በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’

 ምዕራፍ 1

“አምላክን መውደድ” ሲባል ምን ማለት ነው?

“አምላክን መውደድ” ሲባል ምን ማለት ነው?

“አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም።”1 ዮሐንስ 5:3

1, 2. ይሖዋ አምላክን እንድትወደው የሚገፋፋህ ምንድን ነው?

አምላክን ትወደዋለህ? ራስህን ለይሖዋ አምላክ የወሰንክ ክርስቲያን ከሆንክ ያላንዳች ማመንታት ‘አዎን’ ብለህ እንደምትመልስ ግልጽ ነው፤ ደግሞም እንደዚያ መሆን ይኖርበታል። ይሖዋን መውደዳችን ትክክለኛ ነገር ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አምላክን የወደድነው እሱ አስቀድሞ ስለወደደን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “[ይሖዋ] አስቀድሞ ስለወደደን እኛም በበኩላችን ፍቅር እናሳያለን” በማለት ይናገራል።—1 ዮሐንስ 4:19

2 ይሖዋ ለእኛ ፍቅሩን ለመግለጽ ቀዳሚ ሆኗል። ውብ የሆነችውን ምድር መኖሪያችን አድርጎ ሰጥቶናል። ለአካላዊም ሆነ ለቁሳዊ ፍላጎቶቻችን ያስባል። (ማቴዎስ 5:43-48) ከዚህም ይበልጥ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ያሟላልናል። ቃሉ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። በተጨማሪም ጸሎታችንን እንደሚሰማና ረዳት የሆነውን ቅዱስ መንፈሱን እንደሚሰጠን ቃል በመግባት ወደ እሱ እንድንጸልይ ጋብዞናል። (መዝሙር 65:2፤ ሉቃስ 11:13) ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ከኃጢአትና ከሞት እንድንድን ከምንም በላይ የሚወደውን ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል። ይሖዋ ያሳየን ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው!ዮሐንስ 3:16፤ ሮም 5:8

3. (ሀ) ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ከእኛ ምን ይፈለጋል? (ለ) ልናስብበት የሚገባን አስፈላጊ ጥያቄ የትኛው ነው? መልሱስ የት ይገኛል?

3 ይሖዋ ለዘላለም የእሱን ፍቅር እያገኘን እንድንኖር ይፈልጋል።  ይሁንና የእሱን ፍቅር ለዘላለም ማግኘት አለማግኘታችን የተመካው በእኛ ላይ ነው። የአምላክ ቃል ‘የዘላለም ሕይወትን [ተስፋ እያደረጋችሁ] ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ’ በማለት ያሳስበናል። (ይሁዳ 21) ‘ሳትወጡ ኑሩ’ የሚለው አነጋገር ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ከእኛ የሚፈለግ ነገር እንዳለ ያመለክታል። ተጨባጭ በሆኑ መንገዶች ለፍቅሩ ምላሽ መስጠት ያስፈልገናል። እንግዲያው ልናስብበት የሚገባን አንድ አስፈላጊ ጥያቄ አለ፤ እሱም ‘አምላክን እንደምወድ በተግባር ማሳየት የምችለው እንዴት ነው?’ የሚለው ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው ቃል ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። ዮሐንስ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም” ብሏል። (1 ዮሐንስ  5:3) አምላካችንን ምን ያህል እንደምንወደው ማሳየት ስለምንፈልግ የእነዚህን ቃላት ትርጉም በጥንቃቄ መመርመራችን ተገቢ ነው።

“አምላክን መውደድ” ምን ማለት ነው?

4, 5. ይሖዋን መውደድ የጀመርከው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

4 ሐዋርያው ዮሐንስ “አምላክን መውደድ” በማለት ሲጽፍ በአእምሮው ይዞት የነበረው ነገር ምንድን ነው? እያንዳንዳችን ለአምላክ ያለንን ጥልቅ የፍቅር ስሜት እየገለጸ ነበር። በልብህ ውስጥ ለይሖዋ ፍቅር ማዳበር የጀመርክበት ጊዜ ትዝ ይልሃል?

ራስን መወሰንና መጠመቅ፣ በፍቅር ተነሳስተን ይሖዋን እየታዘዝን ለመኖር የምንወስደው የመጀመሪያው እርምጃ ነው

5 ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ እውነቱን የተማርክበትንና እምነት ማሳደር የጀመርክበትን ጊዜ እስቲ ለአንድ አፍታ አስብ። ኃጢአተኛና ከአምላክ የራቅህ ሆነህ ብትወለድም ይሖዋ አዳም ያጣውን ፍጽምናና የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ በክርስቶስ በኩል መንገድ እንደከፈተልህ ተረዳህ። (ማቴዎስ 20:28፤ ሮም 5:12, 18) ይሖዋ ከምንም በላይ የሚወደውን ልጁን ወደ ምድር ልኮ ለአንተ እንዲሞት በማድረግ የከፈለው መሥዋዕትነት ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ተገነዘብክ። በዚህም ልብህ በጣም ስለተነካ እንዲህ ያለ ታላቅ ፍቅር ያሳየህን አምላክ መውደድ ጀመርክ።1 ዮሐንስ 4:9, 10

6. እውነተኛ ፍቅር የሚገለጸው እንዴት ነው? ለአምላክ ያለህ ፍቅር ምን እንድታደርግ ገፋፍቶሃል?

6 ይሁን እንጂ ይህ ስሜት ይሖዋን መውደድ እንደጀመርክ የሚያሳይ ብቻ ነው። ፍቅር እንዲያው ስሜት ብቻ አይደለም፤ ወይም ደግሞ በቃላት ብቻ የሚገለጽ ነገርም አይደለም። እውነተኛ ፍቅር “ይሖዋን እወደዋለሁ” ብሎ ከመናገር ያለፈ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። እንደ እምነት ሁሉ እውነተኛ ፍቅርም በተግባር የሚገለጽ ነው። (ያዕቆብ 2:26) ፍቅር፣ የምንወደው ሰው የሚደሰትባቸውን ነገሮች በማድረግ ይገለጻል። ስለሆነም ለይሖዋ ያለህ ፍቅር በልብህ ውስጥ ሥር እየሰደደ ሲሄድ የሰማዩን አባትህን በሚያስደስት መንገድ ለመኖር ፍላጎት አደረብህ። የተጠመቅክ የይሖዋ ምሥክር ነህ? ከሆንክ በሕይወትህ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ይህን ውሳኔ እንድታደርግ የገፋፋህ ለይሖዋ  ያለህ ጥልቅ ፍቅርና ታማኝነት ነው። ፈቃዱን ለማድረግ ራስህን ለይሖዋ የወሰንክ ሲሆን ይህን ውሳኔህን ይፋ ለማድረግ ደግሞ ተጠምቀሃል። (ሮም 14:7, 8) ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን የገባነውን ቃል መፈጸም ሐዋርያው ዮሐንስ ቀጥሎ የተናገረውን ማድረግን ይጨምራል።

“ትእዛዛቱን መጠበቅ”

7. ከአምላክ ትእዛዛት መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? እነዚህን ትእዛዛት መጠበቅ ምን ማድረግን ይጠይቃል?

7 ዮሐንስ አምላክን መውደድ ሲባል “ትእዛዛቱን መጠበቅ” ማለት እንደሆነ ተናግሯል። የአምላክ ትእዛዛት ምንድን ናቸው? ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት በግልጽ የተቀመጡ በርካታ ትእዛዛት ሰጥቶናል። ለምሳሌ ያህል፣ እንደ ስካር፣ ዝሙት፣ ጣዖት አምልኮ፣ ስርቆትና ውሸት ያሉ ድርጊቶችን ይከለክላል። (1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 6:18፤ 10:14፤ ኤፌሶን 4:28፤ ቆላስይስ 3:9) የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ከተቀመጡት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖርን ይጠይቃል።

8, 9. ቀጥተኛ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ያልተሰጠባቸው ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ይሖዋን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

8 ይሁን እንጂ ይሖዋን ለማስደሰት ከፈለግን በግልጽ የተቀመጡትን ትእዛዛት ከመጠበቅ አልፈን መሄድ ይኖርብናል። ይሖዋ እያንዳንዱን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንን የሚገድቡ ዝርዝር ሕግጋት በመስጠት መፈናፈኛ አያሳጣንም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግልጽ ትእዛዝ ያልተሰጠባቸው በርካታ ሁኔታዎች በየቀኑ ያጋጥሙናል። እንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አስተሳሰብ ምን እንደሆነ በግልጽ የሚጠቁሙ ሐሳቦችን ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ ይሖዋ ምን እንደሚጠላና ምን እንደሚወድ እንማራለን። (መዝሙር 97:10፤ ምሳሌ 6:16-19) ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ዝንባሌዎችና ድርጊቶች የትኞቹ እንደሆኑ እናስተውላለን። ስለ  ይሖዋ ባሕርያትና ነገሮችን ስለሚያከናውንበት መንገድ ይበልጥ ባወቅን መጠን ደግሞ ውሳኔዎቻችንና ድርጊቶቻችን ከእሱ አስተሳሰብ ጋር የሚስማሙ እየሆኑ ይሄዳሉ። አድርግ ወይም አታድርግ የሚል ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ በማይኖርበት ጊዜም እንኳ በአብዛኛው “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ” ማስተዋል እንችላለን።ኤፌሶን 5:17

9 ለምሳሌ ያህል፣ አሰቃቂ ዓመጽና የጾታ ብልግና የሚታይባቸውን ፊልሞች ወይም የቴሌቪዥን ፕራግራሞች እንዳናይ የሚከለክል ቀጥተኛ ሕግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እንዳናይ የሚከለክል ግልጽ ሕግ የግድ ያስፈልገናል? ይሖዋ እንደነዚህ ስላሉት ጉዳዮች ምን አመለካከት እንዳለው እናውቃለን። ቃሉ “ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች” በማለት በግልጽ ይናገራል። (መዝሙር 11:5) በተጨማሪም “አምላክ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ይፈርድባቸዋል” ይላል። (ዕብራውያን 13:4) በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት በእነዚህ ቃላት ላይ ካሰላሰልን የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማስተዋል እንደማይቸግረን ግልጽ ነው። ስለዚህ አምላካችን የሚጠላቸውን ድርጊቶች በግልጽ የሚያሳዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ላለማየት እንወስናለን። ይህ ዓለም ምንም ጉዳት እንደሌላቸው አድርጎ ከሚያቀርባቸው ወራዳ መዝናኛዎች ስንርቅ ይሖዋ እንደሚደሰት እናውቃለን። *

10, 11. ይሖዋን ለመታዘዝ የምንመርጠው ለምንድን ነው? የምናሳየውስ ምን ዓይነት ታዛዥነት ነው?

10 የአምላክን ትእዛዛት የምንጠብቅበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው? በእያንዳንዷ ቀን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ተስማምተን ለመኖር የምንፈልገው ለምንድን ነው? እንዲህ የምናደርገው ከቅጣት ለማምለጥ ወይም የአምላክን ፈቃድ ችላ የሚሉ ሰዎች ከሚደርስባቸው ጉዳት ለመዳን ብቻ ብለን አይደለም። (ገላትያ 6:7) ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ ታዛዥ መሆናችን ለእሱ ያለንን ፍቅር ለማሳየት የሚያስችል ግሩም  አጋጣሚ እንደሚከፍትልን ስለሚሰማን ነው። አንድ ልጅ አባቱ “ጎሽ፣ የኔ ልጅ” እንዲለው እንደሚጓጓ ሁሉ እኛም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት እንፈልጋለን። (መዝሙር 5:12) እሱ አባታችን ስለሆነ እንወደዋለን። ‘የይሖዋን ሞገስ በሚያስገኝ’ መንገድ እየኖርን እንዳለ ከማወቅ የበለጠ ደስታና ጥልቅ እርካታ የሚሰጥ ነገር የለም።ምሳሌ 12:2

11 የምንታዘዘው ቅር እያለን ወይም እየመረጥን አሊያም ደግሞ ሁኔታውን እያየን አይደለም። * ከተሰጡን ትእዛዛት መካከል ደስ ያለንን፣ የሚመቸንንና ብዙም ችግር የማያስከትልብንን ብቻ እየመረጥን አንታዘዝም። ከዚህ ይልቅ ትእዛዙ ምንም ይሁን ምን ‘ከልብ እንታዘዛለን።’ (ሮም 6:17) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰ አንድ መዝሙራዊ የተሰማው ዓይነት ስሜት አለን፤ መዝሙራዊው “እኔ እወደዋለሁና፣ በትእዛዝህ ደስ ይለኛል” ብሎ ነበር። (መዝሙር 119:47) አዎ፣ ይሖዋን መታዘዝ ያስደስተናል። ይሖዋ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ልንታዘዘው የሚገባ አምላክ እንደሆነና ይህንንም እንደሚጠብቅብን እንገነዘባለን። (ዘዳግም 12:32) ይሖዋ ስለ ኖኅ የተናገረውን ለእኛም እንዲናገርልን እንፈልጋለን። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለብዙ ዘመናት ታዛዥ በመሆን ለአምላክ ያለውን ፍቅር በተግባር ስላሳየው ታማኝ የእምነት አባት ሲናገር ‘ኖኅም ሁሉን አምላክ እንዳዘዘው አደረገ’ ይላል።ዘፍጥረት 6:22

12. የይሖዋን ልብ ደስ የምናሰኘው እንዴት ብንታዘዘው ነው?

12 ይሖዋ በፈቃደኝነት ስንታዘዘው ምን ይሰማዋል? ቃሉ ይህን ማድረጋችን ‘ልቡን ደስ እንደሚያሰኘው’ ይናገራል። (ምሳሌ 27:11) ታዛዥነታችን የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ በእርግጥ ያስደስተዋል? አዎን፣ ያስደስተዋል! ደግሞም ለመደሰት በቂ ምክንያት አለው። ይሖዋ የፈጠረን የመምረጥ ነፃነት እንዲኖረን አድርጎ በመሆኑ የፈለግነውን ለማድረግ የመምረጥ ነፃነት አለን። አምላክን ለመታዘዝም ሆነ  ላለመታዘዝ መምረጥ እንችላለን። (ዘዳግም 30:15, 16, 19, 20) በሰማይ የሚኖረው አባታችን ወደን እሱን ለመታዘዝ መምረጣችን ያስደስተዋል። እንዲህ ያለውን ምርጫ ያደረግነው ለእሱ ባለን ፍቅር ተገፋፍተን መሆኑን ሲመለከት ደግሞ ይበልጥ ይደሰታል። (ምሳሌ 11:20) በተጨማሪም ይህን ማድረጋችን ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት መንገድ መምረጣችንን የሚያሳይ ነው።

‘ትእዛዛቱ ከባዶች አይደሉም’

13, 14. አምላክ የሚሰጠን ‘ትእዛዛት ከባዶች አይደሉም’ ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? ይህንንስ እንዴት በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል?

13 ሐዋርያው ዮሐንስ ይሖዋ ስለሚጠብቅብን ነገር ሲናገር “ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም” ብሏል፤ ይህ በእርግጥም እጅግ የሚያጽናና ነው። አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ትእዛዛቱ ደግሞ የሚያስጨንቁ አይደሉም” ይላል። (ኒው ኢንግሊሽ ትራንስሌሽን) ይሖዋ እንድናደርግ የሚፈልግብን ነገሮች ምክንያታዊነት የጎደላቸው ወይም የሚጨቁኑ አይደሉም። ሰዎች ፍጽምና የጎደላቸው ቢሆኑም እንኳ ሕጎቹን መጠበቅ ከአቅማቸው በላይ አይደለም።

14 አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ የቅርብ ጓደኛህ ቤት ሊለቅ ስለሆነ ዕቃዎቹን በማጓጓዝ እንድትረዳው ጠየቀህ እንበል። ጓደኛህ ብዙ የሚጓጓዙ ዕቃዎች አሉት። አንዳንዶቹ ቀላል በመሆናቸው አንድ ሰው ብቻውን ሊሸከማቸው ይችላል። ሌሎቹ ግን ከባድ ስለሆኑ ሁለት ሰዎች ተጋግዘው ሊሸከሟቸው የሚገቡ ናቸው። ጓደኛህ አንተ እንድትሸከምለት የሚፈልጋቸውን ዕቃዎች ይመርጣል። ከአቅምህ በላይ መሆኑን እያወቀ ከባድ የሆኑትን ዕቃዎች እንድትሸከም የሚጠይቅህ ይመስልሃል? በፍጹም እንዲህ አያደርግም! ብቻህን ለመሸከም ስትጣጣር ጉዳት እንዲደርስብህ አይፈልግም። በተመሳሳይም አፍቃሪውና ደጉ አምላካችን ለመፈጸም አስቸጋሪ የሆኑ ትእዛዛት አይሰጠንም። (ዘዳግም 30:11-14) እንዲህ ያለውን ከባድ ሸክም እንድንሸከም ፈጽሞ አይጠይቀንም። ይሖዋ ‘አፈጣጠራችንን ስለሚያውቅና ትቢያ መሆናችንን ስለሚያስብ’ አቅማችንን ይረዳል።መዝሙር 103:14

15. የይሖዋ ትእዛዛት ለእኛው ጥቅም እንደተሰጡ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

 15 የይሖዋ ትእዛዛት የተሰጡን ሸክም እንዲሆኑብን ሳይሆን ለእኛው ጥቅም ሲባል ነው። (ኢሳይያስ 48:17) በመሆኑም ሙሴ ለጥንት እስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸዋል:- “ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ምን ጊዜም መልካም እንዲሆንልንና በሕይወት እንድንኖር ይህን ሥርዐት ሁሉ እንድንፈጽም፣ አምላካችንንም እግዚአብሔርን እንድንፈራ እግዚአብሔር አዘዘን።” (ዘዳግም 6:24) እኛም ይሖዋ ሕጎቹን የሰጠን ለእኛ አስቦ ይኸውም ዘላለማዊ ጥቅም እንዲያስገኝልን ሲል እንደሆነ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ይሖዋ ከዚህ የተለየ ፍላጎት ይኖረዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ይሖዋ ጥልቅ ጥበብ ያለው አምላክ ነው። (ሮም 11:33) በመሆኑም የሚበጀንን ያውቃል። በተጨማሪም ይሖዋ የፍቅር ተምሳሌት ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) ማንኛውንም ነገር የሚያደርገውና የሚናገረው ዋነኛ ባሕርይው በሆነው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። ለአገልጋዮቹ የሚሰጣቸው ትእዛዛት በሙሉ መሠረታቸው ፍቅር ነው።

16. ይህ መጥፎ ዓለምና ኃጢአተኛ የሆነው ሥጋችን ተጽዕኖ ቢያደርጉብንም ታዛዥ መሆን እንችላለን የምንለው ለምንድን ነው?

16 ይህ ሲባል ግን አምላክን መታዘዝ ቀላል ነው ማለት አይደለም። “በክፉው ኃይል ሥር” ያለው ይህ መጥፎ ዓለም የሚያመጣብንን ተጽዕኖዎች መቋቋም ይኖርብናል። (1 ዮሐንስ 5:19) በተጨማሪም የአምላክን ሕጎች እንድንተላለፍ ከሚገፋፋን ኃጢአተኛ ሥጋችን ጋር መታገል አለብን። (ሮም 7:21-25) ይሁን እንጂ ለአምላክ ያለን ፍቅር ማሸነፉ አይቀርም። ይሖዋ ታዛዥ በመሆን ለእሱ ያላቸውን ፍቅር በተግባር የሚያስመሠክሩ ሰዎችን ይባርካል። “እንደ ገዥያቸው አድርገው እየታዘዙት ላሉት” ቅዱስ መንፈሱን ይሰጣል። (የሐዋርያት ሥራ 5:32) ይህ መንፈስ ደግሞ ጥሩ ፍሬ እንድናፈራ ማለትም ታዛዥ ለመሆን በምናደርገው ጥረት የሚያግዙንን ግሩም ባሕርያት እንድናዳብር ይረዳናል።ገላትያ 5:22, 23

17, 18. (ሀ) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ምን እንመረምራለን? ይህንን ስናደርግ በአእምሯችን ልንይዛቸው የሚገቡ ነጥቦች ምንድን ናቸው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ውስጥ የሚብራራው ምንድን ነው?

 17 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የይሖዋን መሠረታዊ ሥርዓቶችና የሥነ ምግባር ደንቦች፣ እንዲሁም የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ የሚጠቁሙንን ሌሎች በርካታ ሐሳቦች እንመረምራለን። ይህን በምናደርግበት ጊዜ አንዳንድ ጠቃሚ ነጥቦችን በአእምሯችን መያዝ ያስፈልገናል። ይሖዋ ሕጎቹንና ሥርዓቶቹን እንድንታዘዝ እንደማያስገድደን ከዚህ ይልቅ ከልብ በመነጨ ፍቅር ተነሳስተን በፈቃደኝነት እንድንታዘዘው እንደሚፈልግ እናስታውስ። እንዲሁም ይሖዋ የሚፈልግብን በአሁኑ ጊዜ የተትረፈረፈ በረከት በሚያሳጭደን፣ ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት በሚያስገኝልን የሕይወት ጎዳና ላይ እንድንጓዝ መሆኑን አንዘንጋ። በተጨማሪም በሙሉ ልብ ታዛዥ መሆን ይሖዋን ምን ያህል እንደምንወደው የምናሳይበት ግሩም አጋጣሚ መሆኑን እናስታውስ።

18 ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ትክክል የሆነውን ነገር ስህተት ከሆነው ለመለየት የሚረዳንን ሕሊና ሰጥቶናል። ይሁን እንጂ ሕሊናችን አስተማማኝ መሪ እንዲሆንልን መሠልጠን ይኖርበታል። የሚቀጥለው ምዕራፍ ስለዚህ ጉዳይ ያብራራል።

^ አን.9 ጤናማ የሆኑ መዝናኛዎችን መምረጥ ስለሚቻልበት መንገድ ማብራሪያ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ምዕራፍ 6 ተመልከት።

^ አን.11 ክፉ መናፍስት ባይፈልጉም እንኳ ይታዘዛሉ። ኢየሱስ ከሰዎች እንዲወጡ አጋንንትን ባዘዘ ጊዜ ወደው ባይሆንም ሥልጣኑን ለመቀበልና ለመታዘዝ ተገደዋል።ማርቆስ 1:27፤ 5:7-13