በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’

 ምዕራፍ 14

በሁሉም ነገር ሐቀኛ ሁን

በሁሉም ነገር ሐቀኛ ሁን

‘በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንመኛለን።’ዕብራውያን 13:18

1, 2. ይሖዋ ሐቀኛ ለመሆን የምናደርገውን ጥረት ሲመለከት የሚደሰተው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

አንዲት እናትና ትንሽ ልጇ ከአንድ ሱቅ ይወጣሉ። ልጁ በድንገት ድንግጥ ብሎ ይቆማል። ከሱቁ ያነሳውን ትንሽ መጫወቻ በእጁ ይዟል። መጫወቻውን መልሶ ማስቀመጥ ወይም እናቱ እንድትገዛለት መጠየቅ እንደነበረበት ረስቷል። ከመጨነቁ የተነሳ ወደ እናቱ ይጮኻል። እናቱ ካረጋጋችው በኋላ መጫወቻውን እንዲመልስና ይቅርታ እንዲጠይቅ ወደ ሱቁ ይዛው ትመለሳለች። ልጁ ይህን በሚያደርግበት ጊዜ የእናትየው ልብ በደስታና በኩራት ስሜት ይሞላል። ለምን?

2 ወላጆች ልጆቻቸው ሐቀኝነት አስፈላጊ ባሕርይ መሆኑን እንደተገነዘቡ ሲመለከቱ በጣም ይደሰታሉ። “የእውነት አምላክ” የሆነው የሰማዩ አባታችንም ተመሳሳይ ስሜት አለው። (መዝሙር 31:5) ይሖዋ ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና ለማደግና ሐቀኞች ሆነን ለመመላለስ የምናደርገውን ጥረት ሲመለከት ይደሰታል። እሱን ለማስደሰትና ከፍቅሩ ሳንወጣ ለመኖር ስለምንፈልግ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንመኛለን’ ሲል በተናገረው ሐሳብ እንስማማለን። (ዕብራውያን 13:18) በመጀመሪያ ሐቀኛ መሆን ተፈታታኝ ሊሆን የሚችልባቸውን አራት መስኮች እናያለን። ከዚያም ሐቀኛ መሆን የሚያስገኝልንን በረከቶች እንመለከታለን።

ለራሳችን ሐቀኛ መሆን

3-5. (ሀ) የአምላክ ቃል ራስን ማታለል ስለሚያስከትለው አደጋ የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው? (ለ) ለራሳችን ሐቀኞች እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?

3 በመጀመሪያ ደረጃ ተፈታታኝ የሚሆንብን ነገር ለራሳችን ሐቀኛ መሆን ነው። ፍጽምና የጎደለን ሰዎች በመሆናችን በቀላሉ ራሳችንን ልናታልል  እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በሎዶቅያ የነበሩ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ጎስቋላ ማለትም ‘ድሃ፣ ዕውርና የተራቆቱ’ ሆነው ሳለ ሀብታም እንደሆኑ አድርገው በማሰብ ራሳቸውን እንዳታለሉ ኢየሱስ ነግሯቸዋል። (ራእይ 3:17) ራሳቸውን ማታለላቸው የነበሩበትን አደገኛ ሁኔታ አባባሰባቸው እንጂ የፈየደላቸው ነገር አልነበረም።

4 በተጨማሪም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንደሚከተለው ሲል አስጠንቅቆ እንደነበር ታስታውስ ይሆናል:- “አንድ ሰው አምልኮቱን እያከናወነ እንዳለ የሚሰማው ቢሆንም እንኳ አንደበቱን የማይገታ ከሆነ ይህ ሰው የገዛ ልቡን እያታለለ ይኖራል፤ የዚህ ሰው አምልኮም ከንቱ ነው።” (ያዕቆብ 1:26) በአንደበታችን የማይገባ ነገር እየተናገርን አምልኮታችን በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ይኖረዋል ብለን የምናስብ ከሆነ ልባችንን ከማታለል ውጭ የምናገኘው አንዳች ጥቅም አይኖርም። ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ከንቱ ወይም መና ይሆንብናል። ታዲያ እንዲህ ካለው አደገኛ አካሄድ ሊጠብቀን የሚችለው ምንድን ነው?

5 ያዕቆብ በዚያው መልእክቱ ላይ የአምላክን ቃል እውነት ከመስተዋት ጋር አመሳስሎታል። ፍጹም የሆነውን የአምላክ ሕግ በትኩረት እንድንመለከትና አስፈላጊውን ማስተካከያ እንድናደርግ መክሮናል። (ያዕቆብ 1:23-25) መጽሐፍ ቅዱስ ለራሳችን ሐቀኛ እንድንሆንና ለመሻሻል ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን እንድናስተውል ይረዳናል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:40፤ ሐጌ 1:5) በተጨማሪም ወደ ይሖዋ በመጸለይ ውስጣችንን እንዲመረምርልን ማለትም ከባድ ጉድለት ካለብን ጉድለታችንን እንድናውቅና ለማሻሻል እንድንችል እንዲረዳን ልንጠይቀው እንችላለን። (መዝሙር 139:23, 24) ሐቀኛ አለመሆን ከባድ ድክመት በመሆኑ ይህንን ጉዳይ የሰማዩ አባታችን በሚያይበት መንገድ ልንመለከተው ይገባል። ምሳሌ 3:32 “[ይሖዋ] ጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤ ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል” ይላል። ይሖዋ የእሱ ዓይነት ስሜት እንዲኖረንና ራሳችንን እሱ በሚያየን መንገድ እንድንመለከት ሊረዳን ይችላል። ጳውሎስ ‘በሐቀኝነት ለመኖር እንመኛለን’ እንዳለ አስታውስ። በአሁኑ ጊዜ ፍጹም መሆን ባንችልም ሐቀኞች ለመሆን እንፈልጋለን፣ በዚህ ረገድ እንዲሳካልንም ልባዊ ጥረት እናደርጋለን።

 በቤተሰብ ውስጥ ሐቀኛ መሆን

ሐቀኛ መሆን ከሌሎች ለመደበቅ የምንፈተንበትን ድርጊት እንዳንፈጽም ይረዳናል

6. የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው ሐቀኛ መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረጋቸውስ ከየትኞቹ አደጋዎች ይጠብቃቸዋል?

6 ሐቀኝነት የአንድ ክርስቲያን ቤተሰብ መለያ ባሕርይ መሆን አለበት። ስለዚህ ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ግልጽና ሐቀኛ መሆን አለባቸው። የትዳር ጓደኛ ያልሆነን ሰው ማሽኮርመም፣ በኢንተርኔት አማካኝነት ድብቅ ወዳጅነት መመሥረት ወይም ማንኛውንም ዓይነት የብልግና ምስል መመልከት እንዲሁም እነዚህን የመሰሉ ጎጂና ርኩስ ልማዶች በክርስቲያኖች ትዳር ውስጥ ቦታ የላቸውም። ባለትዳር የሆኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች የትዳር ጓደኞቻቸው ሳያውቁ እንዲህ ያሉ መጥፎ ድርጊቶችን ፈጽመዋል። እንዲህ ማድረግ ሐቀኝነትን ማጉደል ነው። ታማኝ የነበረው ንጉሥ ዳዊት የተናገራቸውን ቃላት ልብ በል:- “ከማይረቡ [“እውነትን ከማይናገሩ ሰዎች፣” NW] ጋር አልተቀመጥሁም፤ ከግብዞችም ጋር አልተባበርሁም።” (መዝሙር 26:4) ባለትዳር ከሆንክ ማንነትህን ከትዳር ጓደኛህ እንድትደብቅ የሚያደርግህን ነገር ከመፈጸም ራቅ!

7, 8. ልጆች ሐቀኝነት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ባሕርይ መሆኑን እንዲማሩ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ሊረዷቸው ይችላሉ?

7 ወላጆች ሐቀኝነት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ባሕርይ እንደሆነ ለልጆቻቸው በሚያስተምሩበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን ቢጠቀሙ ጥሩ ይሆናል። ሐቀኝነት በጎደለው መንገድ የተመላለሱ ሰዎችን በተመለከተ በርካታ ታሪኮችን ማግኘት ይቻላል። ለምሳሌ፣ ከሰረቀ በኋላ ስርቆቱን ለመደበቅ ስለሞከረው ስለ አካን፣ ገንዘብ ለማግኘት ሲል ውሸት ስለተናገረው ስለ ግያዝ፣ እንዲሁም በአደራ የተሰጠውን ንብረት ይሰርቅ ስለነበረውና ኢየሱስን አሳልፎ ስለመስጠት እያሰበ የአስመሳይነት ተግባር  ስለፈጸመው ስለ ይሁዳ የሚናገሩትን ታሪኮች መጥቀስ ይቻላል።ኢያሱ 6:17-19፤ 7:11-25፤ 2 ነገሥት 5:14-16, 20-27፤ ማቴዎስ 26:14, 15፤ ዮሐንስ 12:6

8 መጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኛ በመሆን ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ታሪክም ይዟል። ለምሳሌ፣ ያዕቆብ ልጆቹ በከረጢታቸው ውስጥ ያገኙት ገንዘብ በስህተት ገብቶ ይሆናል ብሎ ስላሰበ እንዲመልሱት አሳስቧቸው ነበር። የዮፍታሔንና የሴት ልጁን ሁኔታም ማስታወስ ይቻላል። የዮፍታሔ ልጅ አባቷ የተሳለውን ስእለት መፈጸም ከፍተኛ መሥዋዕትነት የሚጠይቅባት ቢሆንም ከመፈጸም ወደኋላ አላለችም። ኢየሱስም ስለ እሱ የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸምና ወዳጆቹን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲል አደጋ ሊያደርሱበት በመጡ በርካታ ሰዎች ፊት ማንነቱን በግልጽ ከመናገር ወደኋላ አላለም። (ዘፍጥረት 43:12፤ መሳፍንት 11:30-40፤ ዮሐንስ 18:3-11) ከብዙው በጥቂቱ የቀረቡት እነዚህ ምሳሌዎች፣ ወላጆች ልጆቻቸው ሐቀኝነትን እንዲወዱና ለዚህ ባሕርይ ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጡ ለማስተማር የሚረዷቸው በርካታ ታሪኮች በአምላክ ቃል ውስጥ እንደሚገኙ የሚያሳዩ ናቸው።

9. ወላጆች በሐቀኝነት ረገድ ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ ለመሆን ከፈለጉ ምን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል? የወላጆች ምሳሌነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

9 እንዲህ ያለው ትምህርት በወላጆች ላይ ከባድ ኃላፊነት ያስከትልባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ታዲያ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርም? አንተ ‘አትስረቅ’ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህ?” ሲል ተናግሯል። (ሮም 2:21) አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ሐቀኛ እንዲሆኑ እያስተማሩ ራሳቸው ግን ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት በመፈጸም ግራ ያጋቧቸዋል። ጥቃቅን ነገሮችን መስረቅ ወይም አሳሳች የሆነ ነገር መናገር ምንም ችግር እንደሌለበት ለማስመሰል “ሁሉም ሰው እንደሚወስድ ይታወቃል” ወይም “ይሄ ማንንም የማይጎዳ ውሸት ነው” የሚል ሰበብ ያቀርባሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የተሰረቀው ነገር አነሰም በዛ፣ ስርቆት ስርቆት ነው። እንዲሁም ርዕሰ ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን ወይም የተነገረው ውሸት ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን ውሸት ውሸት ነው። *  (ሉቃስ 16:10) ልጆች ግብዝነትን በማየት ረገድ ፈጣኖች ስለሆኑ በጣም ሊጎዱበት ይችላሉ። (ኤፌሶን 6:4) ከወላጆቻቸው ምሳሌነት ሐቀኝነትን ሲማሩ ግን በዚህ ሐቀኝነት በሌለበት ዓለም ይሖዋን የሚያስከብሩ ሆነው ያድጋሉ።ምሳሌ 22:6

በጉባኤ ውስጥ ሐቀኛ መሆን

10. ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ስንጨዋወት ምንጊዜም ሐቀኛ ለመሆን ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል?

10 ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር መቀራረባችን ሐቀኝነትን ለማዳበር የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎች ያስገኝልናል። በምዕራፍ 12 ላይ እንደተማርነው ከአምላክ ያገኘነውን የመናገር ስጦታ በተለይ ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በምንሆንበት ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል። ተራው ጭውውት በቀላሉ ወደ ሐሜት፣ አልፎ ተርፎም ወደ ስም ማጥፋት ሊያመራ ይችላል። ካልተረጋገጠ ምንጭ ያገኘነውን ወሬ ደግመን የምናወራ ከሆነ ውሸት በማሰራጨት መተባበር ስለሚሆንብን አንደበታችንን መቆጣጠራችን በጣም የተሻለ ነው። (ምሳሌ 10:19) በሌላ በኩል ደግሞ ወሬው እውነት እንደሆነ የምናውቅ ቢሆንም መነገር ያለበት ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ጉዳዩ ፈጽሞ የማይመለከተን ወይም ብንናገረው ደግነት የማይንጸባረቅበት ሊሆን ይችላል። (1 ተሰሎንቄ 4:11) አንዳንዶች ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ከተናገሩ በኋላ ‘የተናገርኩት ሐሰት አይደለም’ የሚል ሰበብ ያቀርባሉ። ይሁንና ከአንደበታችን የሚወጡት ቃላት ምንጊዜም ለዛ ያላቸውና ደግነት የተላበሱ መሆን ይገባቸዋል።ቆላስይስ 4:6

11, 12. (ሀ) ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ አንዳንድ ሰዎች ችግራቸውን ይበልጥ የሚያወሳስቡት እንዴት ነው? (ለ) ከባድ ኃጢአቶችን በተመለከተ ሰይጣን ከሚያስፋፋቸው ውሸቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? በእነዚህ ውሸቶች ላለመታለል ምን ማድረግ እንችላለን? (ሐ) ለይሖዋ ድርጅት ሐቀኞች መሆናችንን የምናሳየው እንዴት ነው?

 11 በተለይ በጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው ለሚያገለግሉ ወንድሞች ሐቀኛ መሆናችን በጣም አስፈላጊ ነው። ከባድ ኃጢአት የሠሩ አንዳንድ ግለሰቦች ኃጢአታቸውን በመሰወርና የጉባኤ ሽማግሌዎች ስለ ጉዳዩ በሚጠይቋቸው ጊዜም በመዋሸት ችግሩን ይበልጥ ያወሳስቡታል። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ከባድ ኃጢአት እየሠሩም ይሖዋን የሚያገለግሉ በመምሰል ሁለት ዓይነት ኑሮ መኖር ይጀምራሉ። ይህ አካሄዳቸው መላ ሕይወታቸው በውሸት የተሞላ እንዲሆን ያደርግባቸዋል። (መዝሙር 12:2) ሌሎች ደግሞ ዋናውን ነገር ደብቀው ከፊሉን እውነት ብቻ ለሽማግሌዎች ይናገራሉ። (የሐዋርያት ሥራ 5:1-11) እንዲህ ያለው ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት አብዛኛውን ጊዜ የሚመነጨው ሰይጣን የሚያስፋፋቸውን ውሸቶች ከማመን ነው።—“ ከባድ ኃጢአቶችን በሚመለከት ሰይጣን የሚያስፋፋቸው ውሸቶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

12 በተጨማሪም በጽሑፍ መልስ የምንሰጥባቸው አጋጣሚዎች ሲከሰቱ ለይሖዋ ድርጅት ሐቀኛ መሆናችን አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በመስክ አገልግሎት ያደረግነውን እንቅስቃሴ ሪፖርት ስናደርግ ትክክል ያልሆነ ነገር ሪፖርት እንዳናደርግ እንጠነቀቃለን። በተመሳሳይም አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት ለማግኘት የማመልከቻ ቅጽ በምንሞላበት ጊዜ ስለ ጤንነታችን ሁኔታ ወይም እኛን በሚመለከት ለሚቀርብልን ማንኛውም ጥያቄ የተሳሳተ መረጃ መስጠት የለብንም።ምሳሌ 6:16-19

13. ከአንድ የእምነት ባልንጀራችን ጋር በሥራ የምንገናኝ ከሆነ ሐቀኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

13 ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በሥራ የምንገናኝ ከሆነ በዚህ ረገድም ሐቀኞች መሆን ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር አብረው ሊሠሩ ይችላሉ። የሥራ ጉዳዮችንና በሥራ ቦታ ያላቸውን ግንኙነት በመስክ አገልግሎት ላይ ወይም በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከሚያከናውኑት አምልኮ ጋር እንዳያቀላቅሉት መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። የሥራ ግንኙነታቸው የአሠሪና የሠራተኛ ሊሆን ይችላል።  ወንድሞችን ወይም እህቶችን ቀጥረን የምናሠራ ከሆነ የተስማማንበትን ደመወዝ በጊዜው በመክፈልና በሕግ የተፈቀደላቸውን ጥቅማ ጥቅሞች በመስጠት በሐቀኝነት ልንይዛቸው ይገባል። (1 ጢሞቴዎስ 5:18፤ ያዕቆብ 5:1-4) በአንጻሩ ደግሞ ለአንድ ወንድም ወይም እህት ተቀጥረን የምንሠራ ከሆነ ለደመወዛችን የሚመጥነውን ሥራ ሳናጓድል እንሠራለን። (2 ተሰሎንቄ 3:10) አሠሪያችን ለሌሎች ሠራተኞች የማይሰጠውን ፈቃድ ወይም ሌላ ጥቅም ለእኛ የመስጠት ግዴታ ያለበት ይመስል በመንፈሳዊ የምንዛመድ በመሆናችን ብቻ ልዩ አስተያየት እንዲደረግልን አንጠብቅም።ኤፌሶን 6:5-8

14. ክርስቲያኖች በሽርክና ሥራ በሚጀምሩበት ጊዜ ምን ጥንቃቄ ያደርጋሉ? ለምንስ?

14 ከአንድ ክርስቲያን ጋር የሚያገናኘን የሥራ ጉዳይ በሽርክና አብሮ መሥራትን ወይም ገንዘብ ማበደርን አሊያም መበደርን የሚመለከት ቢሆንስ? በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊና ጠቃሚ የሆነ አንድ መመሪያ ይሰጣል:- እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ በጽሑፍ አስፍር! ለምሳሌ ኤርምያስ መሬት በገዛ ጊዜ የግዢውን ውል ምሥክሮች በተገኙበት በሁለት ቅጂ አዘጋጅቶ ለወደፊት ለማመሳከሪያነት እንዲያገለግል ጥሩ ቦታ እንዲቀመጥ አድርጓል። (ኤርምያስ 32:9-12፤ በተጨማሪም ዘፍጥረት 23:16-20ን ተመልከት።) ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር የንግድ ግንኙነት በሚኖረን ጊዜ ዝርዝር ነጥቦችን በጥንቃቄ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ማስፈራችንና ምሥክሮች በተገኙበት መፈራረማችን እንደማንተማመን የሚያሳይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በኋላ ላይ አለመግባባት፣ ብስጭትና መለያየትን የሚፈጥር ጭቅጭቅ እንዳይነሳ ለመከላከል ይረዳል። በአንድ ላይ የሚሠሩ ክርስቲያኖች ለንግድ ሥራቸው ሲሉ የጉባኤውን አንድነትና ሰላም መሥዋዕት ማድረግ ሞኝነት እንደሆነ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። *1 ቆሮንቶስ 6:1-8

በንግዱ ዓለምና በሌሎች መስኮች ሐቀኛ መሆን

15. ይሖዋ ሐቀኝነት በጎደለው መንገድ መነገድን በተመለከተ ምን ይሰማዋል? ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን የተለመደ ድርጊት በተመለከተ ምን አቋም አላቸው?

15 አንድ ክርስቲያን ሐቀኛ እንዲሆን የሚጠበቅበት ከክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር በተያያዘ ብቻ አይደለም። ጳውሎስ ‘በሁሉም ነገር በሐቀኝነት  ለመኖር እንመኛለን’ ብሏል። (ዕብራውያን 13:18) ፈጣሪያችን ከንግድ ሥራ ጋር በተያያዘ ሐቀኞች እንድንሆን ይፈልጋል። በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ ስለ ትክክለኛ ሚዛን አስፈላጊነት አራት ቦታዎች ላይ ተጠቅሷል። (ምሳሌ 11:1፤ 16:11፤ 20:10, 23) በጥንት ዘመን ሰዎች በሚገበያዩበት ጊዜ የተገዛውን ዕቃም ሆነ ለመገበያያ የሚያገለግለውን ገንዘብ ለመመዘን ሚዛኖችንና የሚዛን መለኪያ ድንጋዮችን መጠቀም የተለመደ ነበር። ሐቀኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች ደንበኞቻቸውን ለማጭበርበር ሁለት ዓይነት መለኪያዎችንና ትክክል ያልሆነ ሚዛን ይጠቀሙ ነበር። * ይሖዋ እንደዚህ ያለውን ድርጊት ይጠላል! ከይሖዋ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ሐቀኝነት ከጎደለው ከማንኛውም ዓይነት የንግድ ሥራ እንርቃለን።

16, 17. በዛሬው ዓለም ምን ዓይነት ሐቀኝነት የጎደላቸው ድርጊቶች የተለመዱ ናቸው? እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል?

16 ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ በመሆኑ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት በጣም መስፋፋቱ አያስደንቀንም። በየቀኑ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም ልንፈተን እንችላለን። ሰዎች ሥራ ለመቀጠር ማመልከቻ ሲያስገቡ የትምህርት ማስረጃቸውን እንዲሁም የሥራ ልምዳቸውን ማጋነናቸውና መዋሸታቸው የተለመደ ነገር ነው። ብዙውን ጊዜ ከኢሚግሬሽን፣ ከግብር፣ ከኢንሹራንስና ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር በተያያዘ ቅጾችን ሲሞሉ የሚፈልጉትን ለማግኘት ሲሉ የተሳሳተ መረጃ ይሰጣሉ። በርካታ ተማሪዎች ፈተና ላይ ይኮርጃሉ። በአንድ ርዕስ ላይ የጥናት ጽሑፍ ወይም ሪፖርት እንዲያቀርቡ በሚጠየቁበት ጊዜ ከኢንተርኔት ያገኙትን በቀጥታ በመገልበጥ የሌላውን ሰው ሥራ የራሳቸው እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ። ከዚህም በላይ ሰዎች ምግባረ ብልሹ የሆኑ ባለ ሥልጣናት በሚያጋጥሟቸው ጊዜ የሚፈልጉትን ለማግኘት ጉቦ ይሰጣሉ። ብዙዎች “ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . ጥሩ ነገር የማይወዱ” በሆኑበት በዚህ ዓለም ውስጥ ከዚህ የተለየ ነገር አንጠብቅም።2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

17 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደነዚህ ያሉትን ድርጊቶች ላለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። አንዳንድ ጊዜ ሐቀኝነትን ተፈታታኝ የሚያደርገው፣ ሐቀኝነት የጎደላቸውን ድርጊቶች የሚፈጽሙ ሰዎች በዛሬው ዓለም  የተሳካላቸው መስለው ወይም አድገው መታየታቸው ነው። (መዝሙር 73:1-8) ክርስቲያኖች ግን “በሁሉም ነገር” ሐቀኞች ለመሆን ስለሚፈልጉ የገንዘብ ኪሳራ ይደርስባቸው ይሆናል። ታዲያ ሐቀኛ ለመሆን ሲሉ ይህን ያህል መሥዋዕትነት መክፈላቸው የሚያስቆጫቸው ነው? በፍጹም የሚያስቆጭ አይደለም! ለምን? ሐቀኛ መሆን ምን በረከት ያስገኛል?

ሐቀኛ መሆን የሚያስገኛቸው በረከቶች

18. ሐቀኛ ነው የሚል ስም ማትረፍ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ለምንድን ነው?

18 ሐቀኛና እምነት የሚጣልበት ሰው ነው የሚል መልካም ስም ከማትረፍ የበለጠ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጣቸው ነገሮች ቢኖሩ በጣም ጥቂት ናቸው። (“ ሁልጊዜም ሐቀኛ ነኝ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ማንኛውም ሰው እንዲህ ያለውን መልካም ስም ማትረፍ ይችላል። ሐቀኛ መሆን በችሎታህ፣ በሀብትህ፣ በቁመናህ፣ በአስተዳደግህ ወይም ከአንተ አቅም በላይ በሆነ በማንኛውም በሌላ ነገር ላይ የተመካ አይደለም። ሆኖም ብዙ ሰዎች መልካም ስም በማትረፍ ረገድ አልተሳካላቸውም። ሐቀኝነት በቀላሉ የማይገኝ ብርቅ ባሕርይ ሆኗል። (ሚክያስ 7:2) አንዳንዶች ሐቀኛ በመሆንህ ያሾፉብህ ይሆናል፤ ሌሎች ግን ሐቀኝነትህን ከማድነቃቸው የተነሳ እምነት ይጥሉብሃል፣ አልፎ ተርፎም ያከብሩሃል። ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ሐቀኛ መሆናቸው የገንዘብ ጥቅም እንዳስገኘላቸው ተገንዝበዋል። ሐቀኝነት የጎደላቸው ሠራተኞች ከሥራ ሲባረሩ እነሱ ግን ሥራቸው ላይ እንዲቆዩ ተደርገዋል፤ ወይም ሐቀኛ ሠራተኞች በጣም በሚፈለጉባቸው ቦታዎች ለመቀጠር ችለዋል።

19. ሐቀኛ ሆነን መኖራችን ከሕሊናችን እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ካለን ዝምድና ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

19 እንዲህ ያለው ሁኔታ አጋጥሞህ የማያውቅ ቢሆን እንኳ ሐቀኝነት የበለጠ በረከት ያስገኝልሃል። ንጹሕ ሕሊና ይኖርሃል። ጳውሎስ “ሐቀኛ ሕሊና እንዳለን እርግጠኞች ነን” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 13:18) ከዚህም በላይ አፍቃሪው የሰማዩ አባታችን ሐቀኝነትህን ማየቱ አይቀርም። ይሖዋ ደግሞ ሐቀኛ የሆኑ ሰዎችን ይወዳል። (መዝሙር 15:1, 2፤ ምሳሌ 22:1) አዎ፣ ሐቀኛ መሆንህ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ እንድትኖር ይረዳሃል። ከዚህ የበለጠ ወሮታ ደግሞ ሊኖር አይችልም። ቀጥለን ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለው ርዕሰ ጉዳይ እንመለከታለን፤ ይህም ይሖዋ ለሥራ ያለው አመለካከት ነው።

^ አን.9 በጉባኤ ውስጥ ሆን ብሎ ሌሎችን ለመጉዳት በማሰብ ከባድ ውሸት የመናገር ልማድ ያለበት ሰው ካለ ሽማግሌዎች የፍርድ እርምጃ ሊወስዱበት ይችላሉ።

^ አን.14 አንድ የንግድ ሥራ ባይሳካ ወይም አንዳንድ ችግሮች ቢያጋጥሙ ምን መደረግ እንዳለበት “ገንዘብ ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን መፍታት” የሚለውን ተጨማሪ መረጃ ተመልከት።

^ አን.15 ሲገዙ አንድ ዓይነት የክብደት መለኪያ፣ ሲሸጡ ደግሞ ሌላ መለኪያ በመጠቀም ከሁለቱም ወገን ያተርፋሉ። በተጨማሪም በአንድ ወገን ክብደት በመጨመር ወይም በሌላ ዘዴ ሚዛንን በማዛባት በማንኛውም የንግድ ልውውጥ ደንበኞቻቸውን ያጭበረብራሉ።