በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’

 ተጨማሪ መረጃ

ለባንዲራ ሰላምታ መስጠት፣ ድምፅ መስጠትና የሲቪል አገልግሎት

ለባንዲራ ሰላምታ መስጠት፣ ድምፅ መስጠትና የሲቪል አገልግሎት

ለባንዲራ ሰላምታ መስጠት። የይሖዋ ምሥክሮች የሕዝብ መዝሙር እየተዘመረ ለባንዲራ ሰላምታ መስጠት፣ አዳኝነት የአምላክ ሳይሆን የአንድ ብሔር ወይም የመሪዎቹ መሆኑን የሚያሳይ ሃይማኖታዊ ድርጊት እንደሆነ ያምናሉ። (ኢሳይያስ 43:11፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14፤ 1 ዮሐንስ 5:21) የጥንቷ ባቢሎን ንጉሥ የነበረው ናቡከደነፆር ምን እንዳደረገ እንመልከት። ይህ ኃያል ንጉሥ፣ ሕዝቡ ታላቅነቱንና ሃይማኖታዊ ቅንዓቱን እንዲያደንቅለት ሲል አንድ ትልቅ ምስል አሠራ፤ ከዚያም እንደ ሕዝብ መዝሙር ያለ ሙዚቃ በሚሰማበት ጊዜ ተገዥዎቹ በሙሉ ለምስሉ እንዲሰግዱ አዘዘ። ይሁን እንጂ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉ ሦስት ዕብራውያን፣ የሞት ቅጣት የሚያስከትልባቸው ቢሆንም እንኳ ለምስሉ ለመስገድ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ።ዳንኤል ምዕራፍ 3

የታሪክ ምሑር የሆኑት ካርልተን ሄይዝ፣ በእኛ ዘመን “የብሔራዊ ስሜት ዋነኛ የእምነት ምልክትና የአምልኮ መሣሪያ ባንዲራ ነው” በማለት ጽፈዋል። “ወንዶች ባንዲራ በአጠገባቸው ሲያልፍ ባርኔጣቸውን ያነሳሉ፣ ገጣሚዎች ባንዲራን ለማወደስ ግጥም ይደርሳሉ፣ ልጆች መዝሙሮችን ይዘምራሉ።” አክለውም ብሔራዊ ስሜት፣ ልክ እንደ አንድ ሃይማኖት የራሱ የሆኑ በዓላት (በዩናይትድ ስቴትስ ሐምሌ 4 እንደሚከበረው ያሉ)፣ “ቅዱሳንና ገድለኞች” እንዲሁም “መቅደሶች” እንዳሉት ጽፈዋል። በብራዚል በተደረገ ሕዝባዊ በዓል ላይ የሠራዊቱ አዛዥ “አባት አገር እንደሚመለከው ሁሉ ባንዲራም ቅዱስ ተደርጎ ይታያል፣ ይመለካልም” ብለዋል። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና በአንድ ወቅት “ባንዲራ ልክ እንደ መስቀል ቅዱስ ነው” ብሏል።

ከላይ የተጠቀሰው ኢንሳይክሎፒዲያ በቅርቡ እንደገለጸው የሕዝብ መዝሙሮች፣ “የአገር ፍቅር ስሜት መግለጫዎች ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ አምላክ ሕዝቡን ወይም የአገሪቱን መሪዎች እንዲጠብቃቸው እና እንዲመራቸው የሚቀርቡ ልመናዎች ናቸው።” ስለሆነም የይሖዋ አገልጋዮች፣ ለባንዲራ ሰላምታ መስጠትንና የሕዝብ መዝሙርን የሚያካትቱ ብሔራዊ ስሜት የሚንጸባረቅባቸው ክብረ በዓሎችን እንደ አምልኮ መቁጠራቸው ምክንያተቢስ ናቸው አያሰኛቸውም። እንዲያውም ዚ አሜሪካን ካራክተር የተባለው መጽሐፍ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች በዩናይትድ ስቴትስ ትምህርት ቤቶች ለባንዲራ ሰላምታ ለመስጠትም ሆነ  የታማኝነት ቃለ መሐላ ለመፈጸም ፈቃደኞች ስላለመሆናቸው አስተያየት ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሰጣቸው ተከታታይ ብይኖች በየዕለቱ የሚፈጸሙት እነዚህ ሥነ ሥርዓቶች ሃይማኖታዊ ይዘት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።”

የይሖዋ ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱስ በማይደግፋቸው ሥነ ሥርዓቶች ለመካፈል ፈቃደኛ ባይሆኑም ሌሎች ሰዎች በእነዚህ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ለመካፈል ያላቸውን መብት ያከብራሉ። በተጨማሪም ብሔራዊ ባንዲራዎች አንድን አገር የሚወክሉ ምልክቶች በመሆናቸው ያከብሯቸዋል፤ እንዲሁም ሕጋዊ መንግሥታት ‘የበላይ ባለሥልጣናት’ እንደሆኑና “የአምላክ አገልጋይ” ሆነው እንደሚሠሩ ይቀበላሉ። (ሮም 13:1-4) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች “ነገሥታትንና በሥልጣን ላይ ያሉትን ሁሉ በተመለከተ” እንዲጸልዩ የተሰጣቸውን ማሳሰቢያ ይፈጽማሉ። ይሁን እንጂ ይህን የምናደርግበት ዓላማ “ሙሉ በሙሉ ለአምላክ በማደርና በጥልቅ ማስተዋል በጸጥታና በተረጋጋ ሁኔታ መኖራችንን እንቀጥል ዘንድ ነው።”1 ጢሞቴዎስ 2:2

በፖለቲካ ምርጫዎች ወቅት ድምፅ መስጠት። እውነተኛ ክርስቲያኖች የሌሎችን ድምፅ የመስጠት መብት ወይም የመምረጥ ነፃነት ያከብራሉ። ምርጫዎችን በመቃወም ዘመቻ አያካሂዱም፣ ከተመረጡ ባለ ሥልጣናት ጋር ይተባበራሉ። ይሁን እንጂ በብሔራት የፖለቲካ ጉዳዮች ረገድ ፍጹም ገለልተኞች ለመሆን ቆራጥ አቋም አላቸው። (ማቴዎስ 22:21፤ 1 ጴጥሮስ 3:16) አንድ ክርስቲያን ድምፅ መስጠት ግዴታ በሚሆንባቸው አገሮች ወይም ወደ ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች በማይሄዱ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ችግር በሚደርስባቸው አካባቢዎች የሚኖር ከሆነ ምን ያደርጋል? ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ እስከ ዱራ ሜዳ ሄደው እንደነበረ በማስታወስ ሕሊናው ከፈቀደለት ወደ ምርጫ ጣቢያው ለመሄድ ሊወስን ይችላል። ይሁን እንጂ የገለልተኝነት አቋሙን የሚያስጥስ አንዳች ነገር እንዳያደርግ ይጠነቀቃል። የሚከተሉትን ስድስት መሠረታዊ ሥርዓቶች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል:-

  1. የኢየሱስ ተከታዮች ‘የዓለም ክፍል አይደሉም።’ዮሐንስ 15:19

  2. ክርስቲያኖች የክርስቶስና የመንግሥቱ ወኪሎች ናቸው።ዮሐንስ 18:36፤ 2 ቆሮንቶስ 5:20

  3. የክርስቲያን ጉባኤ የእምነት አንድነት ያለው ሲሆን አባሎቹም ክርስቶስ በነበረው ዓይነት ፍቅር የተሳሰሩ ናቸው።1 ቆሮንቶስ 1:10፤ ቆላስይስ 3:14

  4.   አንድን ባለ ሥልጣን የሚመርጡ ሰዎች ይህ ባለ ሥልጣን ለሚያደርጋቸው ነገሮች በኃላፊነት ይጠየቃሉ።—በ1 ሳሙኤል 8:5, 10-18 እና በ1 ጢሞቴዎስ 5:22 ላይ ያሉት ሐሳቦች የያዟቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ልብ በል።

  5. የእስራኤል ሕዝብ የሚታይ ንጉሥ ለማንገሥ መፈለጉ ይሖዋን እንደመናቅ ተቆጥሮበታል።1 ሳሙኤል 8:7

  6. ክርስቲያኖች ማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት በሚያነጋግሩበት ጊዜ የመናገር ነፃነት ሊሰማቸው ይገባል።ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ዕብራውያን 10:35

የሲቪል አገልግሎት። በአንዳንድ አገሮች መንግሥታት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችን ለተወሰነ ጊዜ በነፃ አንድ ዓይነት የሲቪል አገልግሎት እንዲሰጡ ያስገድዳሉ። በዚህ ረገድ ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልገን ስለ ጉዳዩ መጸለይና ምናልባትም ከጎለመሰ ክርስቲያን ጋር መወያየት አለብን፤ ከዚያም በበቂ መረጃ ላይ ተመሥርተን ሕሊናችን የሚነግረንን ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል።ምሳሌ 2:1-5፤ ፊልጵስዩስ 4:5

የአምላክ ቃል ‘ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት እንድንታዘዝና ለመልካም ሥራ ሁሉ ዝግጁዎች እንድንሆን እንዲሁም ምክንያታዊ እንድንሆን’ ይመክረናል። (ቲቶ 3:1, 2) ይህን በአእምሯችን ይዘን ራሳችንን የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ እንችላለን:- ‘የተጠየቅኩትን የሲቪል አገልግሎት መፈጸሜ ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሜን እንዳላላ ወይም ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ ያለው ነገር እንድሠራ ያደርገኛል?’ (ሚክያስ 4:3, 5፤ 2 ቆሮንቶስ 6:16, 17) ‘ይህን ሥራ መሥራቴ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቼን መወጣት እንዲከብደኝ ወይም ጭራሹኑ እንዳልወጣቸው ያደርገኛል?’ (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ኤፌሶን 6:4፤ ዕብራውያን 10:24, 25) ‘በአንጻሩ ደግሞ እንዲህ ያለውን አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኔ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዬን ለማስፋት፣ ምናልባትም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል የሚያስችል ጊዜ ያስገኝልኛል?ዕብራውያን 6:11, 12

አንድ ክርስቲያን ጉዳዩን በሚገባ ካሰበበት በኋላ እስር ቤት ከመግባት ይልቅ ሲቪል አገልግሎት መስጠት እንደሚሻለው ቢወስን፣ ሌሎች ክርስቲያኖች ውሳኔውን ሊያከብሩለት ይገባል። (ሮም 14:10) ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለውን አገልግሎት መስጠት እንደማይፈልግ ከወሰነም ይህንን አቋሙን ሊያከብሩለት ይገባል።1 ቆሮንቶስ 10:29፤ 2 ቆሮንቶስ 1:24