በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’

 ምዕራፍ 7

ልክ እንደ አምላክ ለሕይወት ከፍተኛ ዋጋ ትሰጣለህ?

ልክ እንደ አምላክ ለሕይወት ከፍተኛ ዋጋ ትሰጣለህ?

“የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነው።”መዝሙር 36:9

1, 2. ከፍተኛ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የማገናዘብ ችሎታ በተለይ በዛሬው ጊዜ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

የሰማዩ አባታችን በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ ስጦታ ሰጥቶናል። ይህ ስጦታ የእሱን ባሕርያት የማንጸባረቅና የማሰብ ችሎታ ያለን ሰብዓዊ ፍጡራን ሆነን እንድንኖር ያስቻለን የሕይወት ስጦታ ነው። (ዘፍጥረት 1:27) ይህ ውድ ስጦታ ስላለን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማገናዘብ ችለናል። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ በማዋል ይሖዋን የምንወድ እንዲሁም “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንድንችል የማስተዋል ችሎታችንን በማሠራት ያሠለጠንን” ጎልማሳ ክርስቲያኖች መሆን እንችላለን።—ዕብራውያን 5:14

2 የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የማገናዘብ ችሎታ በተለይ በዛሬው ጊዜ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ምንም ያህል ብዙ ሕጎች ቢወጡ በሕይወት ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ሁኔታዎች በሙሉ ማካተት እስከማይቻል ድረስ ዓለም በጣም ውስብስብ ሆኗል። በዚህ ረገድ ከደም ከሚቀመሙ መድኃኒቶችና ደምን መጠቀምን ከሚጠይቁ የሕክምና ዓይነቶች ጋር በተያያዘ ብዙ መሻሻል የሚያደርገው የሕክምናው ሳይንስ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ይህ ይሖዋን ለመታዘዝ የሚፈልጉ ሰዎችን በሙሉ ሊያሳስባቸው የሚገባ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። እንደዚያም ሆኖ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመረዳት ሕሊናችንን የሚያረካና ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ እንድንኖር የሚያስችለን ውሳኔ ላይ መድረስ መቻል ይኖርብናል። (ምሳሌ 2:6-11) እስቲ ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንዳንዶቹን እንመልከት።

 ሕይወትና ደም ቅዱስ ናቸው

3, 4. ደም ቅዱስ መሆኑ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸው መቼ ነበር? የተመሠረተውስ በየትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ነው?

3 ይሖዋ ሕይወትና ደም የማይነጣጠሉ ነገሮች ስለመሆናቸውና ሁለቱም ቅዱስ እንደሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የገለጸው ቃየን አቤልን ከገደለው በኋላ ነበር። አምላክ ቃየንን “ስማ! የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 4:10) በይሖዋ ዓይን የአቤል ደም በአጭር የተቀጨውን ሕይወቱን ይወክል ነበር። በመሆኑም የአቤል ደም ወደ አምላክ ለበቀል ይጮኽ ነበር ለማለት ይቻላል።ዕብራውያን 12:24

4 ከኖኅ የጥፋት ውኃ በኋላ አምላክ የሰው ልጆች የእንስሳትን ሥጋ እንዲበሉ የፈቀደላቸው ሲሆን ደሙን ግን እንዲበሉ አልፈቀደላቸውም። አምላክ “ነፍሱ ደሙ ያለችበትን ሥጋ አትብሉ፤ ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ” ብሏል። (ዘፍጥረት 9:4, 5 የ1954 ትርጉም) ይህ ትእዛዝ በዘመናችን ያሉ ሰዎችን ጨምሮ በኖኅ ዘሮች ሁሉ ላይ የሚሠራ ከመሆኑም በላይ አምላክ ቀደም ሲል ደም የፍጥረትን ሁሉ ነፍስ ወይም ሕይወት እንደሚወክል ለቃየን በተዘዋዋሪ መንገድ የተናገረውን ሐሳብ ያጠናክራል። በተጨማሪም ይህ ትእዛዝ ለሕይወትና ለደም አክብሮት የማያሳዩ ሰዎች ሁሉ የሕይወት ምንጭ በሆነው በይሖዋ ፊት ተጠያቂዎች መሆናቸውን ያረጋግጣል።መዝሙር 36:9

5, 6. የሙሴ ሕግ ደም ቅዱስና ውድ ነገር እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው? (በተጨማሪም “ ለእንስሳት ሕይወት አክብሮት ይኑርህ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

5 እነዚህ ሁለት መሠረታዊ እውነቶች በሙሴ ሕግ ውስጥ ተንጸባርቀዋል። ዘሌዋውያን 17:10, 11 እንዲህ ይላል:- “ማንኛውም [ሰው] . . . ደም ቢበላ፣ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ፤ የፍጡር ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ በመሠዊያ ላይ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ደሙን ሰጥቻችኋለሁ፤ ለሰውም ሕይወት ስርየት የሚያስገኝ ደም ነው።” *—“ ደም ያለው የማስተሰረይ ኃይል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

 6 የአንድ የታረደ እንስሳ ደም ማስተሰረያ ለመሆን መሠዊያ ላይ ካልፈሰሰ መሬት ላይ መፍሰስ ነበረበት። በዚህ መንገድ በምሳሌያዊ ሁኔታ ያ ሕይወት፣ የሕይወት ሁሉ ባለቤት ወደሆነው አምላክ ይመለሳል። (ዘዳግም 12:16፤ ሕዝቅኤል 18:4) ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በእንስሳው ሥጋ ውስጥ አንድ ጠብታ ደም እንኳ እንዳይቀር የተለየ ጥረት እንዲያደርጉ እንዳልተነገራቸው ልብ በል። እንስሳው በተገቢው መንገድ ታርዶ ደሙ ከፈሰሰ፣ የሕይወት ምንጭ ለሆነው አምላክ የሚገባው ክብር ስለተሰጠ  ማንኛውም እስራኤላዊ ሕሊናው ሳይወቅሰው ሥጋውን ሊበላ ይችላል።

7. ዳዊት ለደም ቅድስና አክብሮት ያሳየው እንዴት ነው?

7 አምላክ “እንደ ልቤ” ያለው ዳዊት ስለ ደም የተሰጠው ሕግ የተመሠረተበትን መሠረታዊ ሥርዓት በሚገባ ተረድቶ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 13:22) በአንድ ወቅት ውኃ በጣም ጠምቶት በነበረ ጊዜ ሦስቱ ኃያላን ሰዎች የጠላትን ሰፈር ሰንጥቀው በማለፍ ውኃ ከጉድጓድ ቀድተው አመጡለት። ዳዊት ምን ተሰማው? “ይህ በነፍሳቸው ቈርጠው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን?” ሲል ጠየቀ። በዳዊት ዓይን ያ ውኃ የሰዎቹ ደም ነበር። ስለሆነም ምንም ያህል ውኃ ቢጠማውም “[በይሖዋ] ፊት . . . አፈሰሰው።”2 ሳሙኤል 23:15-17

8, 9. የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ አምላክ ለደምና ለሕይወት ያለው አመለካከት ተለውጧል? አብራራ።

8 ደምን አስመልክቶ ለኖኅ ትእዛዝ ከተሰጠ ከ2,400 ዓመታት ገደማ በኋላና የሕጉ ቃል ኪዳን ከተሰጠ 1,500 ዓመታት ያህል ቆይቶ፣ ይሖዋ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ የበላይ አካል የሚከተለውን እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል:- “ከሚከተሉት አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳንጭንባችሁ መንፈስ ቅዱስና እኛ ወስነናል፤ ለጣዖት ከተሠዉ ነገሮች፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋና ከዝሙት ራቁ።”የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29

9 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የመጀመሪያው መቶ ዘመን የበላይ አካል፣ ደም ቅዱስ ነገር መሆኑንና ደምን አለአግባብ መጠቀም ከጣዖት አምልኮ ወይም ከዝሙት ተለይቶ የማይታይ መጥፎ ድርጊት እንደሆነ አስተውሎ ነበር። ዛሬም እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህን መመሪያ ያከብራሉ። ከዚህም በላይ የሚመሩት በሕግ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመሆኑ ከደም አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ውሳኔዎችን በሚያደርጉበት ጊዜ ይሖዋን ማስደሰት ይችላሉ።

ደም ለሕክምና አገልግሎት ሲውል

የደም ንዑሳን ክፍልፋዮችን በተመለከተ ያለኝን አቋም ለአንድ ሐኪም እንዴት ማስረዳት እችላለሁ?

10, 11. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉውን ደም ወይም ዋና ዋናዎቹን የደም ክፍሎች ስለመውሰድ ምን አመለካከት አላቸው? (ለ) ክርስቲያኖች ደምን በተመለከተ የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው የሚችለው መቼ ነው?

10 የይሖዋ ምሥክሮች ‘ከደም ራቁ’ የሚለው ትእዛዝ፣ ደምን ለሕክምና ሲባል በደም ሥር ከመውሰድ፣ ለሌላ ሰው ከመለገስ ወይም  የራስ ደም ከሰውነት ወጥቶ ከቆየ በኋላ በደም ሥር መልሶ ከመውሰድ መቆጠብ ማለት እንደሆነ ይገነዘባሉ። ለአምላክ ሕግ አክብሮት ስላላቸው አራቱን አበይት የደም ክፍልፋዮች ማለትም ቀይ የደም ሴል፣ ነጭ የደም ሴል፣ ፕሌትሌትና ፕላዝማ አይወስዱም።

11 በዛሬው ጊዜ ሳይንሳዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ከእነዚህ አበይት የደም ክፍልፋዮች የሚወጡትን ንዑሳን ክፍልፋዮች በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ ማዋል ተችሏል። አንድ ክርስቲያን እነዚህን ንዑሳን ክፍልፋዮች ለሕክምና ሊወስድ ይችላል? እነዚህን ክፍልፋዮች እንደ “ደም” አድርጎ ይመለከታቸዋል? በዚህ ጉዳይ ላይ እያንዳንዱ ክርስቲያን የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። ደሙ ከሰውነት ተወስዶ እንዲቀመጥ እስካልተደረገ ድረስ ሄሞዳያሊስስን፣ ሄሞዳይሉሽንን እንዲሁም የራስን ደም መጠቀም የሚቻልበትን ዘዴ ማለትም ሴል ሳልቬጅንና የመሳሰሉትን የሕክምና ዓይነቶች በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።—“ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችና የቀዶ ሕክምና ሂደቶች” የሚለውን ተጨማሪ መረጃ ተመልከት።

12. ለሕሊና የተተዉ ጉዳዮችን እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል? እነዚህን ጉዳዮች ልንይዛቸው የሚገባውስ እንዴት ነው?

 12 ለግል ውሳኔ የተተዉ ጉዳዮችን በተመለከተ የፈለግነውን ብንወስን ይሖዋ ግድ የለውም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም፣ ምክንያቱም ይሖዋ የምናስበውን ነገርና አንድ ውሳኔ ላይ እንድንደርስ ያነሳሳንን ውስጣዊ ግፊት ትኩረት ሰጥቶ ይከታተላል። (ምሳሌ 17:3፤ 21:2፤ 24:12) በመሆኑም ስለ አንድ መድኃኒት ወይም የሕክምና ዓይነት ጸሎት የታከለበት ምርምር ካደረግን በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናችን የሚነግረንን መታዘዝ ይኖርብናል። (ሮም 14:2, 22, 23) እርግጥ ነው፣ ሌሎች የእነሱን ውሳኔ እንድንቀበል ሊገፋፉን አይገባም፤ ወይም “አንተ በእኔ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?” ብለን መጠየቅ ተገቢ አይደለም። እንደነዚህ ባሉት ጉዳዮች እያንዳንዱ ክርስቲያን “የራሱን ሸክም ሊሸከም” ይገባል። *ገላትያ 6:5፤ ሮም 14:12፤ “ ደምን እንደ ቅዱስ ነገር እመለከታለሁ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

የይሖዋ ሕጎች የአባትነት ፍቅሩን ያንጸባርቃሉ

13. የይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ስለ እሱ ምን ያሳያሉ? በምሳሌ አስረዳ።

13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ ይሖዋ ታላቅ ጥበብ ያለው ሕግ አውጪና ስለ ልጆቹ ደህንነት በጥልቅ የሚያስብ አፍቃሪ አባት እንደሆነ ያሳያሉ። (መዝሙር 19:7-11) ‘ከደም ራቁ’ የሚለው ትእዛዝ የተሰጠው ከጤንነት አንጻር ባይሆንም እንኳ ደም በመውሰድ ምክንያት ከሚመጡ የጤና ችግሮች ይጠብቀናል። (የሐዋርያት ሥራ 15:20) እንዲያውም በሕክምናው መስክ የተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎች ያለደም የሚደረግን ቀዶ ሕክምና “ወርቃማው የሕክምና ዘዴ” ሲሉ ጠርተውታል። እንደነዚህ ያሉት ግኝቶች ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋ ወደር የማይገኝለት ጥበብና አባታዊ ፍቅር እንዳለው የሚያረጋግጡ ናቸው።ኢሳይያስ 55:9፤ ዮሐንስ 14:21, 23

14, 15. (ሀ) አምላክ ለሕዝቦቹ ፍቅር እንዳለው የሚያሳዩት የትኞቹ ሕጎች ናቸው? (ለ) አደጋን ለመከላከል የሚያስችሉት እነዚህ ሕጎች የተመሠረቱባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ማዋል የምትችለው እንዴት ነው?

14 አምላክ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የሰጣቸው ብዙዎቹ ሕጎች ለሕዝቡ  ደህንነት ያስብ እንደነበረ ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን በቤታቸው ጣሪያ ላይ ብዙ እንቅስቃሴ ያደርጉ ስለነበር አደጋ እንዳይደርስ ለመከላከል በጣሪያቸው ዙሪያ መከታ እንዲሠሩ አዟቸዋል። (ዘዳግም 22:8፤ 1 ሳሙኤል 9:25, 26፤ ነህምያ 8:16፤ የሐዋርያት ሥራ 10:9) በተጨማሪም አምላክ ተዋጊ በሬዎች እንዲሁ መለቀቅ እንደሌለባቸው የሚያዝዝ ሕግ ሰጥቷቸዋል። (ዘፀአት 21:28, 29) እነዚህን ትእዛዛት ችላ ማለት ለሌሎች ደህንነት ደንታ ቢስ መሆንን ስለሚያመለክት በደም ዕዳ ተጠያቂ ያደርግ ነበር።

15 እነዚህ ሕጎች የተመሠረቱባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ማዋል የምትችለው እንዴት ነው? እስቲ ቆም ብለህ ስለ መኪናህ፣ ስለምታሽከረክርበት መንገድ፣ ስለ እንስሶችህ፣ ስለ ቤትህና ስለ ሥራ ቦታህ እንዲሁም ስለ መዝናኛ ምርጫህ አስብ። በአንዳንድ አገሮች ለወጣቶች ሞት ዋነኛው መንስኤ አደጋ ነው። ምክንያቱም ወጣቶች ለአደጋ የሚያጋልጡ የጀብደኝነት ድርጊቶችን መፈጸም ያስደስታቸዋል። ከአምላክ ፍቅር ሳይወጡ ለመኖር የሚፈልጉ ወጣቶች ግን ለሕይወት ከፍተኛ ዋጋ ስለሚሰጡ አደገኛ በሆኑ እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ ደስታ ለማግኘት አይሞክሩም። ‘ወጣት ስለሆንን ምንም አንሆንም’ እያሉ ራሳቸውን አያሞኙም። ከዚህ ይልቅ አደጋ ከሚጋብዝ ነገር በመሸሽ በወጣትነት ዕድሜያቸው ይደሰታሉ።መክብብ 11:9, 10

16. ውርጃ ትክክል እንዳልሆነ የሚያመለክተው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት የትኛው ነው? (በተጨማሪም የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

16 በማህጸን ውስጥ ያለ ጽንስ እንኳ በአምላክ ዓይን ውድ ነው። በጥንት እስራኤል፣ አንድ ሰው ነፍሰ ጡር በሆነች ሴት ላይ ጉዳት ቢያደርስና በዚህም ምክንያት ሴቲቱ ወይም ጽንሱ ቢሞቱ፣ አምላክ ጉዳት ያደረሰውን ሰው እንደ ነፍሰ ገዳይ ስለሚቆጥረው “ሕይወት በሕይወት” እንዲከፍል ይደረግ ነበር። * (ዘፀአት 21:22, 23) በመሆኑም ይሖዋ፣ በየዓመቱ በውርጃ አማካኝነት ሕይወታቸው የሚቀጨውን ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሕፃናት ሲመለከት ምን እንደሚሰማው መገመት ትችላለህ፤ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ መሥዋዕት የሚደረጉት ከኃላፊነት ነፃ ለመሆንና በሥነ ምግባር ልቅ የሆነ ሕይወት ለመምራት ሲባል ነው።

17. ስለ አምላክ መሥፈርቶች ከመማሯ በፊት ጽንስ አስወርዳ የምታውቅን ሴት እንዴት ማጽናናት ትችላለህ?

 17 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከመማሯ በፊት ጽንስ አስወርዳ ስለምታውቅ ሴት ምን ማለት ይቻላል? አምላክ ፈጽሞ ምሕረት አያደርግላትም?  ያደርግላታል። እንዲያውም አንድ ሰው ከልቡ ንስሐ ከገባ ይሖዋ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም አማካኝነት ይቅርታ እንደሚያደርግለት እርግጠኛ ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 103:8-14፤ ኤፌሶን 1:7) ክርስቶስ ራሱ “እኔ የመጣሁት ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ ለመጥራት እንጂ ጻድቃንን ለመጥራት አይደለም” ብሏል።ሉቃስ 5:32

የጥላቻ አስተሳሰብን አስወግድ!

18. መጽሐፍ ቅዱስ ለከፍተኛ ደም መፋሰስ ምክንያት የሆነውን ነገር የሚገልጸው እንዴት ነው?

18 ይሖዋ ሌሎችን ከመጉዳት እንድንቆጠብ ብቻ ሳይሆን ለከፍተኛ ደም መፋሰስ ምክንያት የሆነውን ጥላቻን ከልባችን ነቅለን እንድናወጣም ይጠብቅብናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 3:15) እንዲህ ዓይነቱ ሰው ወንድሙን ከመጥላት አልፎ እንዲሞት ይመኛል። ይህ ጥላቻው በተንኮል ስም በማጥፋት ወይም እውነት ቢሆን ኖሮ በተከሳሹ ላይ መለኮታዊ ፍርድ ሊያስከትል የሚችል የሐሰት ክስ በመሰንዘር ይገለጣል። (ዘሌዋውያን 19:16፤ ዘዳግም 19:18-21፤ ማቴዎስ 5:22) በመሆኑም በልባችን ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ማንኛውንም ዓይነት ጥላቻ ለማስወገድ መጣራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!ያዕቆብ 1:14, 15፤ 4:1-3

19. በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራ ሰው እንደ መዝሙር 11:5 እና ፊልጵስዩስ 4:8, 9 ያሉትን ጥቅሶች እንዴት ይመለከታቸዋል?

19 ልክ እንደ ይሖዋ ለሕይወት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጡና ከእርሱ ፍቅር ሳይወጡ ለመኖር የሚፈልጉ ሁሉ ከማንኛውም ዓይነት የዓመጽ ድርጊት ይርቃሉ። መዝሙር 11:5 “ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ [የይሖዋ ነፍስ] ትጠላቸዋለች” ይላል። ይህ ጥቅስ የአምላክን ባሕርይ ከመግለጽ አልፎ ለሕይወታችን መመሪያ የሚሆን መሠረታዊ ሥርዓት ይዟል። ለአምላክ ፍቅር ያላቸውን ሰዎች ዓመጽን እንዲወዱ ሊያበረታታቸው ከሚችል ከማንኛውም ዓይነት መዝናኛ እንዲርቁ ይገፋፋቸዋል። በተመሳሳይም ይሖዋ ‘የሰላም አምላክ’ እንደሆነ የተሰጠው መግለጫ አገልጋዮቹ አእምሯቸውንና ልባቸውን ሰላም ለመፍጠር በሚያስችሏቸው ተወዳጅና በጎ በሆኑ እንዲሁም በሚያስመሰግኑ ነገሮች እንዲሞሉ ያነሳሳቸዋል።ፊልጵስዩስ 4:8, 9

በደም ዕዳ ተጠያቂ ከሆኑ ድርጅቶች ራቅ

20-22. ክርስቲያኖች ከዚህ ዓለም ጋር በተያያዘ አቋማቸው ምንድን ነው? ለምንስ?

20 በአምላክ ዓይን መላው የሰይጣን ሥርዓት በደም ዕዳ ተጠያቂ ነው።  በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በጨካኝ አውሬ የተመሰለው የሰይጣን የፖለቲካ ሥርዓት በርካታ የይሖዋ አገልጋዮችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ደም አፍስሷል። (ዳንኤል 8:3, 4, 20-22፤ ራእይ 13:1, 2, 7, 8) የሳይንሱና የንግዱ ዘርፍም ከእነዚህ በአውሬ የተመሰሉ ኃይሎች ጋር እጅና ጓንት በመሆን እጅግ አውዳሚ የሆኑ የጦር መሣሪያዎችን በመፈልሰፍና በማምረት ከፍተኛ ትርፍ አጋብሷል። ‘መላው ዓለም በክፉው ኃይል ሥር’ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው!1 ዮሐንስ 5:19

21 የኢየሱስ ተከታዮች ‘የዓለም ክፍል ስላልሆኑ’ እንዲሁም በዚህ ዓለም ፖለቲካም ሆነ ጦርነቶች ፈጽሞ ስለማይካፈሉ በግለሰብ ደረጃ በደም ዕዳ ተጠያቂ አይሆኑም፤ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ካለበት የደም ዕዳ ነፃ ናቸው። * (ዮሐንስ 15:19፤ 17:16) በተጨማሪም የክርስቶስን አርዓያ በመከተል ሌሎች በሚያሳድዷቸው ጊዜ አጸፋውን አይመልሱም። ከዚህ ይልቅ ለጠላቶቻቸው ፍቅር ያሳያሉ፣ አልፎ ተርፎም ይጸልዩላቸዋል።ማቴዎስ 5:44፤ ሮም 12:17-21

22 ከሁሉ በላይ እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓለም ካሉ ድርጅቶች በሙሉ  በዋነኝነት በደም ዕዳ ከምትጠየቀውና የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖራቸው ይጠነቀቃሉ። የአምላክ ቃል “በእሷ ውስጥ የነቢያት፣ የቅዱሳንና በምድር ላይ የታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም ተገኝቷል” ይላል። በዚህም ምክንያት “ሕዝቤ ሆይ፣ . . . ከእሷ ውጡ” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል።ራእይ 17:6፤ 18:2, 4, 24

23. ከታላቂቱ ባቢሎን መውጣት ሲባል ምን ማለት ነው?

23 ከታላቂቱ ባቢሎን መውጣት ስምን ከአባልነት መዝገብ ላይ ከማሰረዝ ያለፈ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። የሐሰት ሃይማኖት ችላ ብሎ የሚያልፋቸውን ወይም በይፋ የሚደግፋቸውን ነገሮች ማለትም የሥነ ምግባር ብልግናን፣ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትን፣ ለሀብት መስገብገብንና የመሳሰሉትን ክፉ ድርጊቶች መጥላትን ይጨምራል። (መዝሙር 97:10፤ ራእይ 18:7, 9, 11-17) እነዚህ ድርጊቶች ብዙውን ጊዜ ለደም መፋሰስ ምክንያት ይሆናሉ።

24, 25. አምላክ የደም ዕዳ ላለበት አንድ ንስሐ የገባ ሰው ምሕረት ሊያደርግ የሚችለው በምን አማካኝነት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ለዚህ ጥላ ሆኖ ያገለገለው ምንድን ነው?

24 ሁላችንም እውነተኛውን አምልኮ ከመቀበላችን በፊት በአንዱ ወይም በሌላው መንገድ ለሰይጣን ሥርዓት ድጋፍ እንሰጥ ስለነበር ከፍተኛ የደም ዕዳ ነበረብን። ይሁን እንጂ የአኗኗር ለውጥ ስላደረግን፣ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ስላሳደርን፣ እንዲሁም ሕይወታችንን ለአምላክ ስለወሰንን የአምላክን ምሕረትና መንፈሳዊ ጥበቃ አግኝተናል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩት መማጸኛ ከተሞች እንዲህ ላለው መንፈሳዊ ጥበቃ ጥላ ነበሩ።ዘኍልቍ 35:11-15፤ ዘዳግም 21:1-9

25 ይህ ዝግጅት የሚሠራው እንዴት ነበር? አንድ እስራኤላዊ ሳያስበው የሌላውን እስራኤላዊ ነፍስ ቢያጠፋ ከመማጸኛ ከተሞች ወደ አንዱ መሸሽ ይኖርበት ነበር። ብቃት ያላቸው ዳኞች በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ከሰጡ በኋላ ሳያስበው ነፍስ ያጠፋው ሰው ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማጸኛ ከተማ ውስጥ መኖር ነበረበት። ሊቀ ካህናቱ ከሞተ በኋላ ግን በፈለገው ቦታ መኖር ይችላል። ይህ ዝግጅት አምላክ መሐሪ መሆኑንና ለሕይወት ከፍተኛ ዋጋ እንደሚሰጥ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው። ዛሬም ከእነዚህ መማጸኛ ከተሞች ጋር የሚመሳሰል ዝግጅት አለ፤ አምላክ ስለ  ሕይወትና ስለ ደም ቅድስና ያወጣውን ትእዛዝ ሳይታወቀን በመተላለፋችን ከሚመጣብን ሞት እኛን ለመታደግ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ዝግጅት አድርጎልናል። ለዚህ ዝግጅት ከፍተኛ አድናቆት አለህ? አድናቆት እንዳለህ እንዴት ማሳየት ትችላለህ? አንደኛው መንገድ በተለይ ‘ታላቁ መከራ’ በጣም በቀረበበት በዚህ ዘመን ሌሎች ሰዎች ወደ እውነተኛው መማጸኛ ከተማ እንዲገቡ በመጋበዝ ነው።ማቴዎስ 24:21፤ 2 ቆሮንቶስ 6:1, 2

የመንግሥቱን መልእክት በመስበክ ለሕይወት ከፍተኛ ዋጋ እንደምትሰጥ አሳይ

26-28. ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ነቢዩ ሕዝቅኤል ከነበረበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው በምን መንገድ ነው? ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር የምንችለውስ እንዴት ነው?

26 በዘመናችን የአምላክ ሕዝቦች ያሉበት ሁኔታ ለእስራኤል ቤት ማስጠንቀቂያ የሚናገር ጉበኛ እንዲሆን ይሖዋ የሾመው ነቢዩ ሕዝቅኤል የነበረበትን ሁኔታ ያስታውሰናል። አምላክ “የምናገረውን ቃል ስማ፤ ማስጠንቀቂያዬንም ስጣቸው” ብሎት ነበር። ሕዝቅኤል ይህን ተግባሩን ችላ ቢል ኢየሩሳሌም ፍርዷን በምትቀበልበት ጊዜ በሚገደሉት ሰዎች ደም ተጠያቂ ይሆናል። (ሕዝቅኤል 33:7-9) ሕዝቅኤል ግን ታዛዥ ስለነበር ከደም ዕዳ ነፃ ሆኗል።

27 ዛሬም የመላው የሰይጣን ዓለም ጥፋት ከፊታችን ተደቅኗል። ስለሆነም የይሖዋ ምሥክሮች ግዴታቸውና መብታቸው እንደሆነ ተሰምቷቸው የአምላክን “የበቀል ቀን” እንዲሁም የመንግሥቱን መልእክት ይሰብካሉ። (ኢሳይያስ 61:2፤ ማቴዎስ 24:14) በዚህ አስፈላጊ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ እያደረግክ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ የስብከት ተልእኮውን በቁም ነገር ተመልክቶታል። በመሆኑም “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ [ነኝ] . . . ምክንያቱም የአምላክን ፈቃድ ሁሉ ለእናንተ ከመንገር ወደኋላ አላልኩም” በማለት ለመናገር ችሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:26, 27) ሁላችንም ልንከተለው የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!

28 እርግጥ ነው፣ አባታችን ከሆነው ከይሖዋ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ከፈለግን ለሕይወትና ለደም እሱ ያለውን አመለካከት ከመኮረጅ ያለፈ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንደሚብራራው በአምላክ ፊት ንጹሕ ወይም ቅዱስ ሆነን መኖር ያስፈልገናል።

^ አን.5 ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው መጽሔት፣ አምላክ “የፍጡር ሕይወት በደሙ ውስጥ ነው” ሲል የተናገረውን ሐሳብ በማስመልከት እንዲህ ብሏል:- “ምሳሌያዊ ትርጉሙን ብንተወው እንኳን ይህ አባባል ቃል በቃልም እውነት ነው:- ሁሉም ዓይነት የደም ሴል ለሕይወት የግድ አስፈላጊ ነው።”

^ አን.12 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የነሐሴ 2006 ንቁ! መጽሔት ገጽ 3-12ን ተመልከት።

^ አን.16 የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አዘጋጆች፣ ጥቅሱ በዕብራይስጥ የተጻፈበት መንገድ “በሴቲቱ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ብቻ የሚያመለክት ነው ለማለት አያስችልም” ይላሉ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የጽንሱ ወይም የሽሉ ዕድሜ በይሖዋ ፍርድ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ስለመኖሩ የሚናገረው ነገር እንደሌለ ልብ በል።

^ አን.70 ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት “ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችና የቀዶ ሕክምና ሂደቶች” የሚለውን ተጨማሪ መረጃ ተመልከት።