚታይ አንድ ሌላ ምሳሌ ይኸውም ዳዊትና ዮናታን የነበራቸውን ወዳጅነት እንመልከት።

9, 10. ዳዊትና ዮናታን ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ያስቻላቸው ምን ነበር?

9 መጽሐፍ ቅዱስ ዳዊት ጎልያድን ከገደለው በኋላ “የዮናታን ነፍስ ከዳዊት ነፍስ ጋር ተቆራኘች፤ እንደራሱም አድርጎ ወደደው” ይላል። (1 ሳሙኤል 18:1) በመካከላቸው ሰፊ የዕድሜ ልዩነት የነበረ ቢሆንም እንኳ ዮናታን በጦር ሜዳ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ የቀጠለ ጠንካራ ወዳጅነት የተጀመረው በዚህ ሁኔታ ነበር። * (2 ሳሙኤል 1:26) እነዚህ ሁለት ጓደኛሞች ይህን የመሰለ ጠንካራ ዝምድና እንዲመሠርቱ ያስቻላቸው ምን ነበር?

10 ዳዊትንና ዮናታንን ያስተሳሰራቸው ለአምላክ ያላቸው ፍቅርና ለእሱ ታማኝ ሆነው ለመኖር የነበራቸው ጠንካራ ፍላጎት ነው። እነዚህን ሰዎች ያቆራኛቸው መንፈሳዊ መሆናቸው ነው። ሁለቱም አንዳቸው በሌላው እንዲወደዱ ያደረጓቸው ባሕርያት ነበሯቸው። ዮናታን፣ ያላንዳች ፍርሃት ለይሖዋ ስም የቆመው ወጣት ያሳየው ድፍረትና ቅንዓት እንደማረከው ምንም ጥርጥር የለውም። ዳዊትም በበኩሉ የይሖዋን ዝግጅት በታማኝነት የደገፈውንና ከገዛ ራሱ ጥቅም ይልቅ የእሱን  ጥቅም ያስቀደመውን ይህን በዕድሜ ጠና ያለ ሰው በጥልቅ ያከብር እንደነበር ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ዳዊት ክፉ ንጉሥ ከነበረው ከዮናታን አባት ከሳኦል ቁጣ ሸሽቶ በምድረ በዳ ይንከራተት በነበረበትና ተስፋ በቆረጠበት የመከራ ጊዜ የሆነውን እንመልከት። በዚህ ወቅት ዮናታን አስደናቂ የሆነ ታማኝነት በማሳየት በራሱ ተነሳስቶ “ዳዊት ወዳለበት ወደ ሖሬሽ ሄዶ፣ [በአምላክ፣ NW] ስም አበረታታው።” (1 ሳሙኤል 23:16) ዳዊት በጣም የሚወደው ጓደኛው መጥቶ  ባጽናናውና ባበረታታው ጊዜ ምን ሊሰማው እንደሚችል አስብ! *

11. ከዳዊትና ከዮናታን ምሳሌ ስለ ወዳጅነት ምን ትምህርት ታገኛለህ?

11 ከዮናታንና ከዳዊት ምሳሌ ምን እንማራለን? የምናገኘው ትልቁ ትምህርት ጓደኛሞች በጋራ ሊኖራቸው የሚገባው በጣም አስፈላጊ ነገር መንፈሳዊነት መሆኑን ነው። የእኛ ዓይነት እምነትና የሥነ ምግባር አቋም ካላቸው እንዲሁም ለአምላክ ታማኝ ሆነው ለመኖር ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር ስንቀራረብ ሐሳባችንን፣ ስሜታችንንና ተሞክሮዎቻችንን በመለዋወጥ እርስ በርሳችን መበረታታትም ሆነ መጽናናት እንችላለን። (ሮም 1:11, 12) እንዲህ ያሉ መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ወዳጆች  ማግኘት የምንችለው ከእምነት ባልንጀሮቻችን መካከል ነው። ይሁንና እንዲህ ሲባል የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሁሉ ጥሩ ወዳጅ ይሆናሉ ማለት ነው? ላይሆን ይችላል።

የቅርብ ጓደኞቻችንን መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው?

12, 13. (ሀ) ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን መካከል እንኳ የቅርብ ጓደኞችን ስንመርጥ ጠንቃቆች ልንሆን የሚገባን ለምንድን ነው? (ለ) በአንደኛው መቶ ዘመን የነበሩ ጉባኤዎች እንዴት ያለ ፈተና ገጥሟቸው ነበር? ይህስ ጳውሎስ ምን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ ገፋፍቶታል?

12 ጓደኞቻችን በመንፈሳዊ የሚያንጹን እንዲሆኑ ከፈለግን በጉባኤ ውስጥም እንኳ መራጭ መሆን አለብን። ይህ ሊያስደንቀን ይገባል? አይገባም። በአንድ ዛፍ ላይ ያሉ ፍሬዎች በሙሉ እኩል እንደማይበስሉ ሁሉ በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም መንፈሳዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ ብዙ ጊዜ ሊፈጅባቸው ይችላል። በመሆኑም በሁሉም ጉባኤ ውስጥ በተለያየ የመንፈሳዊ እድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖችን እናገኛለን። (ዕብራውያን 5:12 እስከ 6:3) እርግጥ በመንፈሳዊ እንዲያድጉ ልንረዳቸው ስለምንፈልግ ለአዲሶችና ደካማ ለሆኑ ትዕግሥትና ፍቅር እናሳያቸዋለን።ሮም 14:1፤ 15:1

13 አንዳንድ ጊዜ በጓደኛ ምርጫ ረገድ ጥንቃቄ ለማድረግ የምንገደድበት ሁኔታ በጉባኤ ውስጥ ሊፈጠር ይችላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች አጠያያቂ የሆነ አካሄድ ሊጀምሩ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ የማማረርና የማጉረምረም መንፈስ ይታይባቸው ይሆናል። በአንደኛው መቶ ዘመን የነበሩ ጉባኤዎች ተመሳሳይ ፈተና አጋጥሟቸው ነበር። አብዛኞቹ የጉባኤው አባላት ታማኞች የነበሩ ቢሆንም በትክክለኛው አካሄድ የማይመላለሱ አንዳንድ ግለሰቦች ነበሩ። የቆሮንቶስ ጉባኤ አባላት የነበሩ ጥቂት ሰዎች አንዳንዶቹን የክርስትና ትምህርቶች የማይጠብቁ ስለነበሩ ሐዋርያው ጳውሎስ ጉባኤውን “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” ሲል አስጠንቅቋል። (1 ቆሮንቶስ 15:12, 33) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በክርስቲያኖች መካከልም እንኳ በሥርዓት የማይመላለሱ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቆታል። ጢሞቴዎስ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች  እንዲርቅና ከእነሱ ጋር የቅርብ ጓደኝነት እንዳይመሠርት ተነግሮታል።2 ጢሞቴዎስ 2:20-22

14. ጳውሎስ ስለ ጓደኝነት የሰጠው ማስጠንቀቂያ የተመሠረተበትን መሠረታዊ ሥርዓት ሥራ ላይ ልናውል የምንችለው እንዴት ነው?

14 ጳውሎስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ የተመሠረተበትን መሠረታዊ ሥርዓት ሥራ ላይ ልናውል የምንችለው እንዴት ነው? በጉባኤ ውስጥም ይሁን ከጉባኤ ውጭ፣ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ከሚችል ከማንኛውም ሰው ጋር የቅርብ ጓደኛ ባለመሆን ነው። (2 ተሰሎንቄ 3:6, 7, 14) መንፈሳዊነታችንን ከአደጋ መጠበቅ ይገባናል። የቅርብ ጓደኞቻችንን ዝንባሌና አካሄድ ልክ እንደ ስፖንጅ እንደምንመጥ አስታውስ። አንድን ስፖንጅ ኮምጣጤ ውስጥ ነክረን ውኃ ይዞ ይወጣል ብለን እንደማንጠብቅ ሁሉ መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩብን ሰዎች ጋር ገጥመን ጠቃሚ ነገር እንወርሳለን ብለን ልንጠብቅ አንችልም።1 ቆሮንቶስ 5:6

ከእምነት ባልንጀሮቻችን መካከል ጥሩ ጥሩ ጓደኞች ማግኘት ትችላለህ

15. በጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ጓደኞች ለማግኘት ምን ልታደርግ ትችላለህ?

15 በጣም ደስ የሚለው ግን ከእምነት ባልንጀሮቻችን መካከል ጥሩ ጓደኞችን የማግኘት አጋጣሚያችን በጣም ሰፊ ነው። (መዝሙር 133:1) ከጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያላቸው ጓደኞች ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? አምላካዊ ባሕርያትን ስታዳብር ተመሳሳይ ጥረት በማድረግ ላይ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች ወደ አንተ መሳባቸው አይቀርም። በተጨማሪም አዳዲስ ጓደኞችን ለማፍራት አንተ ራስህ ልትወስዳቸው የሚገቡ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ እርምጃዎች አሉ። (“ ጥሩ ጓደኞች አገኘን፤ እንዴት?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) አንተ እንዲኖሩህ የምትፈልጋቸው ባሕርያት ያሏቸውን ሰዎች ፈልግ። ዘራቸው፣ ብሔራቸው ወይም ባሕላቸው ከአንተ የተለየ ቢሆንም ከእምነት ባልንጀሮችህ መካከል ጓደኛ ለማግኘት በመጣር መጽሐፍ ቅዱስ “ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ” ሲል የሰጠውን ምክር ሥራ ላይ አውል። (2 ቆሮንቶስ 6:13፤ 1 ጴጥሮስ 2:17) ጓደኝነትህ ከዕድሜ እኩዮችህ ጋር ብቻ አይሁን። ዮናታን ከዳዊት በዕድሜ ብዙ ይበልጥ እንደነበር አስታውስ። በዕድሜ ጠና ያሉ ሰዎች ያላቸው ተሞክሮና ጥበብ ጓደኝነታችሁን በጣም አስደሳች እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል።

 ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ

16, 17. አንድ ክርስቲያን በሆነ መንገድ ቢጎዳን ከጉባኤ መራቅ የማይኖርብን ለምንድን ነው?

16 በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሰዎች በጣም የተለያየ አስተዳደግና ጠባይ ስላላቸው አልፎ አልፎ ችግሮች ሊነሱ ይችላሉ። አንድ የእምነት ባልንጀራችን ስሜታችንን የሚጎዳ ነገር ይናገር ወይም ያደርግ ይሆናል። (ምሳሌ 12:18) አንዳንድ ጊዜ ለግጭቶች መንስኤ የሚሆነው የባሕርይ አለመጣጣም፣ አለመግባባት ወይም የአመለካከት ልዩነት ሊሆን ይችላል። ታዲያ በዚህ ተሰናክለን ከጉባኤ እንርቃለን? ለይሖዋና ይሖዋ ለሚወዳቸው ሰዎች እውነተኛ ፍቅር ካለን ከጉባኤ አንርቅም።

17 ይሖዋ ሕይወትንና ለሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮችን የሰጠን በመሆኑ ልንወደውና በሙሉ ልባችን ልንገዛለት የሚገባን አምላካችን ነው። (ራእይ 4:11) በተጨማሪም ይሖዋ የሚጠቀመው በጉባኤ በኩል ስለሆነ ይህን ጉባኤ በታማኝነት መደገፍ ይኖርብናል። (ዕብራውያን 13:17) ታዲያ አንድ ክርስቲያን በሆነ መንገድ ቢጎዳን ወይም ቢያሳዝነን  መቀየማችንን ለመግለጽ ብለን ከጉባኤ መራቅ ይኖርብናል? በፍጹም እንደዚያ ማድረግ አይኖርብንም። ያስቀየመን ይሖዋ አይደለም። ለይሖዋ ያለን ፍቅር፣ ጀርባችንን ለእሱም ሆነ ለሕዝቦቹ እንድንሰጥ አይፈቅድልንም!መዝሙር 119:165

18. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ምን ልናደርግ እንችላለን? (ለ) ይቅር ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ይቅርታ ማድረጋችን ምን በረከት ያስገኝልናል?

18 ለእምነት ባልንጀሮቻችን ያለን ፍቅር በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናደርግ ይገፋፋናል። ይሖዋ ከሚወዳቸው ሰዎች ፍጽምና ስለማይጠብቅ እኛም ልንጠብቅ አይገባም። ፍቅር፣ ሁላችንም ፍጹማን እንዳልሆንና እንደምንሳሳት በማስታወስ ጥቃቅን ጉድለቶችን ችላ ብለን እንድናልፍ ያስችለናል። (ምሳሌ 17:9፤ 1 ጴጥሮስ 4:8) ፍቅር ‘እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችንን’ እንድንቀጥል ይረዳናል። (ቆላስይስ 3:13) ይህን ምክር ሥራ ላይ ማዋል ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። በውስጣችን ያለው ቅሬታ እንዲቆጣጠረን ከፈቀድን ምናልባት በማኩረፍ የበደለንን ሰው መቅጣት እንደምንችል ተሰምቶን ቂም ወደመያዝ ልናዘነብል እንችላለን። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ቂም ይዞ መቆየት የሚጎዳው ራሳችንን ነው። ይቅር ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ይቅርታ ማድረጋችን ብዙ በረከት ያስገኝልናል። (ሉቃስ 17:3, 4) የልብና የአእምሮ ሰላም ይሰጠናል፤ እንዲሁም በጉባኤው ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ይጠብቅልናል።ማቴዎስ 6:14, 15፤ ሮም 14:19

ጓደኝነታችንን ማቋረጥ የሚገባን መቼ ነው?

19. ከአንድ ሰው ጋር የነበረንን ቅርርብ እንድናቋርጥ የሚያስገድድ ምን ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል?

19 የጉባኤው አባል ከነበረ ሰው ጋር የነበረንን ቅርርብ ለማቋረጥ የምንገደድበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ የሚፈጠረው አንድ ሰው የአምላክን ሕግ ከጣሰ በኋላ ንስሐ ለመግባት እምቢተኛ ሆኖ ሲወገድ ወይም የሐሰት ትምህርቶች በማስተማር እምነትን ሲክድ አሊያም ደግሞ ራሱን ከጉባኤ ሲያገል ነው። የአምላክ ቃል እንዲህ ካለው ሰው  ጋር ‘መግጠማችሁን ተዉ’ በማለት በግልጽ ያዛል። * (1 ቆሮንቶስ 5:11-13፤ 2 ዮሐንስ 9-11) የቅርብ ጓደኛችን ከነበረ ወይም ዘመዳችን ከሆነ ሰው መራቅ አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። በዚህ ረገድ ጠንካራ አቋም በመያዝ ከምንም በላይ ለይሖዋና ለጽድቅ ሕጎቹ ታማኝ መሆናችንን እናሳያለን? ይሖዋ ታማኝነትንና ታዛዥነትን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት አትርሳ።

20, 21. (ሀ) የውገዳ እርምጃ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ጓደኞቻችንን በጥንቃቄ መምረጣችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

20 እንደ እውነቱ ከሆነ የውገዳ እርምጃ የይሖዋ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆነን ኃጢአተኛ ከጉባኤ ማስወገድ ለይሖዋ ቅዱስ ስምና ስሙ ለሚወክላቸው ነገሮች በሙሉ ፍቅር እንዳለን ያሳያል። (1 ጴጥሮስ 1:15, 16) የውገዳ ዝግጅት የጉባኤውን ደህንነት ያስጠብቃል። ታማኝ የጉባኤው አባላት ሆን ብለው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች ከሚያሳድሩት መጥፎ ተጽዕኖ ይጠበቃሉ፤ እንዲሁም ጉባኤው ከዚህ ክፉ ዓለም መሸሸጊያ እንደሆነ ተሰምቷቸው አምልኳቸውን ያላንዳች ስጋት ማካሄድ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 5:7፤ ዕብራውያን 12:15, 16) እንዲህ ያለ ጠንካራ ተግሣጽ መሰጠቱ በደለኛው የሚወደድ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ግለሰቡ ወደ ልቡ እንዲመለስና የይሖዋን ሞገስ መልሶ ለማግኘት የሚያስችለውን እርምጃ እንዲወስድ የሚያነሳሳው እንዲህ ያለው ከባድ ተግሣጽ ሊሆን ይችላል።ዕብራውያን 12:11

21 የቅርብ ጓደኞቻችን ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብንና ሊቀርጹን እንደሚችሉ መካድ አንችልም። ስለዚህ ጓደኞቻችንን በጥንቃቄ መምረጣችን በጣም አስፈላጊ ነው። የይሖዋን ወዳጆች ወዳጆቻችን ካደረግን እንዲሁም አምላክ የሚወዳቸውን ከወደድን በጣም ግሩም ባሕርያት ባሏቸው ባልንጀሮች እንከበባለን። ከእነሱ የምንኮርጀው ነገር ይሖዋን ለማስደሰት ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ እንድንጸና ይረዳናል።

^ አን.4 ይሖዋ አብርሃም ይህን እንዲያደርግ በመጠየቅ እሱ ራሱ አንድያ ልጁን በመስጠት ወደፊት የሚከፍለውን መሥዋዕትነት በምሳሌያዊ ሁኔታ አሳይቷል። (ዮሐንስ 3:16) ለአብርሃም ግን ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ በይስሐቅ ምትክ መሥዋዕት የሚሆን አውራ በግ አዘጋጅቷል።ዘፍጥረት 22:1, 2, 9-13

^ አን.9 ዳዊት ጎልያድን በገደለው ጊዜ “አንድ ፍሬ ልጅ” ሲሆን ዮናታን በሞተበት ጊዜ ወደ 30 ዓመት ይጠጋው ነበር። (1 ሳሙኤል 17:33፤ 31:2፤ 2 ሳሙኤል 5:4) ዮናታን የሞተው በ60 ዓመቱ ስለነበረ ዳዊትን በ30 ዓመት ያህል ይበልጠው እንደነበር ግልጽ ነው።

^ አን.101 ሳሙኤል 23:17 ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ዮናታን ዳዊትን ለማበረታታት አምስት ነገሮች ተናግሯል:- (1) ዳዊት እንዳይፈራ መከረው። (2) ሳኦል የሚያደርገው ጥረት እንደማይሳካ አረጋገጠለት። (3) አምላክ ቃል እንደገባለት ንግሥናውን ማግኘቱ እንደማይቀር ነገረው። (4) ለዳዊት ታማኝ ሆኖ እንደሚቀጥል ቃል ገባለት። (5) ሳኦልም ዮናታን ለዳዊት ታማኝ መሆኑን እንደሚያውቅ ነገረው።

^ አን.19 ከተወገዱ ወይም ራሳቸውን ካገለሉ ሰዎች ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “ከአንድ የተወገደ ግለሰብ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረን ይገባል?” የሚለውን ተጨማሪ መረጃ ተመልከት።